የአቶ ልደቱ ጤና፣ የአቶ በቀለ የረሃብ አድማ እንዲሁም የአቶ ደጀኔ በኮሮና መያዝ

አቶ ልደቱ አያሌው ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ልደቱ አያሌው ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ደጀኔ ጣፋ

ከሳምንታት በፊት የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ፖለቲከኞች መካከል የተወሰኑት ዛሬ ችሎት ፊት ቀርበዋል።

በዚህም መሰረት ከኢዴፓ አቶ ልደቱ አያሌው ለመጀመሪያ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የጤናቸው ጉዳይ ተነስቶ ነበር።

የኦፌኮው አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ ዛሬ የችሎት ቀጠሮ የነበራቸው ሲሆን ባለቤታቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት አቶ በቀለ ከቅዳሜ ጀምሮ ምግብ አልበላም ማለታቸውንና የባንክ አካውንታቸው መታገዱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ከኦፌኮ አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ ኮርሳ ደቻሳ ዛሬ ችሎት መቅረብ የነበረባቸው ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ስለተገኘባቸው ህክምና ላይ በመሆናቸው በጠበቃቸው መወከላቸው ቢቢሲ ከጠበቃቸው ተረድቷል።

የአቶ ልደቱ ጤናና ተጨማሪ ቀጠሮ

ባለፈው አርብ በፌደራል ፖሊስ አዲስ አበባ ውስጥ ተይዘው ወደ ቢሾፍቱ የተወሰዱት አቶ ልደቱ አያሌው ከሦስት ቀናት እስር በኋላ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የፓርቲያቸው ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ ለቢቢሲ ገለጹ።

የአቶ ልደቱ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ፖሊስ ጥርጣሬውን በአግባቡ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለማቅረቡን በመጥቀስ ደንበኛቸው የአስምና የልብ ህመም ያለባቸው በመሆኑ ጤንነታቸው ከግምት ገብቶ በዋስ ተለቅቀው ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው ጉዳያቸው ቋሚ አድራሻቸው ባለበት አዲስ አበባ ውስጥ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

ነገር ግን የአቶ ልደቱን ጉዳይ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ለታሳሪው ጤና አስፈላጊ መሻሻል እንዲደረግ በማዘዝ፣ የተጠረጠሩበት ድርጊት የተፈጸመው ቢሾፍቱ መሆኑንና ችሎቱም ጉዳዩን መመልከት ስልጣን እንዳለው ጠቅሶ አዲስ አበባ ይታይ የሚለውን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረገው አቶ አዳነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ችሎቱ ፖሊስ ምርመራውን ለማከናወን የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ተቀብሎ የአቶ ልደቱን ጉዳይ መልሶ ለመመልከት ለነሐሴ 4/2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጠ የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ አዳነ ተናግረዋል።

የአቶ በቀለ የረሃብ አድማና የባንክ አካውነት እገዳ

በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር አባል አቶ በቀለ ገርባ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ሃና ረጋሳ ለቢቢሲ ገለጹ።

ለዚህም ምክንያቱ በሚጠይቋቸው ሰዎች ላይ የተጣለው ገደብ እንደሆነ ወ/ሮ ሃና ተናግረው አቶ በቀለን መጠየቅ የሚችሉት ሦስት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም ባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው ብቻ እንዲሆን በመደረጉ "ከልጆቼ መርጬ እንዲጠይቁኝ አላደርግም፤ ልጆቼ እኔን ማግኘት አለባቸው፤ እኔም ልጆቼን ማግኘት አለብኝ" ማለታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በእነዚህ ምክንያቶችም ከቅዳሜ ጀምሮ ምግብ እንዳልገባላቸው ጠቅሰው "ምግብ እንዲገባልኝ ስለፈቀዱ፤ ለእኔ ትልቅ ነገር አይደለም። አንድ እስረኛ የሚገባው መብት ካልተከበረልኝ ፤ ምግብም አታምጡልኝ" በማለት ምግብ እንዳይወስዱ እንደከለከሏቸው አስረድተዋል።

ዛሬ ጠዋትም ቁርስ ይዘውላቸው እንደሄዱና "ፍርድቤት ሄጄ መናገር ያለብኝ ተናግሬ፣ መጠየቅ ያለብኝን ጠይቄ፣ መልስ ሳገኝ እበላለሁ" በማለት ምግቡን ተቀብለው እንዳስቀመጡት ገልፀዋል።

ወ/ሮ ሃና አክለውም የአቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የመላው ቤተሰቡ የባንክ አካውንት መታገዱንም ተናግረዋል።

አካውንቱ ለምን እንደተዘጋ እንደማያውቁ የሚናገሩት ወ/ሮ ሃና፤ "በቀለም የመንግሥት ሠራተኛ ነው፤ ነጋዴም አይደለም። በአካውንታችን ላይ የተለየ ገንዘብ የለም። እኔም ቢሆን ሠራተኛ አይደለሁም" በማለት ለእለት መተዳዳሪያ ያስቀመጧትን ገንዘብ ሊያወጡ በሄዱበት የእርሳቸውና የባለቤታቸው አካውንት መታገዱ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

ሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀናት ምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ባለመቀበል ስምንት ተጨማሪ ቀናት ሰጥቷል።

አቶ ደጀኔና የአቶ ኮርሳ በኮሮናቫይረስ መያዝ

በቅርቡ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ ኮርሳ ደቻሳ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው ህክምና ላይ እንደሆኑ ጠበቃቸው አቶ ደጀኔ ፈቃዱ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዚህም ሳቢያ ታሳሪዎቹ በቀጠሯቸው መሰረት ዛሬ የፍርድ ቤት መገኘት ሳይችሉ መቅረታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

በወረርሽኙ ተይዘዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የተመለከተው ችሎት ፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተጨማሪ ስምንት የምርመራ ቀናትን እንደፈቀደ አቶ ደጀኔ ለቢቢሲ ገልጸዋል።