የፍርድ ቤት ውሎ፡ ኢዴፓ የአቶ ልደቱ እስርን በሚመለከት ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደብዳቤ መጻፉን ገለፀ

አቶ ልደቱ አያሌው

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑትና በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ቢሾፍቱ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙትን አቶ አቶ ልደቱ በሚመለከት ቅዳሜ ዕለት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ደብዳቤ መጻፉን ፓርቲያቸው አስታወቀ።

ፓርቲው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የአቶ ልደቱ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነ በመጥቀስ "አቶ ልደቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከወንጀል ጋር የተገናኘ ድርጊት ፈጽመው ሳይሆን በፖለቲካ ታስረዋል ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን" መግለፁን አቶ አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፓርቲው በደብዳቤው ላይ አቶ ልደቱ በአሁኑ ሰዓት የታሰሩበት ሁኔታ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው መንግሥት ተመልክቶ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት መጠየቁን በተለይ ለቢቢሲ ገልጿል።

አቶ አዳነ አክለውም ይህ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና አቶ ልደቱ ዛሬ ሰኞ ጠዋት 4፡00 ሰዓት ላይ ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ የሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ችሎት የቀረቡትም ፖሊስ የደረሰበትን እንዲያስረዳ እንደነበር ተናግረዋል።

ፖሊስ ተጨማሪ ነገር ይዞ ሊቀርብ አለመቻሉን የሚናገሩት አቶ አዳነ "የሽግግር መንግሥት ሠነድ እጃቸው ላይ ተገኝቷል፤ በዚህ ሰነድ ሰበብም ብጥብጥና ሁከት ተነስቷል የሚል የፖሊስ ማስረጃ ችሎቱ ተመልክቶ ውድቅ አድርጎ፣ ከስልካቸው ላይ የተወሰዱ የድምጽና የመልዕክቶች ከቴሌ አስገልብጠናል እርሱን አደራጅተን፣ አስተርጉመን ለማቅረብ እንዲመቸን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይፈቀድልን ሲል ፖሊስ ጠይቋል" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ልደቱም ያሉበትን የጤና ሁኔታን በመጥቀስ የዋስትና ጥያቄ ቢያቀርቡም ችሎቱ በድጋሚ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን የተናገሩት አቶ አዳነ፤ አቶ ልደቱ ዛሬ ችሎት ፊት በቀረቡበት ወቅት ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ መታሰራቸውን በመጥቀስ፣ አምስት ጊዜም በነጻ መሰናበታቸውን፤ አሁንም በነጻ እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ብለዋል።

ጨምረውም አሁን እየታየ ያለው የፍትህ ሂደት ጥርጣሬ ላይ እንደጣላቸው በማስረዳት "ችሎቱ ለፖሊስ ብቻ እድል እየሰጠ እርሳቸውን ግን እያጉላላቸው እንደሆነ" ጠቅሰው ቅሬታቸውን እንዳቀረቡ አቶ አዳነ ተናግረዋል።

ችሎቱም ፍርድ ቤቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ እንደሆነ በመግለጽ፤ ነገር ግን ከቴሌ መጣ የተባለው ድምጽና የመልዕክት ማስረጃ መተርጎምና መቅረብ ስላለበት ለመጨረሻ ጊዜ በሚል የሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ልደቱ አያሌው ለቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ መርማሪ ፖሊስ ለምርመራ ተጨማሪ ሰባት ቀናት እንደተፈቀደለት አቶ አዳነ ገልፀው ቀጣይ ቀጠሮ ለነሐሴ 25 ተሰጥቷል ብለዋል።

አቶ ልደቱ አያሌው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ አመጽና ተቃውሞ እንዲነሳ ሲቀሰቅሱና ሲያስተባብሩ ነበር በሚል ከአዲስ አበባ በፌደራል ፖሊስ ተይዘው ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ጉዳያቸው በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።