ልደቱ አያሌው፡ “አቶ ልደቱ በፍትሕ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ቆርጧል”

የአቶ ልደቱ አያሌው የመቶ ሺህ ብር የዋስትና መብት እንዲጸና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ያስተላለፈውን ማዘዣ ለቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ቢሰጡም፤ ፖሊስ አቶ ልደቱን አልለቅም ማለቱን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዘዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ ገለጹ።
"ፖሊስ አለቅም በማለቱ ተስፋ ቆርጠን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል። አቶ ልደቱ ምንም እንዳይደረግ ብሎ በመከልከሉ እኛም ጠበቆቹም ከዚህ በኋላ በፍትሕ ሥርዓቱ በኩል ተጨማሪ እንቅስቃሴ አናደርግም። እሱም ከልክሎናል እኛም አናምንበትም" ብለዋል አቶ አዳነ።
አቶ ልደቱ በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ እንደቆረጡ ገልጸው፤ "ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ከመጠበቅ ውጪ የትም አትሂዱ ብሎናል" ብለዋል።
የፍርድ ቤት ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል እየተሻረ እያዩ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በኋላ "ፍርድ ቤት አቅም አለው ብለን አንሄድም። የፍርድ ሂደቱን በፈለጉት መንገድ ያስኬዱታል። የፖለቲካ ውሳኔ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ስለጉዳዩ ትላንት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንዳደረጉ ገለጸዋል። ኮሚሽነሩ ከፖሊስ ጋር እንደሚነጋገሩ እንደገለጹላቸውም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ደብዳቤ ማስገባታቸውንም ገልጸዋል።
"ማንኛውም አካል ለፍርድ ቤት ውሳኔ ተገዢ መሆን አለበት። የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ከሄደ ሥርዓት አልበኝነት በአገሪቱ ነግሷል። አስፈጻሚው አካል ከማንም ቁጥጥር በላይ ሆኗል። ይህን እያደረገ ያለው የፖለቲካ ሥርዓቱ ነው" ሲሉም አቶ አዳነ ተናግረዋል።
አቶ አዳነ እንዳሉት፤ ፖሊስ ከፍርድ ቤት የተላለፈውን ውሳኔ ያልተቀበለው ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም የቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት በነፃ ሲያሰናብታቸው፣ ከዛ ደግሞ የመቶ ሺህ ብር ዋስ ሲወስንላቸው፣ አሁን ደግሞ ዋስትናው እንዲጸና ውሳኔ ሲተላለፍም ፖሊስ አቶ ልደቱን ከእስር እንዳልፈታቸው አስረድተዋል።
"አቶ ልደቱ ከጤናቸው አንጻር ውጪ ቢወጡም ከፍትህ ይርቃሉ፣ ይጠፋሉ ብለን አናምንም ስለዚህ ውጪ ወጥተው ይከራከሩ ብሎ እንዲለቀቁ ብሎ ነበር" ያሉት የፓርቲው ፕሬዘዳንት፤ አቶ ልደቱ በዛሬው ችሎት "ይህን ብትወስኑም ፖሊስ እንደማይለቀኝ አምናለሁ። ስለዚህ ከዚሁ ልሰናበት" እንዳሉም አክለዋል።
ፍርድ ቤቱ የዋስትናው መብት እንዲጸና ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍ ለአቶ ልደቱ ቢገልጽም፤ "እኛም እንደፈራነው፣ አቶ ልደቱም እንደፈሩት ፖሊስ አለቅም ብሏል" ብለዋል።
የትናንቱ የፍርድ ቤት ውሳኔ ምን ይላል?
የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ ከዚህ ቀደም ተፈቅዶላቸው የነበረው የመቶ ሺህ ብር ዋስትና እንዲፀና በትናንትናው ዕለት፣ ማክሰኞ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት መወሰኑን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አቶ አዳነ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ማክሰኞ ዕለት፣ መስከረም 26፣ 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት የዋስትና እግድን በተመለከተ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ሲሆን፣ የአቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄ እግድ አይገባውም፣ ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚለውን የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመቶ ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ የሚለውን ውሳኔ አፅንቶ እንዲፈቱም ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከዚህ ቀደም አቶ ልደቱ ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከራከሩና፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር የምስራቅ ሸዋ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳልፎ የነበረ ሲሆን የቢሾፍቱ ፖሊስ በበኩሉ አቶ ልደቱ "በአደራ ነው" ያሉት በማለት አልለቅም ማለቱ ይታወሳል።
ይህንንም ጉዳይ ማክሰኞ የዋለው ችሎት ላይ አቶ ልደቱ ስጋታቸውን መግለፃቸውን አቶ አዳነ ይናገራሉ።
"ከዚህ በፊት የነበረውን ሁኔታ በመጥቀስ ፖሊስ አልለቅም ሊል ይችላል፤ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ከዚሁ በነፃ ያሰናብተኝ የሚል ጥያቄ አንስተው ፍርድ ቤቱ ግን ለፖሊስ በአስቸኳይ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ የ100 ሺህ ብር ዋስትናውን ለወሰነው ለምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ትዕዛዙ እንዲደርስ በሚል ወስኗል" ብለዋል አቶ አዳነ።
ከዚህ ቀደም የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ በመቶ ሺህ ብር ዋስ ወጥተው ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከላከሉ በሚል ለመስከረም 20፣ 2013 ዓ.ም ውሳኔ አስተላልፎ ቀጠሮ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ያንን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ ወስደው እንዲያስፈፅም በጠየቁበትም ወቅት ፖሊስ አልፈታም ማለቱ ይታወሳል።
አቶ ልደቱም በእስር ለሁለት ቀናት ከቆዩ በኋላ የአቶ ልደቱ ዋስትና የሚታገድበት ክስ (አቤቱታ) አቃቤ ህግ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ መስከረም 20፣ 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎትም አቃቤ ህግ አቶ ልደቱ በዋስትና መውጣት የለባቸውም በሚል እንደ ምክንያትነት ያቀረባቸውን መከራከሪያ ሃሳቦች ሰምቷል።
አቃቤ ህግም አቶ ልደቱ ዋስትና እንዲከለከሉ ካቀረባቸው ምክንያቶች መካከል በዋስትና ቢወጡ የውጭ የህክምና ቀጠሮ ስላላቸው ሄደው ሊቀሩ ይችላሉ፣ ምስክሮችን ያስፈራራሉ፣ በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት ውጭ ሆነውም ተፅእኖ ይፈጥራሉ፤ እንዲሁም የተከሰሱበት የጦር መሳሪያ ክስ ከ18-20 አመት የሚያስፈርድ ነው የሚል ነው።
አቶ ልደቱ በበኩላቸው ውጭ ወጥተው ይቀራሉ ለሚለው "ከመጀመሪያውም ውጭ የህክምና ቀጠሮ እንዳላቸው የተናገርኩት እኔ ነኝ ይህንን በተናገርኩበት ሁኔታ አቃቤ ህግ እንደራሱ የክስ ጭብጥ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም፣ ውጭ ወጥቼም የምቀር አይደለሁም፣ ባለኝ ቀጠሮ ለመምጣት እንዲያመቸኝ ነው የውጭ ቀጠሮዬን የተናገርኩት።፡" ማለታቸውንም አቶ አዳነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቃቤ ህግ እንደ መቃወሚያ ላቀረበው " ምስክሮቹን ያስፈራሩብኛል' ለሚለው ምስክሮቹን ለማስፈራራት ምክንያት እንደሌላቸውና ምስክሮቹ መሳሪያው እጃቸው ሲገኝ ከተገኘ የታዘቡ ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሰው እሳቸው ደግሞ መሳሪያው በእጃቸው መገኘቱን ባልካዱበት ሁኔታ ምስክሮችን ሊያስፈራሩ እንደማይችሉም ተከራክረዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ደጋፊዎች ለተባለው" የፖለቲካ ፓርቲ ነው የምመራው ደጋፊዎች ይኖሩኛል፣ ደጋፊዎች ተፅእኖ ያሳድራሉ ብሎ የፖለቲካ አመለካከቴን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ የመብት ጉዳይ መነሳት የለበትም።" ብለዋል
በህገ ወጥ መሳሪያ ክስና ከ18-20 አመት ስለሚያስፈርድ በዋስ ሊለቀቁ አይገባም ብሎ አቃቤ ህግ ላቀረበውም መሳሪያውን የሰጣቸው መንግሥት መሆኑን የተናገሩት አቶ ልደቱ እየከሳሳቸውም ያለውም መንግሥት መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህንን ደግሞ እለመካዳቸውን ጠቅሰው "በኦሮሚያ ባለው ህግም ደግሞ ህጋዊ አድርግ ተብሎ ነው መጠየቅ ያለብኝ እንጂ ሊያስከስሰኝም የሚችል ስላይደለ በዚህ የዋስትና ጥያቄዬ መልስ ማግኘት አለበት" ብለው ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራና ቀኝ ክርክሮቹን ከሰማም በኋላ ገምግሞ ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ ልደቱ ውጭ ሆነው ቢከራከሩ ከፍርድ አደባባይ፣ ከፍትህ ይርቃሉ ብሎ እንደማያምን ፣ ከዚህ በፊት የነበራቸውም የፖለቲካ ተሞክሮ፣ ያላቸው ተደማጭነት፣ አሁንም ቢሆን ህግን አክብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በማየቱ ስለዚህ ቢወጡም ሊቀሩ እንደማይችሉ በማመን የአቃቤ ህግን አቤቱታ ውድቅ ማድረጉን አቶ አዳነ ይናገራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የመሳሪያው ክስም ከ18-20 አመት የሚል ቢሆንም በመሳሪያው የሞተም ሆነ ለመግደልም የታሰበ ሰው ስለሌለ፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱን ከባድነት ፍርድ ቤት ስላላመነበት ከዚህ በፊት የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔን አፅንቶታል።
የልብ ህመምተኛ የሆኑት አቶ ልደቱ ጤና ስጋት ላይ እንደጣላቸው የሚናገሩት አቶ አዳነ ሆኖም በቢሾፍቱ ያለው የፖሊስ ጣቢያ አያያዝም መልካም እንደሆነ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ እያመሩ ሲሆን ስጋቱ እንዳለ ሆኖ ፖሊስ የሚወስነው ውሳኔ ያለውን የፍትህ ስርአትም የሚያሳይ ይሆናል ብለዋል።














