ሩሲያ ባለስልጣኖቿ እንዳይሰደቡ የሚከለክል ህግ አወጣች

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ በተለይ የባለስልጣናቴን ስብዕና የሚያንቋሽሽና በአጠቃላይ የሩሲያን ክብር የሚነካ ነገር እያየሁ አልታገስም ለዚህም የመከላከያ ህግ ያስፈልገኛል ብላለች።

ህጉም በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ የፕሬዝዳንት ፑቲንን ፊርማ ብቻ እየጠበቀ ነው። በሌላ በኩል የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨትና ማጋራትም ሩሲያን ያሳሰበ ጉዳይ በመሆኑ ሌላ ህግ እንዲዘጋጅለት ተደርጓል።

ሁለቱንም ረቂቅ ህጎች የሩሲያ የላይኛው ምክር ቤት ከተወያየባቸው በኋላ በሚቀጥለው መጋቢት 13 ፕሬዝዳንት ፑቲን ፈርመውባቸው ህግ ሆነው እንደሚወጡ ይጠበቃል።

በሁለቱም ህጎች ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ከፍተኛ ቅጣት የሚጠብቀው ሲሆን ስም በማጉደፍ የተጠረጠረ ግለሰብ እስከ 15 ቀናት እስራት ሊቀጣ ይችላል።

ህጉን ተላልፎ ባለስልጣናትን ያጥላላ ወይም ስብዕናቸውን የሚነካ ጽሁፍ ወይም ንግግር ያሰራጨ ግለሰብ 100000 ሩብል ወይም 1500 ዶላር ሊቀጣ ይችላል።በድጋሚ ተመሳሳይ ችግር ከፈጸመ ደግሞ ቅጣቱ ሁለት ወይም ሶስት እጥፍ ይሆናል።

የሃሰት ዜና ያሰራጨ ደግሞ ግለሰብ ፣ ባለስልጣንና የቢዝነስ ተቋማት ተብሎ የተከፋፈለ ሲ ሆን በቅደም ተከተል 300000 ፣600000 እና 1 ሚሊዮን ሩብል እንደሚቀጡ ረቂቅ ህጉ ያትታል።

በህጉ መሰረት ከሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር ፈቃድ ወስደው የሚሰሩ የብሮድ ካስት ሚዲያዎች ፍቃድ እስከመነጠቅ ገደብ ሲጣልባቸው የዜና መረቦች ደግሞ ያለቅድመ ማሰጠንቀቂያ ሊዘጉ ይችላሉ።

ይህንን ተከትሎም ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ሚንስትሮችም ጭምር ረቂቅ ህጉን በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

ኒኮላይ ስቫኒድዜ የተባለው ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ሲናገር "ይህ አረመኔ የሆነ ምክር ቤት ጋዜጠኞች እንዳይናገሩና እንዳይጽፉ አንደበታቸውን ሊዘጋቸው ነው" ብሏል።

የድረገፅ ዘጋቢዎችም የመንግስትን ድክመት የሚናገሩ የሌሎችን ሰዎች ሃሳብ እንዳንወስድ ለማሸማቀቅ ታሰቦ የተሰራ ነው እያሉ ነው።

የፓርላማ አባሉ ፓቬል ክራሸኒኒኮቭ እንደገለጹት ግን ህጉ "በድረ ገጽ የተከፈተን ሽብርተኝነት ለመከላከል ነው"። ሌላኛው የፓርላማ አባል አናቶላይ ቪቦርኒ እንደገለጹት ደግሞ ህጉ የተዘጋጀው "ስነ ምግባር ያለው ዜጋን ለመፍጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን ነው"።