ኮሮናቫይረስ፡ ፖለቲካዊ አለመግባባት የሰውን ህይወት ለማዳን የሚደረገን ጥረት እንዳያደናቅፍ ዶ/ር ቴድሮስ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክትር ዶክትር ቴድሮስ አድኃኖም በፖለቲካዊ አለመግባባት ሳቢያ የሰውን ህይወት ለማዳን የሚደረገው ጥረት ሊደናቅፍ እንደሚችልም አስጠነቀቁ።
ከአሜሪካ ጋር አለምግባባት ውስጥ ስለገባው ድርጅታቸው በተመለከተ ዶክተር ቴድሮስ በስሜት ተሞልተው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት "በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ ምንም ምስጢር የለንም፤ የህይወት ጉዳይ በመሆኑ መረጃን ባገኘን ጊዜ ሁሉ እናጋራለን" ሲሉ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም "ከየት እንደመጣሁ ታውቃላችሁ፤ ስለጦርነት አውቃለሁ። ድህነትንም አውቃለሁ። ሰዎችን ለስቃይ ስለሚዳርጉ ነገሮች አውቃለሁ። ሰዎች እንዴት በድህነት ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉ አውቃለሁ" ሲሉ በስሜት ተናግረዋል።
"ይህን ሁሉ የማያውቁ ይኖራሉ. . . በቀላል የህይወት ጎዳና ላይ አልፈው ይሆናል። ምናልባትም ጦርነት ማለት፤ ድህነት ማለት ምን እንደሆኑ ላያውቁ ይችላሉ። ለዚህም ነው ስሜታዊ የሆንኩት" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ድርጅታቸው የኮሮናቫይረስን የተመለከተ ምንም አይነት መረጃ ከየትኛውም አገር አለመደበቁን በዘርዝር አብራርተዋል።
ዶክትር ቴድሮስ በቴሌቪዥን በተላለፈው መግለጫቸው ላይ እንዳሉት ከአሜሪካ የበሽታ መቆጠጠሪያና መከላከያ ማዕከል የተወከሉ 15 ባለሙያዎች ከጥር ወር ጀምሮ ስለበሽታው ያሉ መረጃዎችን በሙሉ እንዲያውቁ ሲደረጉ ቆይተዋል ብለዋል።
ትራምፕ ድርጅቱን በግልጽ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአግባቡ አልያዘውም ከማለታቸው በተጨማሩ ለቻይና ወገንተኛ ሆኗል በማለት ሲተቹ ቆይተዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አያያዙን በተመለከተ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ሲተች የቆየ ሲሆን፤ ባላፈው ሳምንትም አሜሪካ ለድርጅቱ ታበረክት የነበረውን የገንዘብ አስተዋጽኦ ማገዳቸው ይታወሳል።














