ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሆስፒታል ገቡ

ትራምፕ ወደ ሆስፒታሉ ሲደርሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ወደ ሆስፒታሉ ሲደርሱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ከተገለጸ በኋላ ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ።

ፕሬዝዳንቱ ትኩሳት አላቸው። ዋይትሐውስ ትንሽ ድካም ተሰምቷቸው ነው እንጂ መንፈሳቸው ጠንካራ ነው ብሏል።

ትራምፕ አሁን በሆስፒታል ሆነው ገና ሙከራ ላይ ያለው መድኃኒት እየወሰዱ እንደሆነ ተሰምቷል። ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ አብረዋቸው ናቸው።

ትራምፕ ወደ ሆስፒታል በሄሊኮፕተር ከነጩ ቤተ መንግሥት ሲወሰዱ ቀድሞ ይሳለቁበት የነበረውን የአፍና የአፍንጫ ጭምብልን ግጥም አድርገው ለብሰው ታይተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የተወሰዱት ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው የዋልተር ሪድ ብሔራዊ የወታደራዊ ህክምና ማዕከል ነው።

ወደ ሄሊኮፕተሩ ሲያቀኑ እጃቸውን አውለብልበዋል። በአውራ ጣታቸውም የደህና ነኝ ምልክት አሳይተዋል።

በዝምታ ሄሊኮፍተር ውስጥ የገቡት ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው ቀደም ብሎ የተቀረጸ ቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።

'ደህና ነኝ ብዬ እገምታለሁ። ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ይሄዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ባለቤቴም ደህና ናት። ስለሁሉም እናመሰግናችኋለን" ብለዋል።

የትራምፕ ልጆች ኢቫንካ እና ኤሪክ በትዊተር ሰሌዳቸው አባታቸውን "ጀግና፣ እጅ የማይሰጠው፣ ተፋላሚው" ብለው ካወደሷቸው በኋላ "እንወድሀለን" ብለዋቸዋል።

ትራምፕ አሁን የገቡበት የዋልተር ሪድ ሆስፒታል የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በብዛት የጤና ምርመራ የሚያደርጉበት ስፍራ ነው።

ትራምፕ ከልዩ ረዳታቸው ጋር በኤይርፎርስ ዋን አውሮፕላን ለነበረባቸው የፕሬዝዳንታዊ ክርክር ወደ ኦሃዬ አቅንተው ከተመለሱ በኋላ ነው ረዳታቸው ሆፕ ሒከስ በተህዋሲዋ መጠቃቷን ተከትሎ ምርመራ ያደረጉት።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኬይሊ ማካነኒ "ትራምፕ በጣም ደህና ናቸው። የተወሰነ የጉንፋን ምልክት ከማሳየታቸው ውጪ እንዲያውም በሥራ ላይ ናቸው" ብላ ነበር።

አሁን ሆስፒታል የተወሰዱትም "እንደው ለከፍተና ጥንቃቄ ሲባልና ሐኪሞቻቸውም ይህ እንዲሆን ስለጠየቁ እንጂ…ደህና ናቸው" ብላለች ቃል አቀባያቸው።

ሆኖም ሌሎች ትራምፕ ደህና እንዳልሆኑ መገመት ይቻላል ይላሉ።

በተለይም እድሜያቸው መግፋቱና ክብደታቸውም አሳሳቢ በመሆኑ ትራምፕ ክፉ እጣ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የሚገምቱም አልጠፉም።

ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሥራ ላይ ናቸው። ሥልጣናቸውን ወደ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ አላስተላለፉም። ማይክ ፔንስ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን ለጊዜው ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል።

ትራምፕ በትዊተር ላይ በለቀቁት ቪዲዮ መጠነኛ መገርጣት ይታይባቸዋል። በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት መውሰዳቸው፣ እድሜያቸው 74 መድረሱና ከፍ ያለ ክብደት ያላቸው መሆኑ ነገሩ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ከባይደን ጋር በነበራቸው የቀጥታ የቴሌቪዥን ክርክር ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ጭምብል አዘውትረው ማልደረጋቸው ላይ ሲሳለቁ ነበር።

ጆ ባይደን ኮሮናቨዓይረስ ምርመራ ወዲያውኑ አድርገው እሳቸውም ሆኖ ባለቤታቸው ነጻ እንደሆኑ ተነግሯቸዋል።

ጆ ባይደን ለትራምፕና ለባለቤታቸው ሚላኒያ ጤንነትን ተመኝተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተራ ጉንፋን ነው፣ በራሱ ጊዜ ይጠፋል በሚል ተገቢውን ክብደት አልሰጡትም ሲሉ ተቀናቃኞቻቸው ይተቿቸዋል።

ትራምፕ ለወባ በሽታ ፈዋሽነቱ የሚታወቀውን ሀይድሮክሲክሎሮኪውን መድኃኒትን በተደጋጋሚ ሰዎች እንዲወስዱ ሲወተውቱ ነበር። ከዚህ በፊት ይህንኑ መድኃኒት እንደወሰዱትና ጥሩ እንደሆነም ተናግረው ያውቃሉ።

አሁን እርሳቸው ሀይድሮክሲክሎሮኪውንን ወስደው ይፈወሱ ይሆን ወይ የሚለው የጠላትም የወዳጅም ጥያቄ ሆኗል።

ትራምፕ አሁን የሚወስዱት መድኃኒት ረምዴስቪር የተባለ ጸረ-ቫይረስ መድኃኒት ነው። ይህ መድኃኒት በኢቦላ ፈዋሽነቱ ይታወቃ።

የትራምፕ በተህዋሲው መያዝን ተከትሎ ሴናተሮችና ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዲሁም ረዳቶቻቸው ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል።

እስከአሁን ምክትል ፕሬዝዳንቱና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተህዋሲው እንደሌለባቸው ተረጋግጧል። ሆኖም የቀድመው የፕሬዝዳንቱ አማካሪ ኬሌያን ኮንዌይ፣ ሁለት የሪፐብሊካን ሴናተሮች ማይክ ሊ እና ቶም ቲሊስ ቫይረሱ ተግኝቶባቸዋል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ ቢል ሰቴፒን በተመሳሳይ ተህዋሲው ተገኝቶበታል።