ኢትዮጵያ፡ ፖለቲከኛ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ደራሲው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታዋቂው ምሁር፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰማ።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከሳምንት በፊት ታምመው ሆስፒታል መግባታቸው ተነግሮ የነበረ ሲሆን ህክምና እየተከታተሉ በነበረበት ጊዜ የጤናቸው ሁኔታ መሻሻሉን የቅርብ ሰዎቻቸው ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ማክሰኞ መስከረም 19/2013 ዓ.ም ለረቡዕ አጥቢያ ከቤተሰቦቻቸው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አዛውንቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዘጠና ዓመታቸው ማረፋቸው ተገልጿል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከአጼ ኃይለሥላሴ አስተዳደር ጊዜ አንስቶ የነበሩትን የኢትዮጵያ መንግሥታት በግልጽ በመተቸትና የሚያውቁትን፣ ያዩትን እንዲሁም የሚሰማቸውን በጽሁፍና በተለያዩ መንገዶች በመግለጽ የሚጠቀሱ ምሁር ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ1922 ዓ.ም የተወለዱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ወደ ዘመናዊው ትምህርት ከመግባታቸው በፊት በልጅነታቸው በቤተክርስትያን የሚሰጠውን ሐይማኖታዊ ትምህርት በመከታተል ድቁናን እንዳገኙ የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
ከዚያም በኋላ በአሁኑ የእንጦጦ አጠቃላይ፣ በቀድሞው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ጥሩ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎች መካከል ለመሆን ችለዋል።

"የሐሳብ ልዕልና ምልክት፤ የሰላማዊ ትግል አርአያ፣ ላመኑበት ነገር እስከ መጨረሻቸው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በማረፋቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል።" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

በዚህም በወቅቱ ኮከብ ከሚባሉት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ልቀው የተገኙት መስፍን ወልደማሪያም፣ በወቅቱ ለጎበዝ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው የውጪ አገር የትምህርት እድል አግኝተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ ባሳዩት ብቃት ከፍ ያለ ትምህርት እንዲከታተሉ ወደ ህንድ አገር በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ፣ በማስከተል ደግሞ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ፕሬፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ አብዛኛውን የሥራ እድሜያቸውን ወዳሳለፉበት የመምህርነት ሥራ በመሰማራት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አገልግለዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት እንዲሁም በትምህርት ክፍሉ ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ለክፍሉ ማስተማሪያ የሚሆኑ መጽሐፍትን በማዘጋጀትም ታላቅ ባለውለታ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሮፌሰር መስፍን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት ባገለገሉባቸውና ከዚያም ውጪ በነበሩት ጊዜያት በርካታ የጥናታዊ ጽሑፎችንና ሌሎች መጽሐፍትን አዘጋጀተው አሳትመዋል። እንዲሁም የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ጽሑፎች በማዘጋጀት በጋዜጦች፣ በመጽሔቶችና ፌስቡክን በመሰሉ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ጭምር ሲያካፍሉ ቆይተዋል።
በተለይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈተና ሆኖ የቆየውን እሳቸው "ጠኔ" የሚሉትን ረሃብ በተመለከተ ተጠቃሽ መጽሐፍትን አዘጋጅተው አሁን ድረስ ጉዳዩን በተመለከተ እንደማጣቀሻ ከሚቀርቡ ሥራዎች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ ነው።
ፕሮፌሰር መስፍን የአገሪቱ ተደጋጋሚ ፈተና የሆነውን ረሃብን በምሁር ዓይን በማየት ትኩረት እንዲያገኝ ምርምርና ጽሑፍ ከማዘጋጀት ባሻገር፣ በተለይም በንጉሡ ጊዜ የተከሰተውን ረሃብ ወደተለያዩ ቦታዎች በመሄድ በቅርበት ለመመልከት ከመቻላቸው ባሻገር የተቸገሩትን ለመርዳት ከባልደረቦቻቸው ጋር ጥረት እንዳደረጉ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Sileshi Yilma
ፕሮፌሰር መስፍን ከትምህርታዊ የምርምር ሥራዎቻቸው በተጨማሪም ፖለቲካውን ጨምሮ በአጠቃላዩ የዕለት ከዕለት ህይወታቸው የተመለከቷቸውን ጉዳዮች በማንሳትም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ትችትን እንዲሁም ምክሮችንም በጽሑፎቻቸው ያለፍርሃትና ይሉኝታ የሚያንጸባርቁ ምሁር ነበሩ።
ሃሳባቸውን በረጅሙ በመጽሐፍ፣ በመካከለኛ መጣጥፎች በመጽሔትና በጋዜጣ እንዲሁም በጣፈጠና በአጭሩ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያቀርቡት ፕሮፌሰር መስፍን በግጥምም ጠንካራ ሃሳባቸውን የሚገልጹ ምሁር ነበሩ።
ለዚህም ማሳያዋና አሁን ድረስ መነጋገሪያ እንደሆች ያለችው የፕሮፌሰሩ የሥነ ግጥም ስብስብ መድብል የሆነችው "እንጉርጉሮ" ማሳያ ናት። 'እንጉርጉሮ' የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት በተመረጡ ቃላት ጥልቅ መልዕክትን የያዘች የግጥም መጽሐፍ እንደሆነች በርካታ አንባቢያን አስካሁን ድረስ ይመሰክራሉ።
አስካሁንም በእንግሊዝኛ ከዘጋጇቸው መጽሐፍት ባሻገር በአማርኛ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት፣ አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ፣ሥልጣን ባሕልና አገዛዝ፣ ፖለቲካና ምርጫ፣ የክህደት ቁልቁለት፣ አገቱኒ፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ አድማጭ ያጣ ጩኸት፣ እንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ፣ አዳፍኔ፣ ፍርሃትና መክሸፍ፣ ዛሬም እንደ ትናንት እና ሌሎችም መጽሐፍትን አሳትመዋል።

የፖለቲካ ህይወት
ፕሮፌሰር መስፍን በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ጀመሩት ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ነበር። የሕዝቡ የመብትና የኑሮ ጥያቄዎች እንዲሁም በየዘመኑ ይነሱ የነበሩ የለውጥ ፍላጎቶችን በመደገፍ በተለያየ መንገድ ተሳትፈዋል።
በዩኒቨርስቲው ውስጥ ይነሱ የነበሩ የተማሪዎችን የለውጥ ጥያቄዎች ይደግፉ ስለነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን በንጉሡ ባለስልጣናት በኩል በጎ አመለካከት አልነበረም። ስለዚህም በሹመት ስም ከአዲስ አበባ እንዲወጡ ለማድረግ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጊምቢ አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው ቢነገራቸውም ሹመቱን ተቃውመውት ነበር።
ከዚያም በወቅቱ በወሎ ክፍለ አገር በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ለችግር ተጋልጠው የነበሩት ሰዎች ቀያቸውን እየተዉ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በሚሞክሩበት ወቅት ባለስልጣናት ረሃቡ እንዳይታወቅ ጥረት ማድረጋቸውን የተመለከቱት ፕሮፌሰር መስፍን ችግሩን ለሕዝቡ ለማሳወቅ የቻሉትን አድርገዋል።
በዚህም ረሃቡ ያስከተለውን ጉዳትና ለችግር የተዳረጉትን ሰዎች የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በዩኒቨርስቲው ውስጥ ላለው የመምህራን ማኅበር አቀረቡ። በዚህም ሳያበቁ ከተለያዩ ሰዎች እርዳታን በማሰባሰብ በረሃብ ለተጎሳቆሉት ሰዎች ለማድረስ ጥረት ማድረጋቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይመሰክራሉ።
አንዳንዶች እንደሚሉትም ፕሮፌሰር መስፍን ድርቁንና የተከተለውን ረሃብ በተመለከተ ሌሎች እንዲያውቁት በማድረግ በኩል ቀዳሚ ከመሆናቸው ባሻገር፤ የንጉሡ አስተዳደርን ኋላ ላይ ለውድቀት የዳረገው የተማሪዎች ጥያቄና እንቅስቃሴ ተጨማሪ ምክንያት ለመሆን በቅቷል ይላሉ።
ወታደራዊው ደርግ የንጉሡን አስተዳደር አስወግዶ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለበርካታ ሰዎች ዕልቂት ምክንያት የሆነውን የወሎ ክፍለ አገር ረሃብን በተመለከተ የሚያጣራው መርማሪ ኮሚሽን ውስጥም አባል ሆነው ሰርተዋል።
በደርግ ዘመን አብዛኘውን ጊዜያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በማስተማር ያሳለፉ ሲሆን፤ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እየበረታ በሄደበት ጊዜ የነበረው መንግሥት ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
ከዚያም ወታደራዊው መንግሥት በአማጺያኑ ኃይሎች ተሸንፎ ከስልጣን ሲወገድና ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የተባለ ድርጅት በማቋቋም በአገሪቱ ስለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ክትትል ማድረግና ሪፖርቶችን ማውጣት ጀመሩ።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለረጅም ዓመታት ኢሰመጉን በሊቀመንበርነት በመሩባቸው ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ የመንግሥት ኃይሎችና ባለስልጣናት የሚፈጸሙ ሪፖርቶችን ሲያወጡ ቆይተዋል።
ብዙ የተባለለትና ከባድ ቀውስን አስከትሎ የነበረው የ1997ቱ ምርጫ ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜም የቀስተ ዳመና ንቅናቄ ለማኅበራዊ ፍትህ (ቀስተ ዳመና) የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ ከእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ከሌሎችም ጋር እንዲመሰረት አድርገዋል።
ይህም ፓርቲ በኋላ ላይ በምርጫው ላይ ግዙፉን ኢህአዴግን በመገዳደር በኩል ትልቅ ሚና የነበረውን ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) የተባለውን ጥምረት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመመስረት ችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥም ፕሮፌሰር መስፍን የጎላ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል።
ምንም እንኳን ፕሮፌሰር በምርጫው ላይ ተወዳዳሪ ሆነው ባይቀርቡም በሚደረጉ የምርጫ ክርክሮች ላይ ቀርበው የፓርቲያቸውን ዓላማ በማብራራት ተሳታፊ ነበሩ።
በኋላም ከምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ውዝግብና ሳቢያ መንግሥት የቅንጅት አመራሮችን ሲያስር ፕሮፈሰር መስፍንም ለእስር ተዳርገው ነበር። ይህ እስር ግን የመጀመሪያቸው አልነበረም ቀደም ሲልም በተለያዩ ጊዜያት ታስረው ነበር።












