"ልደቱ እዚሁ ጣቢያ ነው መታሰር ያለብኝ ብሎ ለምኖ ነው [ቢሾፍቱ] የቀረው"፡ የኢዴፓ ፕሬዝደንት አቶ አዳነ ታደሰ

የሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተፈጠረውን ሁከት በማነሳሳት፣ መምራትና በገንዘብ መደገፍ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው "ህገ መንግሥታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ" ሞክረዋል በሚል አዲስ ውንጀላ እንደቀረባባቸው ጠበቃቸው አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ገመዳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብታቸውን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት ውሳኔ ለማስተላለፍ በዋለው ችሎት ላይ ነው አቃቤ ህግና ፖሊስ አዲስ ክስ ያቀረቡባቸው።
የቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የፖሊስን ጥያቄ የህግ አግባብነት እንደሌለው ጠቅሶ ሳይቀበለው የቀረው ነሐሴ 25፣ 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነበር።
ፖሊስ አልለቅም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው እንደገና ማመልከቻ ያስገቡ የሚል ጥያቄም አንስቷል።
ፍርድ ቤቱም የፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ዘግቶ አቶ ልደቱ በሌላ መዝገብ የዋስትና ጥያቄያቸውን እንዲቀርብ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
በትናንትናው ዕለት በዋለውም ችሎት የዋስትና ጥያቄ መልስ ለመስጠት ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም አቃቤ ህግና ፖሊስ በግድያ ከመጠርጠር በተጨማሪ "ህገ መንግሥታዊ ስርአቱን በኃይል የመናድ" ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ የሚሉ ውንጀላዎች ቀርበዋል።
ለዚህም መሰረት የሆነው የሽግግር መንግሥትን ምስረታን ለመንግሥት እንደ አማራጭነት ያቀረቡት ሰነድ ሲሆን ይህም ጠበቃው እንደሚሉት ጥር ወር ገደማ የተፃፈ ሲሆን ሁከቱ ግን ከአርቲስቱ ሞት በኋላ የተከሰተ ነው።
በተጨማሪም አቶ ልደቱ እየፃፉት ነው የተባለውና ቤታቸው ውስጥ የተገኘው የመፅሃፍ ረቂቅ በአባሪነት የቀረበ ሲሆን በይዘቱ "ለውጡን የሚተችና ህገ መንግሥቱን ለመናድ ዝግጅት" የሚሉ አዳዲስ ውንጀላዎች ቀርበውባቸዋል ብለዋል።
"እነዚህ ምክንያቶች አቃቤ ህግ ዋስትና ለማስከልከል ያቀረባቸው ናቸው። የምርመራ መዝገቡን መሰረት ያደረጉ አይደሉም" የሚል ክርክር ማቅረባቸውንም ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ ልደቱ ገና በረቂቅ እንዳለና ለህዝብ ይፋ ያልሆነ ያልታተመ መፅሃፍ እንደሆነም ነግረዋቸዋል።
"ይሄ እንግዲህ በሃሳብ ደረጃ ያለ ስለሆነ፤ ማንኛውም ግለሰብ በሃሳቡ አይቀጣም። ሃሳብ ወንጀል አይደለም። እንዳያስብ ሁሉ ሊከለከል ነው ማለት ነው የሚል ነገር ነው አቶ ልደቱም ያነሱት" ብለዋል
ጠበቃቸው በበኩላቸው ዋስትና በኢትዮጵያ ህገ መንግሥትም ሆነ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መስረት መብት እንደሆነ ጠቅሰው ዋስትና የሚከለከልበት በአንዳንድ አጋጣሚ እንደሆነ ጠቅሰው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ደንበኛቸው የተጠረጠሩበት ወንጀል ግድያ የሌለበትና ከአስራ አምስት አመት በላይም ሊያስቀጣ ስለማይችል የዋስትና መብታቸው እንዲከበር መከራከሪያ ሃሳብ እንዳቀረቡም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቱ በጥዋት ቀጠሮው አቃቤ ህግና ፖሊስ በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ያቀረቡትን ውንጀላ የሚያስረዳ የምርመራ መዝገብ ማምጣት የሚለውን ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠትም ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
ትናንት ከሰዓት በዋለው ችሎትም አቃቤ ህግና ፖሊሶች የፖሊስ ምርመራ መዝገብ ማምጣት አንችልም በሚልም ብዙ እንዳንገራገሩ የገለፁት ጠበቃው የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ለዞን አቃቤ ህግ ተልኳል በማለት ምክንያት ሰጥተዋል።
ግራ ቀኙን ያየው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን ማምጣት አለባችሁ የሚል ውሳኔን አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ፣ ፖሊስ የምርመራ መዝገብና ማስረጃውን እንዲያቀርብ በማዘዝ ለዛሬ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን የምርመራ መዝገቡ ክስ ለመመስረት በቂ ነው ወይስ አይደለም የሚለውንም ሁኔታ የሚወስን እንደሆነ ጠበቃቸው ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለት አካልን ነፃ የማውጣት ክስን ለመመስረት ከደንበኛቸው ጋር መነጋገራቸውንም በተጨማሪ አስረድተዋል። ዋስትናን በሚመለከት ደግሞ በዛሬው እለት ፍርድ ቤቱ ውሳኔን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
"የዋስትና መብት ይከበር በሚል እኛ የምንከራከረው የነፃነትን መብት ለማስጠበቅ ነው" የሚሉት ጠበቃው አቶ ልደቱ፣ ከዚያም ባለፈ በህይወት የመቆየት ሁኔታቸውን ሊፈታተን የሚችል የሃኪም ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።
ከዚህ ቀደም የልብ ቀዶ ህክምና አድርገው አርቲፊሻል ነገር ልባቸው ላይ እንዳለ ሐምሌ 30፣ 2012 ዓ.ም አሜሪካን ሃገር የምርመራ ቀጠሮ ቢኖራቸውም እሱንም መሄድ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ በቀጠሮዎቹ ሲጠቀስ እንደነበርም አቶ አብዱልጀባር ያስረዳሉ ።
ከዚህም በተጨማሪ ደንበኛቸው የአስም ህመምተኛ ሲሆኑ ከልብ ህመማቸው ጋር ተያይዞ ለኮቪድ-19 ተጋላጭነታቸው በጣም ከፍተኛ እንደሚያደርገውና በአዲስ አበባ የሚገኘው ላንድ ማርክ ሆስፒታል የተያያዘው የሃኪም ማስረጃንም ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።
"በሕይወት የመኖር መብትና በነፃነት መካከል የመብት መበላለጥ ባይኖርም ሰው በህይወት ሲኖር ነው የነፃነት መብቱ የሚጠይቀው የእርሳቸው ትንሽ አስከፊ የሚያደርገው በህመም ላይ መሆናቸው ነው" ብለዋል አቶ አብዱልጀባር።
አቶ ልደቱ በመጀመሪያ የተጠረጠሩበት ወንጀል በቢሾፍቱ ከተማ ሁከት በማስነሳት መምራትና በገንዘብ መደገፍ የሚል ነበር።
በጊዜ ቀጠሮ በቆዩባቸው ወቅት ቤታቸው ሲበረበር በተገኙት ፅሁፎችና ሰነዶች የምርመራ ሂደቱ መልኩን ቀይሮ ወደ ሌላ ሁኔታ እያጋደለ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
"ህገ መንግሥታዊውን ስርዓት በኃይል የመናድ፣" አንቀፅ 238ን በመጥቀስ አቶ ልደቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ለዚች አገር የሽግግር መንግሥት ነው የሚበጃትና ሌሎች አማራጮችን ሲናገሩ ከነበሩት አንዳንድ ነገሮች ተገኝተዋል በሚል መልኩንም የቀየረው ቀድሞም እንደነበር ነው ጠበቃቸው ገልጸዋል።
በ25/12/12 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ሲዘጋ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቄያለሁ ብሎ እንደነበርና ሁለተኛ ደግሞ የምርመራ መዝገቡ ውስጥ ከዚህ በፊት መርማሪ ፖሊሶች ሶስት ምስክር ተሰምተው ነበር።
በኋላ ላይ ግን ፍርድ ቤት ሲያጣራ ግን በቢሾፍቱ አቶ ልደቱ ብጥብጥ አስነስተዋል፣ መርተዋል፣ ገንዘብ ደግፈዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ሶስት ምስክር የተባሉት የአቶ ልደቱ ቤት ሲበረበር በምርመራ እንዲገኙ በታዛቢነት የቆሙ ግለሰቦች መሆናቸውን ደርሶበታል ይላሉ።
በአጠቃላይ "እሳቸውን አስሮ ምርመራ ማድረግ ሳይሆን እንዲያውም ወንጀል የማፈላለግ ሁኔታ ነው ሲደረግ የነበረው" ይላሉ።
ፓርቲያቸው ምን ይላል?
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዘዳንት አቶ አዳነ ታደሰ፤ "አሁን ባለው ሂደት መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻል ተማምነን አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ለመመስረት ወስነናል" ብለዋል።
ፖሊስ አቶ ልደቱ ከቢሾፍቱ ወደ አዳማ ማረሚያ ቤት መሄድ አለባቸው ብሎ እንደነበረ ገልጸውም፤ "ልደቱ እዚሁ ጣቢያ ነው መታሰር ያለብኝ ብሎ ለምኖ ነው [ቢሾፍቱ] የቀረው" ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ አዳነ የዛሬው ፍርድ ቤት ውሎ የተቋጨው "በአሳዛኝ ሁኔታ" ነው ብለው፤ "አስፈጻሚው ከሕግ አውጪው በላይ ጡንቻ አለው ብለን ስለምናምን ሰኞ አዲስ አበባ ላይ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ እንመሰርታለን" ሲሉ ውሳኔያቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።












