ሩሲያ ፡ ጋዜጠኛዋ በአደባባይ እሳት ለኩሳ በአሰቃቂ ሁኔታ እራሷን አጠፋች

የፎቶው ባለመብት, IRINA SLAVINA/FACEBOOK
ሩሲያዊቷ ጋዜጠኛ ወደ ሞስኮ ወደሚገኘው ሩሲያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ደጅ ከሄደች በኋላ አደባባይ ላይ ራሷን በእሳት አጋይታ ለህልፈት ተዳረገች።
ኢሪና ስላቪና ይህን አሰቃቂ እርምጃ በራሷ ላይ ከመውሰዷ ቀደም ብሎ ፌስቡክ ሰሌዳዋ ላይ የሚከተለውን ጽፋ ነበር። "ለእኔ ሞት የሩሲያ መንግሥትን ተጠያቂ እንድታደርጉ እለምናችኋለው።"
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ድርጊቱን መፈጸሟን ያመኑ ሲሆን አስከሬኗ በእሳቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
ስላቪና ሐሙስ ዕለት ፖሊስ የምትኖርበት ቤት መጥቶ ፍተሻ እንዳደረገ ገልጻ ነበር። መኖርያ ቤቷ ውስጥ ብርበራው የተካሄደው ምናልባት በሩሲያ ዲሞክራሲ እንዲያብብ ከሚሰራው የ'ኦፕን ሩሲያ' ቡድን ጋር ግንኙነት ካላት በሚል ነው።
ከብርበራው በኋላ ኮምፒውተሯን፣ ቤት ውስጥ የነበሩ ላፕቶፖችንና ፍላሽ ዲስኮችን እንዲሁም ሌሎች መረጃዎች ተወስደውባት ነበር።
ጋዜጠኛዋ ራሷን በእሳት ለኩሳ ስታቃጥል የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት በመጋራት ላይ ይገኛል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አንድ ሰው የለኮሰችው እሳት ሊያጠፋላት ወደ እርሷ ሲሮጥ፤ እርሷ በተቃራኒው ነፍሷን ሊያድን የሚሞክረውን ሰው ገፍትራ ስትጥለውና ስትከላከለው ይታያል።
በመጨረሻም እሳቱ እየበላት ተዝለፍልፋ ትወድቃለች።
ይህም የሆነው ጎርኪ ተብሎ በሚጠራው የሞስኮ ጎዳና ላይ ነው።
የሩሲያ ምርመራ ኮሚቴ ኢሪና ስላቪና በተባለው መንገድ መሞቷን አረጋግጦ ነገር ግን ቤቷን አልበረበርንም ሲል ክዷል።
ኢሪና 'ኮዛ ፕሬስ' የተሰኘ የአንድ የዜና ድረ ገጽ ዋና አዘጋጅ ነበረች። የድረ ገጹ መሪ ቃል "እውነትን ሳንሱር አናደርግም" የሚል ነበር።
ኢሪና ስላቪና ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነበረች።
















