ኮሮናቫይረስ ፡ በጀርመን የወረርሽኙን አደጋ ለማጥናት የሙዚቃ ድግሶች ተዘጋጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አካላዊ ርቀትን ጠብቁ፤ ሰው የሚሰባሰብበት ቦታ አትሂዱ፤ ከሄዳችሁም ጥንቃቄ አይለያችሁ በሚባልበት ጊዜ የጀርመን ተመራማሪዎች ግን በአንድ ቀን ሦስት የፖፕ ሙዚቃ ድግስ አሰናድተዋል።
ታዲያ በግድ የለሽነትና በማን አለብኝነት አይደለም።
ተመራማሪዎቹ ይህን ያደረጉት በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ቤት ውስጥ በሚከናወኑና በርካታ ሰዎች በሚሳተፉባቸው ዝግጅቶች የሚከሰተውን አደጋ ለማጥናት ነው።
በዚህ የሙዚቃ ድግስ ላይ ዕድሜያቸው በ18 እና 50 መካከል የሚገኙ ጤነኛ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል። የተሳታፊዎቹ ቁጥር ግን ከሚጠበቀው ሲሶ ነው።
በሃሌ ዩኒቨርሲቲ በሌፕዚንግ ከተማ የሚሰራው የዚህ ጥናት መሪ ዝግጅቱ በመሳካቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ድምፃዊው እና የሙዚቃ ግጥም ፀሐፊው ቲም ቤንድዝኮ በሦስቱም የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ሥራዎቹን ለማቅረብ ተስማምቷል።
'ሪስታርት-19' የሚል ስያሜ የተሰጠው የሙዚቃ ድግስ የተሰናዳው በወረርሽኙ ወቅት እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ሊከናወኑ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ለመመርመር መሆኑን አጥኝዎቹ ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዕለት ከተሰናዳው ሦስት የሙዚቃ ድግሶች የመጀመሪያው ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የነበሩ ዝግጅቶችን ለማስመሰል ያለመ ሲሆን በሥፍራው ምንም ዓይነት የጥንቃቄ መመሪያዎች አልተተገበሩበትም።
ሁለተኛው ደግሞ ንፅህና የተጠበቀበትና የተወሰነ አካላዊ ርቀት የተጠበቀበት እንዲሆን ተደርጓል።
ሦስተኛው ደግሞ አዳራሹ ከሚይዘው የሰው ቁጥር በግማሽ የተቀነሰ ሲሆን እያንዳንዱ ሰውም በ1.5 ሜትር ልዩነት ተራርቆ ነበር የታደመው።
ከዚህም ባሻገር ሁሉም ተሳታፊዎች በዝግጅቱ ላይ ከመሳተፋቸው በፊት የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እና አካላዊ ርቀት መጠበቃቸውን የሚከታተል መሳሪያም ተሰጥቷቸዋል።
ተመራማሪዎቹም ታዳሚዎቹ በብዛት የሚነካኳቸው የትኞቹን ቦታዎች እንደሆነ ለመከታተልም 'የሚታይ ፀረ ተህዋስ' መጠቀማቸው ተነግሯል።
"መረጃ የማሰባሰብ ሂደቱ በጥሩ መልኩ ሄዷል። ጥራት ያለው መረጃ አግኝተናል፤ ድባቡ ደስ የሚል ነበር፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግንና ፀረ ተህዋስ በመጠቀም ልምዱም ረክተናል" ብለዋል የጥናቱ መሪ ስቴፋን ሞርቲዝ።
ድምፃዊው ቲም ቤንዲዝኮም ዝግጅቱ ከምጠብቀው በላይ ነበር ብሏል። የጥናቱ ውጤት በድጋሜ በታዳሚዎች ፊት እውነተኛ ዝግጅቶችን ለማካሄድ እንደሚረዳ ድምፃዊው ተናግሯል።
የጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤትም መስከረም ወር ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የጥናት ፕሮጀክቱ የአደጋውን ደረጃ በመለየት በቤት ውስጥ የሚከናወኑ ዝግጅቶችን እንደገና ለመመለስ ይረዳል በሚልም ከዛክሰኒይ -አንሃልት እና ዛክሶኒይ ግዛቶች የ1.17 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አግኝቷል።
ዝግጅቱ ከመካሄዱ በፊት የዛክሰኒይ -አንሃልት የኢኮኖሚና ሳይንስ ሚኒስተር ፕሮፌሰር አርሚን ዊሊንግ ማን፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መሰል ዝግጅቶችን ማሰናከሉን ገልፀው፤ "የቫይረሱ ሥርጭት ስጋት ስላለ የሙዚቃ ድግሶች ፣ የንግድ ባዛሮችና ስፖርታዊ ዝግጅቶች መካሄድ አይችሉም፤ በመሆኑም ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች እና ቅንጅት ቢደረግ ይህንን አደጋ ሊቀንሱት እንደሚችሉ ለማወቅ ጥናቱ ጠቃሚ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የጥናቱ መነሻ በጀርመን ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡ ነው።
እንደ ሮበርት ኮች ተቋም መረጃ መሰረት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በአገሪቷ ከ2ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 232 ሺህ 82 አድርሶታል።












