አውሮፓ፡ አንድ አገር ኮሮናቫይረስን ማሸነፉ እንዴት ይታወቃል?

የኮሮናቫይረስ መከላከል ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምዕራብ አውሮፓ አገራት በምጣኔ ሀብት ተቀራራቢ ቢሆኑም ኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ የተለያየ ውጤት አስመዝግበዋል።

በእርግጥ የትኞቹ አገራት ከሌሎቹ በተሻለ ወረርሽኙን ተከላከሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ቀላል አይደለም። ከግምት የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ።

ለምሳሌ ሞት እንዴትና መቼ ይመዘገባል? የሚለው በአገራት መካከል ልዩነት አለው።

እንዴት በአገራት መካከል ልዩነት ተፈጠረ?

ጀርመንን እንደ ማሳያ ብንወስድ የሞት መጠኑ በ100,000 ሰዎች 11.5 ነው። በጎረቤቷ ቤልጄም ግን በ87 እጥፍ ይበልጣል።

የፈረንሳይ የሞት መጠን በ100,000 ዜጎች 48ሲሆን፤ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ደግሞ ቁጥሩ 63.3 ነው።

አገራቱ በሽታውን ለመከላከል ተቀራራቢ እርምጃ ወስደዋል። አካላዊ ርቀት ማስጠበቅ እና የእንቅስቃሴ ደገብን መጥቀስ እንችላለን።

ታዲያ ልዩነቱ እንዴት መጣ? የሚለው አነጋጋሪ ነው።

የጣልያን አጎራባች ከተሞች ሎምባርዲያ እና ቬኔቶ የሞት መጠናቸው 167 እና 43 ነው።

ጀርመን ከሌሎች አገሮች በበለጠ በሽታውን መቋቋም ችላለች ቢባል መታየት ያለባቸው ነጥቦች አሉ።

የመጀመሪያው አንድ አገር ወረርሽኙን ለመግታት የወሰደው እርምጃ አፋጣኝ ነበር? የሚለው ነው።

የጀርመኑ ሳይንቲስት ክርስችን ድሮትሰን “ጀርመን በሽታውን አሸንፋለች ተብሎ የደስታ መግለጫ ተላልፏል። ይህ እንዴት እንደሆነ ግን አይታወቅም። ከሌሎች አገሮች ጋር ተመሳሳይ እርምጃ ብንወስድም ቀድመን መተግበራችን የተለየን ያደርገናል” ይላሉ።

ጀርመን በከፍተኛ ሁኔታ ምርመራ ታደርጋለች። የጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍሎቿም ብዙ ናቸው። በተጨማሪም መራሔተ መንግሥቷ አንግላ መርኬል ሳይንቲስት መሆናቸው ጀርመንን ጠቅሟታል።

መራሔተ መንግሥቷ ኮቪድ-19ን የሚመለከቱ መረጃዎችን ይተነትናሉ። አገሪቷ ከፍተኛ ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባት የገለጹትም መረጃ አጠናቅረው ነበር።

መንግሥት ለሕዝብ የሚሰጠው መረጃ

የጀርመኑ ሳይንቲስት እንደሚሉት፤ አንድ ማኅበረሰብ በአግባቡ መረጃ ከተሰጠው ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ ይወስዳል።

የቤልጄም መንግሥት አማካሪ ፕ/ር የቭስ ቫን ላተም እንደሚሉት፤ መንግሥት የሚሰጠው መረጃ ሕዝቡን ግራ አጋብቷል። በፍጥነት የሚለዋወጥ መረጃ ለዜጎች እየቀረበ ነበር።

“መንግሥት አንድ ሐሳብ ይሰነዝርና ወዲያው ይለወጣል። ሚያዝያ እና ግንቦት ላይ ሰው በሽታውን ፈርቶ ስለነበር የሚባለውን ይሰማ ነበር። አሁን ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም የሞት መጠን አነስተኛ ስለሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊነቱ አይታያቸውም” ይላሉ።

ቤልጄም ቀድመው የእንቅስቃሴ ደገብ ካላሉ አገሮች አንዷ ናት። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግን ግዴታ ነው።

ጎረቤት አገሯ ኔዘርላንድስ የጭምብል ሕጓን ለማጥበቅ ጊዜ ወስዶባታል። ከዛ ግን በመደብር እና በመጓጓዣ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ነው ተብሏል።

አንድርስ ተግነል የተባሉት የስዊድን ቫይሮሎጂስት እንደሚሉት ሕዝቡ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ጫና ማሳደር አስፈላጊ ነው።

ጊዜው ገና ነው?

የፈረንሳይ ጤና ሚንስትር ኦሊቨር ቬረን አዲስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የተገበሩት የአካባቢውን አስተዳደሮች ሳያማክሩ ነበር።

ባርና ሬስቶራንት እንዲዘጋ ውሳኔ አሳልፈው ነበር። ሀኪም የሆኑት የግዛቱ አስተዳዳሪ ግን ውሳኔውን “ያልተገባ” ብለውታል።

ወረርሽኙን በተመለከተ የአገራትን ምላሽ ማወዳደር ቀላል አይደለም።

አካላዊ ርቀትን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የተለያዩ አገሮች የተለያየ ሕግ አላቸው። ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩኬ፤ አንዳቸው አንድ ሜትር ሌላቸው ሁለት ሜትር መራራቅ ግዴታ ነው ይላሉ።

የትኛው ውሳኔ ነው ትክክል? ለሚለው ምላሽ ለመስጠት ጊዜው ገና ነው።

ስቶክሆልም፣ ለንደን እና ፓሪስ ያሉ በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች አንዳቸው ከሌላቸው የተለየ ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡ ማየትም የተለመደ ነው።

አንዱን አስተያየት ከሌላው ጋር አሁን ላይ ለማወዳደር ያስቸግራል።

ኮሮና
Banner