ትግራይ፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ "ቅቡልነት የለውም"- የትግራይ ክልል

የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሩፋኤል ሽፋረ የትናንቱ የፌዴሽን ምክር ቤት ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
አፈ ጉባኤው፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከመስከረም 25፣ 2013 ዓ. ም. ጀምሮ የሥልጣን ዘመኑ ማብቃቱን በማጣቀስ፤ ያስተላለፈው ውሳኔ "ሕጋዊ መሠረት የለውም፤ ተቀባይነት የለውም፤ ተግባራዊም ሊሆንም አይችልም" ብለዋል።
ከክልል መንግሥት በታች ያሉ የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ መዋቅሮችን የማደራጀት ሥልጣን የክልሉ መሆኑን የሚናገሩት አፈ ጉባዔው፤የፌደራል መንግሥት በቀጥታ ወደ ታች ወርዶ ሊሠራ የሚችልበት ሕጋዊ ሥልጣን የለውም በማለት ውሳኔውን "የአሃዳዊነት አስተሳሰብና ተግባር" ሲሉ ኮንነዋል።
አፈ ጉባዔ ሩፋኤል፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የብሔር ብሔረሰቦች ወኪል ነው ካሉ በኋላ፤ በዋናነት ከየክልሎች የሚወከሉ አባላት ያሉበት ምክር ቤት መሆኑን ይገልጻሉ።
ምክር ቤቱ ሥልጣኑን ከሕገ መንግሥቱ ውጪ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ያራዘመ ስለሆነ፤ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም ብለዋል።
"ምክንያቱም የክልል ምክር ቤቶችም ሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ማካሄድ አለባቸው" በማለት በቂ ያልሆነ ምክንያት በማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ሰጥቶ ሥልጣኑን ያራዘመ ስለሆነ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም ብለዋል።
ከዚህ በፊትም የትግራይ ክልል ምክር ቤት ተወካዮቹ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደማይሳተፉ አስታውቋል።
ለዚህም ምክንያቱ የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ስላበቃ፤ አዲስ ምርጫ ተደርጎ ክልሎች ወኪሎቻቸውን ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት መላክ ስላለባቸው መሆኑን አንስተዋል።
አፈ ጉባዔው፤ የምክር ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚነት የሌለው በማለት "ለሕጋዊ አካልና ለትግራይ ሕዝብ ያለውን ንቀት ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር" በማለት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሰው ምርጫ ላይ ተሳትፎ ተወካዮቹን መምረጡን አስታውሰዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምን ይላል?
የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የፌደራል መንግሥቱ ከሕግ ውጪ እየተንቀሳቀሰ ነው ካለው የትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ያውን ግንኙነት እንዲያቋረጥ ወሰነ።
ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የወጣውን መረጃ በመጥቀስ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ ማሳለፉ ተነግሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ድርጊቱ ሕግን ያልተከተለ መሆኑን ገልጾ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉ ይታወሳል።
ከዚያም በኋላ ክልሉ ምርጫውን ለማካሄድ በተዘጋጀበት ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ክልላዊው ምርጫ ሕገ ወጥና ተፈጻሚነት የሌለው እንደሆነ በመግለጽ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, HOF
ነገር ግን የምክር ቤቱ ውሳኔ በክልሉ መንግሥት በኩል ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቶ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ ምክር ቤት መቋቋሙ መገለጹ ይታወሳል።
ከትግራይ ክልል ምርጫ አንጻር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቶ፤ ክልሉ የምክር ቤቱን ውሳኔ አክብሮ ተግባራዊ ባለማድረጉ የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ወስኗል።
በዚህም መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳላፈውን ውሳኔ አላከበረም ያለው ትግራይ ክልል መንግሥትን በሚመለከት የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጿል።
በቀዳሚነት የትግራይ ክልል ያካሄደውን ከሕገ መንግሥቱ ተጻራሪ ነው ያለውን ምርጫ ተከትሎ ከተመሰረቱ የክልሉ ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግሥት ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ አሳልፏል።
በተጨማሪም የፌደራል መንግሥት የክልሉን ሕዝብ የልማትና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ፍላጎት ላይ በማተኮር የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ሕጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ ግንኙነት እንዲያደረግ ወስኗል።
የእነዚህ ውሳኔዎችም ተግባራዊነትና አፈጻጸም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እንዲሁም በሚመለከታቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በትግራይ ክልል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት እየተካረረ ሄዶ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከመስከረም 25 በኋላ ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት እንደሚያበቃ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ሰኞ ዕለት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በተለያዩ የፌደራል መንግሥት የፖለቲካ ሹመት ቦታ ላይ ያሉ አባላቱ ኃላፊነታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በወቅቱ አቶ ጌታቸው ረዳ "በአሁኑ ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ካቢኔያቸው፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ምንም አይነት ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም፤ ከእነዚህ አካላት ጋር ምንም አይነት ሕጋዊ ግንኙነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም" ብለዋል።
"መንግሥት በትክክለኛው መንገድ ለመመስረት የሚያስችል እድል እስኪገኝ ድረስ ግንኙነታችን ከእነዚህ ጋር ብቻ ይሆናል" በማለት "ፈርሰዋል" ካሏቸው ጋር ያላቸው ግንኙት መቋረጡን አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ መንግሥቱን በሚጻረር ተግባራት ላይ ተሰማርቷል በማለት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የቆው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሲገልጽ ቆይቷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ከቀናት በፊት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይህንኑ በተመለከተ እንደተናገሩት "በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ክልሉ ሕገ-መንግሥቱን አደጋ ላይ ጥሏል" ለዚህም እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ መሰረት መኖሩን አመልክተዋል።
ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል የክልሉን ሕግ አውጪና ሕግ አስፈጻሚውን ማገድ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ አንዱ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም ለፌደራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋምና የፌደራል የፀጥታ አካላት በማሰማራት ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሌላኛው መሆኑን አፈጉባኤው ገልጸዋል።












