ሩሲያና ቻይና በአሜሪካ ምርጫ ማን እንዲያሸንፍ ነው የሚፈልጉት?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እውን ክሬምሊን "ዳግም አሜሪካን ታላቅ ማድረግ" የሚለው የትራምፕ ሕልም ነው የሚስማማት? ለዚህም ተግታ ትሰራለች?
እውን ቻይና ለባይደን ያላሰለሰ ድጋፍ እየሰጠች ነው? ትራምፕ አንገት ላይ ገመድ እያስገባች ነው?
በመጪው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ሦስት አገሮች ስለአሜሪካ ከአሜሪካኖች በላይ ሊጨነቁ ይችላሉ። ቻይና፣ ሩሲያና ኢራን።
እነዚህ አገሮች የሚፈልጉት ሰው እንዲመረጥ በይፋም በህቡዕም፣ በቀጥታም በእጅ አዙርም የሚችሉትን ሀሉ ከማድረግ አይቆጠቡም። ምክንያቱም በአሜሪካ ወደ ዋይት ሐውስ የሚዘልቀው ሰው ጎሮሯቸውን ሊከፍተው ወይም ሊዘጋው ስለሚችል ነው
ወራት ብቻ በቀሩት የአሜሪካ ምርጫ የትኛው አገር ማን እንዲመረጥ ይሻል? ለምን? የሚለውን በአጭሩ እንቃኝ። ለጊዜው ኢራንን እናቆያት።
ሩሲያ
ሩሲያ በባለፈው የ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ዶልታለች፣ ፈትፍታለች የሚለው የአደባባይ ምስጢር ነው። ትራምፕና ወዳጆቻቸው ቢክዱትም። ፍርድ ቤት በቂ መረጃ አላገኘሁም ቢልም።
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚያምነው ሩሲያ ዶናልድ ትራምፕን የዛሬ 4 ዓመት ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት እጃቸውን ይዛ አስገብታቸዋለች። የትራምፕ ሰዎችና የሩስያ ሰዎች አብረው ሻይ ቡና ሳይሉ አይቀርም።
የሳይበር ጥቃት በማድረግም ሒላሪን አሳጥተዋታል። ዲሞክራቶችን አሽመድምደዋል። የአገሬውን መራጭ ወደ ትራምፕ እንዲያጋድል በበይነ መረብ ጠልፈው ጥለውታል። አባብለውታል። ሩሲያ ይህን ለማድረግ በቂ አቅም ፈጥራለች።
ባለፈው ወር ሪፐብሊካኖች የመሩት የሴኔት ጉባኤ ሩሲያ ትራምፕ እንዲመረጡ ስለመፈለጓ ተጨማሪ መረጃን ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ይህ ወንጀል ሆኖ ትራምፕን በሕግ የመጠየቁን ነገር አልገፋበትም።
በ2020 ሒላሪ በባይደን ተተክተዋል። ሩሲያም ሒላሪን እንዳበሻቀጠች ባይደንን ነክሳ ይዛለች።
የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነትና ስለላ ክፍል ኃላፊ ዊሊያም ኢናቪና እንደሚሉት ምክትር ፕሬዝዳንት ባይደንን ለማደናቀፍ ሩሲያ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ከፍታለች።
በሰሞኑ መደማመጥ በራቀውና የሰፈር ጎረቤታሞች ብሽሽቅ ይመስል በነበረው የቀጥታ የቴሌቪዥን ክርክር ባይደን ዶናልድ ትራምፕን "የፑቲን አሻንጉሊት" ሲሉ የገለጽዋቸው ወደው አይደለም። ትራምፕ ለፑቲን በይፋም በጓዳም አድናቆት አላቸው። ምናልባትም ከፖለቲከኛ እንደ ፑቲን የሚያስቀናቸው ሰው የለ ይሆናል።
የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሮስቶፎር ሬይ እንደሚያምኑት ሩሲያ መቼም ቢሆን በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ መፈትፈቷን ትታ አታውቅም።
ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ሳይቀር ሩሲያ እጇን ማስገባቷን በመጥቀስ ክርስቶፎር ሬይ ክስተቱን "ለ2020 ተውኔት ቃለ ተውኔት ልምምድ ላይ ያለች ትመስል ነበር" ብለዋል።
ሩሲያ በበኩሏ እኔ በውጭ አገር ምርጫ ምን ጥልቅ አደረገኝ ስትል ድርጊቱን እንደካደች ነው። በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመርያ የክሬምሊን ቃለ አቀባይ አሜሪካኖች የሚያቀርቡትን ክስ "ደንብረው የሚዘላብዱት ነገር ነው" ሲሉ ተሳልቀውበታል።
ሩሲያ ዶናልድ ትራምፕ ለ2ኛ ዙር ዋይት ሐውስ ቢቆዩላት ምርጫዋ ሲሆን ከዚህ በላይ የምትፈልገው ግን በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ትርምስን መፍጠር ነው ይላሉ የደኅንነት ጉዳይ አጥኚዎች።
ለምሳሌ የአውሮፓ ኅብረት አንድ ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ ሩሲያ ከአብዛኛዎቹ ኮሮናቫይረስን ከሚመለከቱ ሐሳዊ ዜናዎች ጀርባ ያለች አገር ናት። ይህን የምታደርገውም ትርምሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ስለሚያስገኝላት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጆ ባይደን ምን አሉ?
ባይደን ሩሲያን ጠንከር ባለ ቃል አስጠንቅቀዋል። ሩሲያ በሉአላዊት ልዕለ ኃያል አሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ እጇን አስገብታ መፈትፈቷን በቶሎ ካልገታች የምትከፍለው ዋጋ ይኖራል ብለዋል።
የፑቲን አሻንጉሊት የሚሏቸው ዶናልድ ትራምፕም ከጠላት አገር ጋር መሞዳሞዳቸውን እንዲተዉ አሳስበዋል።
ባይደን በሩሲያ ላይ ያላቸው አቋም ይህን ሲመልስል ዶናልድ ትራምፕ ግን ራሺያ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ እጇ አለበት የሚለውን ነገር እንዳጣጣሉት ነው የቆዩት።
ትራምፕ በዚህ ረገድ የራሳቸው የደኅንነት አለቆች ከሚያቀርቡት ሪፖርት ይጣረሳሉ። እንኳን ከባለሥልጣናት ጋር ከራሳቸው ንግግርም ጋር ለሚቃረኑት ትራምፕ ይህ እምብዛምም አስገራሚ ነገር ላይሆን ይችላል።
ቻይና ማን ቢመረጥ ምኞቷ ነው?
አሁን በአሜሪካ የሚወጡ የደኅንነት ሰነዶች እንዲሚደመድሙት ከሆነ አሁን ለአሜሪካ ምርጫ ስጋትና ውጋት የምትሆነው ከሩሲያ ይልቅ ቻይና ናት።
ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር የቻይና ከሩሲያ በላይ ስጋት መሆን ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፤ በሰነዶች የተደገፈ ነው ይላሉ።
በምክር ቤቱ የደኅንነት ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ዲሞክራቱ አዳም ስኪፍ አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባርን ቀጣፊ ይሏቸዋል።
ሚስተር ኢቫኒና እንደሚሉ የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት "ቻይና ዶናልድ ትራምፕ ዳግም እንዲመረጡ አትፈልግም" ምክንያቱ ደግሞ ትራምፕ የሚጨበጡ ሰው አለመሆናቸው ነው።
ይህንንም ለማሳካት ቻይና በይነ መረብን ተጠቅማ በአሜሪካ ምርጫ እጇን ማስገባት ከፍተኛ ፍላጎት አላት።
ቻይና በበኩሏ በሌሎች አገሮች ጉዳይ ገብቶ ለወሰን ፍላጎት የለኝም ብላለች።
ዶናልድ ትራምፕ የቻይና እሳቸው እንዲመረጡ አለመፈለግ የተስማማቸው ይመስላል። ለምሳሌ ብሪትባርት በተባለ ድረገጽ የወጣውን አንድ ዜና ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው አጋርተዋል። ዜናው የሚያትተው ቻይና ባይደን እንዲመረጡ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ነው።
የሚገርመው ግን ይህ ድረ ገጽ ጭልጥ ያለ የትራምፕ ደጋፊ መሆኑ ነው።
"ታዲያሳ! ቻይናዎች ባይደንን እንደሚፈልጉ ምን ጥርጥር አለው። ቢሊዮን ዶላር ወስጄባቸዋለኋ! ከቻይና ወስጄ ለአሜሪካ ገበሬዎች ሰጥቼዋለኋ! ከቻይና ወስጄ ለአሜሪካ ግምጃ ቤት ገቢ አድርጊያለኋ። ባይደን ካሸነፈማ ቻይና አሜሪካንን ኪሷ ጠቅልላ ከተተቻት ማለትም አይደል?" ብለዋል ትራምፕ።
የአሜሪካና የቻይና ግንኙነት አሁን ላይ መሬት ነክቷል። በሁሉም ነገር ቅራኔ ውስጥ እየገቡ ነው ያሉት። ኮሮናቫይረስን 'የቻይናው ጉንፋን' እያሉ ነው የሚጠሩት ትራምፕ።
ሆንግኮንግን እየሰለቀጠቻት ያለቸው ቻይና አሜሪካንን ብቻም ሳይሆን አውሮፓን በሙሉ አስቆጥታለች። ቲክቶክንና ሁዋዌን እየተነኮሱ አስቸግረዋታል።
ቻይና ትራምፕን ብትጠላ ከበቂ በላይ ምክንያት አላት።















