ኮሮናቫይረስ፡ ኮቪድ-19 ምን እንደሆነ አናውቅም የሚሉት 10 አገራት

በፕላው የሚገኝ ሆቴል

የፎቶው ባለመብት, Palau Hotel

ኮቪድ ዓለምን አምሷል፡፡ እኛ ግን አናውቀውም የሚሉ 10 አገሮች አሉ ብንላችሁስ፡፡

ለመሆኑ እነዚህ አገሮች እነማን ናቸው? የማያውቁት ኮቪድ እንዴት እያደረጋቸው ይሆን?

1.ፕላው (Palau)

ይቺ አገር የት ያለች ትመስልዎታለች? ሩቅ ምዕራብ ፓስፊክ ነው የምትገኘው፡፡

ማይክሮኒዢያ ሪጂን በሚባለው አካባቢ ከነ ፊሊፒንስ እና ኢንዶኒዢያ ነጠል ብላ በባትሪ ተፈልጋ የምትገኝ ጢኒጥ ደሴት ናት፡፡

እዚያ ፕላው የሚባል ሆቴል አለ፡፡ ድሮ በ1982 ነበር የተከፈተው፡፡ ያኔ የአገሩን ስም የያዘው ይኸው እስከዛሬ አለ፡፡ በአገሩ ሌላ ሆቴል የሌለ ይመስል፡፡

በፓስፊክ ውቅያኖስ ሰማያዊ ቀለም ውሀ ውስጥ ጠብ ያለች ነጥብ የምትመስለው ይቺ አገር የቱሪስት አገር ናት፡፡

ያለፈውን ዓመት ብቻ አሐዝ ብንወስድ፣ ወደ ፕላው ደሴት 90ሺህ ቱሪስት ገብቷል፡፡

ይህ አሐዝ ከፕላው ጠቅላላ ሕዝብ አምስት እጥፍ ይበልጣል ብንላችሁስ?

40 ከመቶ የአገሪቱ ጥቅል አገራዊ ምርት ገቢ በቱሪዝም የሚታለብ ነው፡፡

ይህ ግን ከኮቪድ በፊት ያለ ታሪክ ነው፡፡ ኮቪድ ድንበሯን ሲያዘጋት ፕላው ደሴት ጉሮሮዋ ተዘጋ፡፡

እንኳን ሌላው መዝናኛ ይቅርና የአገሪቱን ስም የያዘው ሆቴል ሳይቀር ተዘጋ፡፡

‹‹ለውድ ደንበኞቻችን፡- ኮቪድ የሚባል በሽታ በተቀረው ዓለም ስለተከሰተ ፕላው ሆቴል ለጊዜው ዝግ መሆናችንን ለውድ እንገልጻለን›› ብለው በር ላይ ሳይለጥፉ አልቀሩም፡፡

ፕላው አገር አንድም ዜጋ በቫይረሱ ባይያዝባትም ቫይረሱ ግን ቱሪዝማዊ ኢኮኖሚዋን ደም እያስተፋው ነው፡፡

2.ማርሻል ደሴቶች

4ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀው በማዕከላዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ መሀል፣ ከምድር ወገብ ሰሜን፣ ብጥስጥስ ብለው ከሚገኙት የእሳተ ገሞራ ደሴቶች ውስጥ የማርሻል ደሴቶች ይገኙበታል፡፡

በሀዋይ እና በፊሊፒንስ መሀል ነው የሚገኙት፡፡ በውስጣቸው 1200 ጥቃቅን ደሴቶችና የጎመራ ፍንጥቅጣቂ የሆኑ የሰመጡ ደቂቀ ደሴቶች (ኮራል አቶልስ) ይገኛሉ፡፡

ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የአሜሪካ የሩቅ ግዛት ሆነው የቆዩ ቢሆንም ከ1986 ወዲህ ራሳቸውን ችለዋል። ደህንነቱና መከላከያን እንዲሁም ጠቀም ያለ ድጎማን ግን አሁንም ከአሜሪካ ነው የሚያገኙት።

የሕዝብ ብዛት 55ሺህ ሲሆን ዋና ከተማቸው ማጁራ ትባላለች፡፡

እነዚህ ደቂቀ ደሴቶችና የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ስብስቦች ማርሻል ደሴቶች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ኮቪድ ምን እንደሆነ ባያውቁም ምጣኔ ሀብታዊ ቁንጥጫው ግን ፓሲፊክን አቋርጦ ተሰምቷቸዋል።

ታዲያ አንድ ፕላው በቱሪዝም በኩል አይደለም ቁንጥጫው፡፡ በዓሣ ማጥመድና መላክ ጥሩ ገንዘብ ያገኙ ነበር፡፡ ኮቪድ ይህንን አስተጓጎለባቸው፡፡

በኮቪድ ምክንያት 700 ሰዎች ሥራ አጥተዋል፡፡ ይህ ትንሽ ሕዝብ ላላት ማርሻል አይላንድስ ብዙ ቁጥር ነው፡፡

3. ቫኑዋቱ

የሕዝብ ብዛቷ 300ሺህ ቢሆን ነው፡፡ ዋና ከተማዋ ፖርትቪላ ይባላል፡፡ በ1ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ላይ የተሰፉ የሚመስሉ 80 ደሴቶች የፈጠሯት አገር ናት፡፡ ከፈረንሳይና እንግሊዝ ቅኝ ነጻ የወጣችው ገና በ1980 ነበር፡፡

አብዛኛው ሕዝቧ ገጠር የሚኖር ገበሬ ነው፡፡

የብዙ አገር ህዝቦች ድንበር ክፈቱልን ሥራ እንስራበት እያሉ ነው የሚያስቸግሩት፡፡ ቫኑዋቱ ብትሄዱ ግን በተቃራኒው ነው የምትሰሙት፡፡

ዶ/ር ሌን ታሪቮንዳ የኅብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር ናቸው፣ የቫኑዋቱ ደሴት፡፡ ዶ/ር ሌን የመጡባት ደሴት አምባኡ ደሴት ትባላለች፡፡ 10ሺ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡

‹‹እኔ የመጣሁበት ደሴት ሄዳችሁ ድንበሩ ይከፈት ወይ ብትሏቸው አረ እንዳታስጨርሱን ነው የሚሏችሁ›› ይላሉ ለቢቢሲ፡፡

መታመም አንፈልግም ነው የሚሉት፡፡ 80 ከመቶ የታሪቮንዳ አገር ሕዝብ ገጠር ነው የሚኖር፡፡ የኮቪድ ሕመም ብዙም አልተሰማቸውም፡፡ እርሻ እንጂ ቱሪዝም ላይ ስላልተንጠላጠሉ ሊሆን ይችላል፡፡

ዶር ሌን ድንበር ለመክፈት አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ጎረቤት ፓፓዎ ጊኒ ለወራት ከቫይረሱ ነጻ ሆና ቆይታ ሐምሌ ላይ እንዴት ጉድ እንደሆነች ሰምተዋል፡፡ ስለዚህ ድንበር መክፈቱ ይቆየን ብለዋል፡፡

4.ቶንጋ

ቶንጋን የፈጠሩት ደግሞ 170 ደቂቀ ደሴቶች ናቸው፡፡ እዚያው ደቡባዊ ፓስፊክ ነው የሚገኙት፡፡ ቶንጋ ደሴቶቿን ብትሰበስብ በስፋት ከጃፓን አታንስም፡፡

ለ165 አመታት ንጉሣዊ የፊውዳል አስተዳደር ነበራት፡፡ ከዚህ ፊውዳላዊ ሥርዓት የወጣችው በ2010 ዓ. ም ነበር፡፡ ጥብቅ ክርስቲያን አማኞች ያሏት ቶንጋ ከእንግሊዝ ነጻ የሆነችው በ1970 ዓ.ም ነበር፡፡

ቶንጋ ምን አይነት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሌላት አገር ተደርጋ ትታያለች፡፡ ማዕድን አልባም ናት ይባላል፡፡ ይህ ነው የሚባል የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ባይኖራትም በዓሣ ሀብት ራሷን ትደጉማለች፡፡ ሌላው የገቢ ምንጭ እርሻ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቶንጋዊያውን ከውጭ አገር የሚልኩት ገንዘብ ነው፡፡ ብዙዎቹ ቶንጋዊያን ያሉት በኒዊዚላንድ ነው፡፡ በአገሪቱ የሥራ አጥ ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡

ያም ሆኖ የውጭ ምንዛሬዋን የምታገኝበት አንዱ ቀዳዳ ቱሪዝም ስለነበር ኮቪድ ባይደርስባትም ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት አድርሶባታል፡፡

5.ሰሙዋ

በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኘው ሰሙዋ እስከ 1961 ዓ. ም ድረስ በኒውዚላንድ ሥር ነበር የምትተዳደረው፡፡

9 የእሳተ ገሞራ ደሴቶች ነው የፈጠሯት ይቺን አገር፡፡ ሆኖም 99 ከመቶ ሕዝቧ የሚኖረው በኡፖሉና ሳቫይ ደሴቶች ነው፡፡

ዋና ከተማዋ አፒያ ይባላል፡፡ ምጣኔ ሀብቷ በእርሻና በዓሣ ሀብት የተንጠለጠለ ነው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቱሪዝም ሞቅ ደመቅ ብሎላት ነበር፡፡ በተለይ ያማሩ የባሕር ዳርቻዎቿ ተወዳጅ ሆነውላታል፡፡

ከቱሪዝም ጋር የባሕር ማዶ ዓለም አቀፍ ኦፍሾር የባንክ አገልግሎት በማሳለጧ ሀብታሞች ሸሸግ ማድረግ የፈለጉትን ገንዘብ ይዘው እዚያ ይሄዳሉ፡፡ አንድም ለመዝናናት፣ አንድም ለባንክ አገልግሎት፡፡

200ሺህ የማይሞላው ሕዝቧ የወግ አጥባቂ ባህልና የጥብቅ ክርስትና ተከታይ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ዜጎቿ ወደ ኒውዚላንድና ሌሎች አገሮች እየተሰደዱ ገንዘብ ወደ ቤተሰብ ይልካሉ፡፡ ኮሮና በሌሎች አገሮች ያደረሰው ጉዳት ሕመሙ ተሰምቷል፣ ሩቅ በምትገኘው በሰሙዋ ደሴት፡፡

የቱና ዓሳ ከመኪና ላይ ሲወርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty

6.ቱቫሉ

ቱቫሉን የፈጠሩት 9 ደሴቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 5ቱ እሳተ ገሞራ ወልዶ፣ አሳብጦ፣ በድጋሚ አስምጦ ዳግም የወለዳቸው (ኮራል አቶልስ) ናቸው፡፡

የተቀሩት አራቱ ደግሞ ሕዝብ በደንብ ይኖርባቸዋል፡፡

ቱቫሉ በማዕከላዊ ፓስፊክ ውቅያኖስ ነው የምትገኘው፡፡ ፉናፉቲ ይባላል ዋና ከተማዋ፡፡

በቱቫሉ ተራራ አይታሰብም፡፡ ከባሕር ጠለል በላይ ከ4.5 ሜትር ከፍ ያለ ቦታ የለም፡፡ የአየር ንብረት በቱቫሉ ትልቁ ጉዳይ ቢሆን የማይገርመውም ለዚሁ ነው፡፡

የባሕር ጠለል ከፍታ ከምድረ ገጽ ከሚያጠፋቸው አገሮች አንዷ ቱቫሉ ነው የምትሆነው፡፡

በቱቫሉ ወንዝም ምንጭም ስለሌለ ኑሮ የዝናብ ጥገኛ ነው፡፡ የኮኮናት ተክል የአገሪቱ ገቢ ምንጭ ነው፡፡ ይህ ገቢ እንዲታወክ ምክንያት በመሆኑ ኮቪድ ቱቫሉ ባይገባም ገብቷል፡፡

7.

በዓለም ትንሽዋ አገር ናውሩ ናት፡፡ ይቺ ደሴት ስሟ በቅርብ ጊዜ ይነሳ የነበረው አውስትራሊያ አገሪቱን እንደ ጓሮ እየተጠቀመቻት ነው በሚል ነው፡፡ ናውሩ ስደተኞች ማጎርያ አለ፤ ንብረትነቱ የአውስትራሊያ የሆነ፡፡

ይሄ ማጎርያ ታዲያ ለናውሩ አንድ የገቢ ምንጭ መሆኑ ይገርማል፡፡ ናውሩዎች አንዱ ሥራ ቀጣሪ ኢንደስትሪያችሁ ምንድነው ቢባሉ የአውስታራሊያ የስደተኛ ካምፕ ብለው ሊመልሱ ይችላሉ፡፡

ከ2013 ጀምሮ አውስትራሊያ በጀልባ ወደ አገሯ ሊገቡ የሚሞክሩ ስደተኞችን በሙሉ ወደ ናውሩ ነው የምትወስዳቸው፡፡ ካልሆነም ፓፓው ኒው ጊኒ፡፡

ከአውስትራሊያ 3ሺህ ኪሎ ሜትር ርቃ በሰሜን ምሥራቅ ፓስፊክ አቅጣጫ የምትገኘው ናውሩ የዜጎቿ ብዛት 10 ሺህ ቢሆን ነው፡፡

ናውሩን የሚያኖራት እርዳታ ነው፡፡ ሌላው ብቸኛ ሀብቷ ፎስፌት ማዕድን ነው፡፡

በናውሩ የውጭ ጋዜጠኛ ሄዶ መዘገብ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በካምፖቹ ውስጥ ያለውን ኢሰብአዊ ድርጊት ያጋልጣል፡፡ ይህ ደግሞ ናውሩ የገቢ ምንጬን ሊጎዳብኝ ይችላል ትላለች፡፡

ናውሩን በዓመት የሚጎበኛት ሰው ከ200 አይበልጥም ይባላል፡፡ ቴሌግራፍ በአንድ ዘገባው በናውሩ እስከዛሬ የገባው ቱሪስት ቢደመር ከ15ሺህ አይበልጥም ሲል ጽፏል፡፡

በስፋት ቫቲካን ሲቲና ሞናኮ ብቻ ናቸው የሚበልጧት፤ ለዚህም ነው የዓለም ትንሽዋ ሪፐብሊክ ደሴት የምትባለው፡፡

ቱሪስት የአገሪቱ ገቢ ምንጭ አለመሆኑ በኮቪድ-19 አልተጎዳችም ማለት ግን አይደለም፡፡ ለጊዜው ከ10ሺህ ዜጎቼ አንድም ሰው ኮቪድ-19 አልያዘውም ብትልም ሕመሙ ግን ናውሩም ደርሷል፡፡

ኮሮና
Banner

8.ኪሪባ

ኪሪባቲ የብጥስጣሽ ደሴቶች አገር በመሆኗ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ 4ሺህ ኪሎ ሜትር፣ ከሰሜን ደቡብ ደግሞ 2ሺህ ኪሎ ሜትር ታስኬዳች፡፡ ይህ ማለት ግን ይህ ሁሉ ርቀት ሰው የሚኖርበት ደረቅ መሬት ነው ማለት አይደለም፡፡

ነጻነቷን ያገኘችው ከእንግሊዝ በ1979 ዓ.ም ነው፡፡ በ1960ዎቹ ይቺ አገር አንዳንድ ደሴቶቿ ለእንግሊዝ የኑክሌር መሞከሪያ ሆነው አገልግለዋል፡፡

እንደ ብዙዎቹ የፓስፊክ ደቂቀ ደሴቶች ሁሉ ኪሪባቲም የዓለም ሙቀት መጨመር ከምድረ ገጽ ሊያጠፋት እንደሚችል ይገመታል፡፡

ኪሪባቲ ከፊጂ ደሴት መሬት ተከራይታ ምግብ ታመርታለች፡፡ ኢኮኖሚዋ ደካማ ሲሆን ኮኮናትና ኮፕራ በመላክ ነው የምትታወቀው፡፡ የዓሣ ማጥመድ ፍቃድ ለውጭ ኩባንያዎች እየቸበቸበች ኢኮኖሚዋን በከፊል ትደጉማለች፡፡

9ኛ ሰለሞን ደሴቶች፤10ኛማይክሮኒዢያ

በዝርዝሩ 9ኛ እና 10ኛ ላይ ያሉት የሰለሞን ደሴቶች እና ማይክሮኒዢያ ናቸው፡፡ ሁለቱም አገራት በዓሣ ምርትና በቱሪዝም ይታወቃሉ፡፡ ሁሉም በኮቪድ-19 የተጠቃ ዜጋ የለባቸውም፡፡

ይህ ዝርዝር ታዲያ ሰሜን ኮሪያና ቱርከሜኒስታን አላካተተም፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁለት አገራት በይፋ ከኮቪድ-19 የያዘው ዜጋ አለም የለምም ብለው አያውቁም፡፡ ወይም አይታመኑ ይሆናል፡፡