አሜሪካ፡ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ለማየት ሆስፒታል ጥለው ወጡ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ከሆስፒታል ውጪ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው ከሆስፒታል ውጪ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ

የዶናልድ ትራምፕ የጤና ሁኔታ የዓለም ሚዲያ ልዩ ትኩረት ሆኗል፡፡

ለዚህ አንዱ ምክንያት የሳቸው መታመም መጪው ምርጫ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ነው፡፡

በአሜሪካ የምርጫው አሸናፊ ሊከተለው የሚችለው ፖሊሲ የብዙ አገራትን እጣ ፈንታ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚነካ መሆኑ ሌላ ምክንያት ነው፡፡

በሜሪላንድ አቅራቢያ ወታደራዊ ሆስፒታል የሚገኙት ትራምፕ ጤናቸውን በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው በሚለው ጉዳይ ላይ እርስበርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎች እየወጡ ባሉበት ወቅት ጥቁር ሱፍ ያለ ከረቫት ለብሰው ከሆስፒታል ወጣ ብለው በመታየት ዓለምን አስደንቀዋል፡፡

ከሰዓታት በፊት (በአሜሪካን እሑድ ዕለት) ትራምፕ ባልተጠበቀ ሁኔታ በጥቁር መኪናቸው የኋላ መቀመጫ ሆነው ከሆስፒታል ውጭ ታይተዋል፡፡

ከሆስፒታል የወጡትም ጤና እንዲሆኑ የሚመኙላቸውን ደጋፊዎቻቸውን ሰላም ለማለትና አድናቆታቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ እርሳቸው የሚገኙበት መኪና ከሆስፒታሉ ደጅ ዋናው አስፋልት ላይ ወዲያ ወዲህ ሲዟዟር ታይቷል፡፡

ይህ የትራምፕ ያልተጠበቀ ድርጊታቸው አንዳንድ ተቺዎቻቸውን አስቆጥቷል፡፡

ዶናልድ ትራምፕን ከሆስፒታል በመኪና ይዘዋቸው የወጡት ሾፌራቸውና ጠባቂዎቻቸው ሁሉም ራሳቸውን ማግለል ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡ ምክንያቱም በአንድ መኪና ውስጥ ቫይረሱ ካለበት ሰው በዚያ ቅርበት መቀመጣቸው ለበሽታው ተጋላጭ ስለሚያደርጋቸው ነው፡፡

ትራምፕ የሚታከሙበት ሆስፒታል ዋልተር ሪድ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ ሐኪሞች ሳይቀሩ ድርጊቱን ተችተዋል፡፡

በጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ የአጣዳፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር ዶ/ር ጀምስ ፍሊፕ በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት ‹የትራምፕ መኪና ከጥይት ይከላከል ይሆናል እንጂ ከቫይረሱ አይከላከልም፡፡ መኪናው ውስጥ አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል›› ብለዋል፡፡

መመርመርና ለ14 ቀናት የጤና ውሸባ መግባትም ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

‹‹ከ205 ሺህ በላይ አሜሪካዊያን ሞተዋል፡፡ አሁን የምንፈልገው ቆራጥ አመራር ነው፡፡ ለፎቶ ከአልጋ የሚነሳ መሪ አይደለም›› ብለዋል የታችኛው ምክር ቤት የዲሞክራቲክ ተወካዮች ሊቀመንበር ሐኪም ጀፍሪስ፡፡

ትራምፕ ከመኪናቸው ሳይወርዱ በመስኮት እጃቸውን እያውለበለቡ ደጋፊዎቻቸውን ሰላም ብለዋል፡፡

ትራምፕ በአሜሪካ ሰዓት አቆጣጠር ምናልባትም ከሰዓታት በኋላ (ሰኞ ማምሻው ድረስ) ሙሉ በሙሉ ከተኙበት ከዋልተር ሪድ ሆስፒታል ወጥተው ወደ ዋይት ሐውስ ቤታቸው ሊያመሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ትራምፕ ሆስፒታል ሳሉ ጤናቸው በምን ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር የሚለው አሁንም የጠራ መረጃ የለም፡፡

ኮሮና
Banner

መጠነኛ የኮቪድ ምልክቶችን ከማሳየት ባሻገር ደህና ሆነው ነው የቆዩት የሚለው መረጃ ግን የተሳሳተ እንደነበረ ተረጋግጧል፡፡

የግል ሐኪማቸው ጭምር እንዳመኑት ትራምፕ የኦክሲጅን መጠናቸው ወርዶ ወርዶ ይተነፍሱ የነበረው ኦክሲጅን ተገጥሞላቸው እንደነበር ኋላ ላይ የወጡ መረጃቸው አስረድተዋል፡፡

የኦክሲጅን መጠናቸው የወረደው ደግሞ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ነበር፡፡

ይህም በመሆኑ ስቴሮይድ ዴክሳሜታዞን መድኃኒት እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

ዴክሳሜታዞን መድኃኒት እንዲወስዱ የሚደረጉ ታማሚዎች ሞት አፋፍ ላይ ሲሆኑ ወይም በሽታው ለሕይወታቸው እጅግ አደገኛ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡

ትራምፕ ይህን መድኃኒት ይወስዱ ነበር የሚለው መረጃ ለሚዲያ የተነገረው እጅግ ዘግይቶ ነበር፡፡

ከዚህ መድኃኒት በተጨማሪም ገና በሙከራ ላይ የነበሩ መድኃኒቶችንም ሲወስዱ እንደነበረ ተገልጧል፡፡

ትራምፕ በዚህ ለሕይወታቸው አስቸጋሪ በሆነ ሰዓት እንኳ ደህና ስለመሆናቸውና ከሆስፒታል ሆነው ሥራቸውን እያጧጧፉት እንደሆነ ነበር ሲገልጹ የነበረው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ትናንት እሑድ ሆስፒታሉን ለአፍታ ጥለው ወጥተው ደጅ የሚገኙ ደጋፊዎቻቸውን ቃኝተው ከመመለሳቸው ጋር ተያይዞ በትዊተር ሰሌዳቸው የስላቅ የሚመስል መልእክት ትተዋል፡፡

‹‹አሁን ስለ ኮቪድ ብዙ ተምሪያለው፡፡ ትምህርት ቤት ሄጄ ነው የተማርኩት፡፡ ይህ ትክክለኛ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ደብተርና እስክሪብቶ የማያስፈልግበት ትምህርት ቤት፡፡ ኮቪድ ምን ማለት እንደሆነ ብዙ አውቂያለው፡፡ ያወቅኩትንም አሳውቃለሁ፡፡›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በኮቪድ ጉዳይ ላይ ሲሳለቁ የኖሩ መሪ ናቸው፡፡ በተህዋሲው መያዛቸው ከተረጋገጠ ወዲህ ለሕይወታቸው አስጊ ሆኖ የታየው ያለ መጠን መወፈራቸውና እድሜያቸውም 74 በመሆኑ ነበር፡፡