ቻይና፡ ሐሰተኛ መረጃ ያጠላበት የሕንድና ቻይና የድንበር ግጭት

ሰኔ ላይ በሕንድ እና በቻይና ድንበር ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ አሁንም በአካባቢው ውጥረት ይስተዋላል። በግጭቱ ቢያንስ 20 የሕንድ ወታደሮች ተገድለዋል።
ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ ላለመጋጨት እየተወያዩ ነው። ሆኖም ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በርካታ ሐሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ ይገኛል።
ከነዚህ ጥቂቱን እንመልከት።
የሚያለቅሱት ቻይናውያን ወታደሮች
የተወራው፡ ቻይናውያን ወታደሮች ወደ ድንበር ሲላኩ ያለቅሳሉ።
እውነታው፡ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ከአውድ ውጪ ተወስዶ የተሰራጨ መረጃ ነው።
ትዊተር ላይ የነበረ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል መስከረም ላይ በታይዋን ዜና ማሰራጫ ተላልፏል። ከዛም በሕንድ ተሰራጭቷል።
ቻይናውያን ወታደሮች ወደ ድንበር ሲላኩ ያለቅሳሉ በሚል ብዙዎች ሲሳለቁ ነበር።
ቪድዮው ከ300,000 ጊዜ በላይ ታይቷል። የሕንድ ሚዲያዎችም አስተላልፈውታል።
በቪድዮው የሚታዩት ቻይናውያን ወታደሮች አውቶብስ ውስጥ ሆነው በማንደሪን ስለ አገር ናፍቆት የሚያወሳ ታዋቂ ወታደራዊ ዘፈን እያዜሙ ነበር።
"በክብር የወታደር ኃይሉን ተቀላቀሉ" የሚል ጽሑፍም የደንብ ልብሳቸው ላይ ተለጥፏል።
ሆኖም ግን እነዚህ ወታደሮች ወደ ሕንድና ቻይና ድንበር እየሄዱ ስለመሆኑ የሚጠቁም መረጃ ቢቢሲ አላገኘም።
የቻይና መገናኛ ብዙሀን እንደሚሉት ወታደሮቹ አዲስ ምልምል ናቸው። ወደ አሁኒ ግዛት የተላኩት ወታደሮች፤ ቤተሰቦቻቸውን ተሰናብተው በሀዘን ተውጠው ነበር።
በቻይናው ማኅበራዊ ሚዲያ ዊቻት ላይ የተሰራጨ መረጃ ከወታደሮቹ አምስቱ ቲቤት ውስጥ ለመሰማራት ፍቃደኛ ነን ብለዋል። ወደ ሕንድ ድንበር ስለመሄዳቸው ግን የተባለ ነገር የለም።
መስከረም 22 አንድ የቻይና ሚዲያ ታይዋን ቪድዮውን ከቻይናና ሕንድ የድንበር ግጭት ጋር በማያያዟ "ውሸታም" ብሏታል።

ከቻይና በተለቀቀ ሙዚቃ ሕንዳውያን ደንሰዋል
የተወራው፡ ከቻይና ድምጽ ማጉያ በተለቀቀ ሙዚቃ ሕንዳውያን ወታደሮች ደንሰዋል።
እውነታው፡ ቪድዮው የተቀረጸው ድንበር ላይ ድምጽ ማጉያ መኖሩ ከመገለጹ በፊት ነው።
መስከረም 16 በሕንድ እና በቻይና ሚዲያ የቻይና ገዢ ፓርቲ ድንበር ላይ ያሉ ሕንዳውያን ወታደሮችን ለማዘናጋት የፑንጃቢ ሙዚቃ ለቋል የሚል መረጃ አውጥተዋል።
የቻይና መንግሥት ድምጽ ማጉያ ድንበር አካባቢ መትከሉ ተዘግቧል። ቦታው 24 ሰዓት በሕንድ ወታደሮች የሚጠበቅ ነው።
የሕንድና የቻይናም ሚዲያዎች የመከላከያ ምንጮቻቸውን ጠቅሰው መረጃውን ዘግበዋል። የሕንድ መከላከያ መረጃውን አላረጋገጠም።
ዘገባው ሲቀርብ ፎቶም ይሁን ቪድዮም አልታየም።
ሆኖም ግን የሕንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ወታደሮች በፑንጃቢ ሙዚቃ ሲደንሱ የሚያሳዩ የቆዩ ቪድዮዎች አሰራጭተዋል።
ቢቢሲ እነዚህ ቪድዮዎች ድምጽ ማጉያ ከመተከሉ በፊት የተቀረጹ መሆናቸውን ደርሶበታል።
አምስት ወታደሮች በፑንጃቢ ሙዚቃ ሲደንሱ የሚያሳይ አንድ ቪድዮ 88,000 ተመልካች አግኝቷል።
ቪድዮው በሕንድና ቻይና ድንበር ላድካህ ነው የተቀረጸው ቢባልም እውነታው ግን ምስሉ ከሕንድና ፓኪስታን ድንበር የተገኘ መሆኑ ነው።
የቻይና ሙዚቃ የሕንዳውያን ወታደሮችን ጆሮ አሳምሟል።
የተባለው፡ ቻይና በትልቅ ድምጽ ማጉያ በምታጫውተው ሙዚቃ ሳቢያ የሕንድ ወታደሮች ጆሯቸውን ታመዋል።
እውነታው፡ በተባለው መሣሪያ ድንበር ላይ ሙዚቃ ስለመከፈቱ ማስረጃ የለም።
በቻይናዊ የትዊተር ተጠቃሚ የተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ቻይና ከመጠን በላይ የሚጮህ ሙዚቃ ከፍታ አንዳንድ የሕንድ ወታደሮች ጆሯቸውን መታመማቸውን ይጠቁማል። ከ200,000 ጊዜ በላይ ታይቷል።
ቪድዮው በሕንድ ሚዲያም ታይቷል።
ቪድዮው የተቀረጸው 2016 ላይ ነው። በቻይና የሚሠራ የተንቀሳቃሽ ስልክ ማስጠንቀቂያን ለማስተዋወቅ ነበር የተለቀቀው።
በምስሉ 4.6 ቶን የሚመዝን የማስጠንቀቂያ ደውል መስጫ ሲሽከረከር ይታያል። መሣሪያው ተፈጥሯዊ አደጋ ሲከሰት ለሕዝብ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደተባለው ሙዚቃ ለመልቀቅ የሚውል መሣሪያ አይደለም። የቻይና ወታደሮች ድንበር ላይ መሣሪያውን ስለመጠቀማቸውም እርግጠኛ መረጃ የለም።
በተጨማሪም ድንበር አካባቢ ጆሮውን የተጎዳ ሕንዳዊ ስለመኖሩ ሪፖርት አልተደረገም።

የመኪና አደጋው
የተባለው፡ የመኪና አደጋ የገጠመው ሕንድ የጸጥታ አባል ጉዳይ ከድንበር ውጥረቱ ጋር ይያያዛል።
እውነታው፡ አደጋው የተከሰተው ድንበር አካባቢ አይደለም።
የቻይና የትዊተር ተጠቃሚ መስከረም 21 ላይ "ሕንድ ከቻይና ጋር ስምምነት ላይ ልትደርስ አትችልም። ምክንያቱም ወታደሮቿ ራሳቸውን እንዳይገሉ ለመታደግ እየሞከረች ነው" በማለት አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ለጥፎ ነበር።
በቪድዮው በከፊል ወንዝ ውስት የሰጠመ የወታደር አውቶብስ በወታደሮች ተከቦ ይታያል። የሕንድ ወታደሮች በድንበር ላድከህ አካባቢ ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደሞከሩም ይጠቁማል።
ወደ 5,000 ጊዜ ገደማ ታይቷል።
ቪድዮው እውነተኛ ቢሆንም የተቀረጸው በቻይና እና በሕንድ ድንበር አይደለም።
አደጋው የተከሰተው በማዕከላዊ ሕንድ ነው። በወቅቱ የሕንድ መገናኛ ብዙሀን ዘግበውትም ነበር።












