ኮሮናቫይረስ፡ ከትራምፕ በፊት በኮቪድ የተያዘችው የትራምፕ አማካሪ ሆፕ ሂክስ ማነች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠው የፕሬዝደንቱ የቅርብ ረዳታቸው ሆፕ ሂክስ በኮሮናቫይረስ መያዟ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
ከፕሬዝደንቱ ለወራት ሲያጣጥሉት በቆዩት ቫይረስ መያዛቸው ከተነገረ በኋላ በተደጋጋሚ ስሟ እየተነሳ ያለችው ሆፕ ሂክስ ለበርካቶች አዲስ ናት።
የ31 ዓመቷ ወጣት የቀድሞ ሞዴል ስሟ በአደባባይ እንዲነሳ ብዙም ፍላጎት የላትም።
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የነበሩት አንቶኒ ስካራሙቺ በ2017 ላይ ከሥራቸው ሲሰናበቱ ነበር ሆፕ ሂክስ በቦታቸው ተተክታ የፕሬዝደንቱ የቅርብ ረዳት የሆነችው።
ሆፕ በዚህ የሥራ መደብ ላይ ስትመደብ ምንም አይነት የፖለቲካ ልምድ አልነበራትም።
ታዲያ በወቅቱ የ28 ዓመት ወጣት እና የፖለቲካ ልምድ የሌላት ሆፕ እንዴት በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ለፕሬዝደንቱ የቀረበ ከፍተኛ ሥልጣንን ልትይዝ ቻለች?
ሆፕ፣ ኢቫንካ እና ትራምፕ
ሆፕ 2017 ላይ የፕሬዝደንቱ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሆና ከመሾሟ አምስት ዓመታት በፊት ከትራምፕ ቤተሰብ ጋር ትውውቅ እንደነበራት ይነገራል።
ሆፕ፤ የዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ልጅ የሆነቸው ኢቫንካ ለምትመራው የፋሽን ኩባንያ የሕዝብ ግንኙነት ሥራን በመስራት ነበር ከፕሬዝደነቱ ልጅ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራት።
በተጨማሪም ሆፕ ሞዴል ነበረች። ራልፍ ሎውረን ለተሰኘው እውቅ የፋሽን ኩባንያ በሞዴልነት ሰርታለች። ለኢቫንካ የፋሽን ኩባንያ የሕዝብ ግንኑነት ባለሙያ ሆና በሰራችበት ወቅትም ስኬታማ ነበረች።
ከኢቫንካ ትራምፕ ጋር በቅርበት መስራቷና በሥራዋም ስኬታማ መሆኗ የዶናልድ ትራምፕን ትኩረት እንድታገን እድል ከፍቶላታል።
በመጀመሪያ ላይም እአአ 2014 ትራምፕ ለሚያንቀሳቅሱት የሪል ስቴት ኩባንያቸው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንድትከውን እራሳቸው መርጠው ሾሟት።
ሚሊየነሩ ትራምፕ ሆፕ ሂክስ በምታከናውነው ሥራ ደስተኛ ስለነበሩ "አስደናቂ ሰው ናት" ሲሉ ለአንድ መጽሔት ተናግረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሆፕ ወደ ፖለቲካው እንዴት ገባች?
ሆፕ ከአሜሪካ ባሻገር ዓለምን ወደሚያሽከረክረው የአሜሪካ የፖለቲካ መድረክ የተሳበችው በድንገት ነበር።
ይህም አለቃዋ ለፕሬዝደንትነት እጩ ሆነው እአአ በ2015 መግቢያ ላይ የመጀመሪያ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ለማድረግ ጉዞ ሲያደርጉ እንደ በአጋጣሚ ሆፕ ሂክስ አብራቸው ነበረች።
በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ፉክክር ውስጥ ከትራምፕ ጎን የመሆን እድል የገጠማት ሆፕ ከፖለቲካው ይልቅ እያከናወነችው በነበረው ሪል ስቴት ኩባንያው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ላይ የማተኮር ፍላጎቷ ነበር።
ነገር ግን የምርጫ ቅስቀሳው እየተጠናከረ ሲሄድ ሆፕ የእጩ ፕሬዝደንቱ የምርጫ ቅስቀሳ አካል መሆን ወይም የትራምፕ ሪል ስቴት ኩባንያ ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ ሆኖ መቀጠል በሚለው ላይ መወሰን ነበረባት።
በሥራዋ የሚተማመኑባት ዶናልድ ትራምፕም ለፕሬዝደንትነት በሚያደርጉ ፉክክር ውስጥ እንድታግዛቸው በፖለቲካ ውስጥ አብራቸው እንድትቆይ ጠየቋት።
እሷም ጥያቄውን ተቀብላ ሙሉ ትኩረቷን በፖለቲካው መድረክ የሕዝብ ግንኙነት ላይ አደረገች።

ትኩረት የማትሻው ሆፕ
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ወይም ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ ሆፕ ሂክስ ከጎናቸው አትታጣም። እሷ ግን ከማይክራፎን ፊት ሆና ማውራትን አትመርጥም።
የፕሬዝደንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባል በሆነችበት ወቅትም እራሷን ከማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች አርቃለች። በዚህም የትዊተር ገጿን የዘጋች ሲሆን የኢንስታግራም ገጿም ለሌሎች ዝግ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ ብዙ በተባለለት ምርጫ አሸንፈው ፕሬዝደንት ሲሆኑ በጽህፈት ቤታቸው ውስጥ ባዋቀሩት አዲስ ክፍል ውስጥ የዋይት ሐውስ ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር በመሆን በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ መስራት ጀመሩ።
ትራምፕ "ሆፕስተር" እያሉ የሚጠሯት ሆፕ ሂክስ ትራምፕ ከሚያምኗቸው የቅርብ ረዳቶቻቸው መካከል አንዷ እንደሆነች እና የፕሬዝደንቱን አመለካከት ማስቀየር ከሚችሉ በዙሪያቸው ካሉ ጥቂት አማካሪዎች መካከል ሆፕ አንዷ እንደሆነች ይነገራል።
ሆፕን የሚያውቋት ሰዎች የፕሬዝደንቱን ሃሳብ ወይም አመለካከት ማስቀየር ሳይሆን፤ ፕሬዝደንቱ ማድረግ የሚሹትን በቀላሉ መፈጸም የሚችሉበትን አማራጭ ነው የምታቀርበው ይሏታል።
'ፖለቲኮ' የተባለው ገጽ በአንድ ዘገባው እንደጠቀሰው ሆፕ ሂክስ የትራምፕ ቤተሰብን በጥልቀት ከሚያውቁት መካከል አንዷም ነች ብሏል።
ሆፕ ሂክስ ፕሬዝደንቱ በሚሄዱባቸው ቁልፍ ቦታዎች ሁሉ የምትገኝ ሲሆን በዋይት ሐውስ ውስጥ ከትራምፕ ጋር በየዕለቱ የቀረበ የሥራ ግንኙነት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዷ ነች።
ይህም ነው ፕሬዝደንቱ ትኩረት ነፍገውት ለሚሊዮኖች አሜሪካዊያን መታመምና ከ200 ሺህ ለሚልቁት ደግሞ ሞት የሆነው የኮሮናቫይረስ ከእሷ እንደተጋባባቸው የተነገረው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በወረርሽኙ መያዛቸው ዓለምን በማስደንገጥ የምድራችን ዋነኛ ርዕስ ሲሆን የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት መሆን የማትሻውንም ሆፕ ሂክስን ይፋ እንድትወጣ አድርጎ መነጋገሪያ አድርጓታል።















