ትራምፕ በጠና ታመው አገር መምራት ቢሳናቸው ምን ይፈጠራል?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ አጠቃላይ ምርጫ ሊከናወን ሳምንታት ሲቀሩት ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

ወደ ሆስፒታልም ተወስደዋል። ፕሬዝዳንቱ የበሽታውን ምልክትም ማሳየት ጀምረዋል፣ ትኩሳት አላቸው። ድካም እየተመሳቸውም ነው።

በቅድሚያ ትራምፕ እራሳቸውን ለይተው በሚያቆዩበት ወቅት ምን ሊያመልጣቸው ይችላል የሚለውን እንይ።

የአሜሪካ የመድኃኒትና ተዛማች በሽታዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሰው እራሱን ለ10 ቀናት ለይቶ ማቆየት ይኖርበታል የሚል ምክር ሃሳብ አለው።

የትራምፕ ውጤት የተሰማው መስከረም 21 ነው። በዚህ የሲዲሲ መመርያ መሠረት ቢያንስ እስከ ጥቅምት 1 ድረስ እራሳቸውን ለይተው ያቆያሉ።

ይህ ማለት ትራምፕ ጥቅምት 5 ላይ ለማካሄድ ቀጠሮ በተያዘለት ሁለተኛው ፕሬዝደንታዊ የመድረክ ክርክር ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

የፊታችን አርብ በፍሎሪዳ ሊያደርጉ ያሰቡት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ግን መገኘት አይችሉም። በዚህም ምክንያት በአካል ይደረግ የነበረው የምርጫ ቅስቀሰው እንዲሰረዝ ተደርጓል።

ትራምፕ እስከ ጥቅምት 1 ድረስ ለማካሄድ ያቀዷቸውን የምርጫ ቅስቀሳዎች ወይ ሰርዘዋል አልያም ወደ ሌላ ጊዜ አዘዋውረዋል።

ምርጫው ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ አለ?

ትራምፕ እራሳቸውን ለይተው ማቆየታቸው የምርጫ ቅስቀሳ ስራቸውን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም።

ይህ ግን የአሜሪካንን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማራዘም በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም።

የአሜሪካ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን የመቀየር መብት ያለው ሕግ አውጪው አካል እንጂ ፕሬዝደንቱ አይደሉም። የታችኛውና የላይኛው ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ሊወስኑ ይገባል፡፡

ምርጫውን የማራዘሙ ነገር በተለይ በዲሞክራቶች በተሞላው የታችኛው ምክር ቤት ያልፋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ሆኖም በሁለቱም ምክር ቤቶች አብላጫ ቢጸድቅ ምርጫው ወደ ሌላ ቀን ሊሸጋገር ይችላል፡፡

የምርጫ ቀኑ እንኳ ቢቀየር የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት አንድ ፕሬዝደንት ዳግም በምርጫ እስካላሸነፈ ድረስ የሥራ ዘመኑ ከአራት ዓመት በላይ ሊሆን አይችልም ስለሚል የትራምፕ የሥራ ዘመን እአአ ጄነዋሪ 20፣ 2021 ላይ ያበቃል።

ስለዚህ የምርጫ ቀኑን የመቀየር ሃሳብ ካለ ቅድሚያ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከምክትላቸው ማይክ ፔንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ ከምክትላቸው ማይክ ፔንስ

ትራምፕ በጠና ታመው አገር መምራት ቢሳናቸው ምን ይፈጠራል?

ለጊዜው ትራምፕ ቀላል ሊባል የሚችል የበሽታው ምልክት አሳይተዋል።

ይሁን እንጂ እድሜያቸውን እና የሰውነት ክብደታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ ቀደም በእርሳቸው የእድሜ ክልል እና ክብደት ውስጥ የሚገኝ ሰው በኮሮናቫይረስ በጠና የመታመም እድሉ ከወጣቶች አንጻር ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ ከፍ ይላል።

ትራምፕ በጠና ታመው ኃላፊነታቸው መወጣት የማይችሉ ከሆነ ሥልጣናቸውን ለምክትል ፕሬዝደንቱ አሳልፈው ይሰጣሉ።

ትራምፕ ወደ ቀደም አቋማቸው እስኪመለሱ ድረስ ማይክ ፔንስ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሆነው ይቆያሉ ማለት ነው።

ማይክ ፔንስም ኃላፊነታቸውን መወጣት የማይችሉበት ምክንያት ቢፈጠር ስልጣኑ ወደ ዲሞክራቷ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ ይሸጋገራል ማለት ነው።

ናንሲ ፔሎሲ ኃላፊነቱን ለመቀበል ካልቻሉ በአራተኛ ደረጃ ላይ ሆነው ሥልጣን ሊረከቡ የሚችሉት የሪፐብሊካን ሴናተሩ እና 87 ዓመት አዛውንቱ ቻርልስ ኢ ግራሰሌይ ናቸው።