ፍሬዲ ብሎም፡'የዓለማችን የእድሜ ባለፀጋ' ደቡብ አፍሪካዊ በ116 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዓለማችን በዕድሜ ትልቁ ሰው ይሆናሉ ተብለው የታሰቡት ደቡብ አፍሪካዊ በ116 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
እኝህ የእድሜ ባለፀጋ ፍሬዲ ብሎም፤ በምስራቅ ኬፕ ግዛት በጎርጎሮሳዊያኑ ግንቦት ወር 1904 እንደተወለዱ የግል መረጃቸው ያሳያሉ። ይህ ግን በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የተረጋገጠ አይደለም።
በጎርጎሮሳዊያኑ 1918 በተከሰተው በስፓኒሽ ጉንፋን ወረርሽኝ (የኅዳር በሽታ) ምክንያት በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ላይ እያሉ ጠቅላላ ቤተሰባቸውን አጡ።
የሚገርመው ከወረርሽኙ ያመለጡት ፍሬዲ፤ ለበርካቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት ሁለት የዓለም ጦርነቶችና እና ከአፓርታይድ ጭፍጨፋም ተርፈዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ረዥም እድሜ ለመቆየታቸው ሚስጥሩ ምንድን ነው ? ተብለው የተጠየቁት የዕድሜ ባለፀጋው ለቢቢሲ ሲናገሩ "ምንም የተለየ ሚስጥር የለውም" ብለዋል።
" አንድ ነገር ብቻ ነበር። ይህም ከፈጣሪ የተሰጠ ፀጋ ነው። ሁሉም ኃይል ያለው እሱ ነው። እኔ ምንም የለኝ። በማንኛውም ጊዜ ልሞት እችል ነበር፤ ግን እርሱ ጠበቀኝ" ብለዋል።
ፍሬዲ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ሰራተኛ ሆነው ነው። ታታሪና ጠንካራ ሰራተኛ ነበሩ። መጀመሪያ ላይ በእርሻው ዘርፍ ከዚያም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተቀላቅለዋል።
ጡረታ የወጡትም በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ እያሉ ነው።
ምንም እንኳን ከበርካታ ዓመታት በፊት ከመጠጥ ጋር ቢለያዩም መደበኛ አጫሽ ነበሩ።
ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የአገሪቷ መንግሥት የእንቅስቃሴ ገደብ ሲጥል ሲጋራ መግዛት ጭንቅ ሆኖባቸው ነበር።
በዚህ ጊዜም በ116ኛው ልደታቸው ጋዜጣ ጠቅልለው የራሳቸውን ሲጋራ ሰርተው አጭሰዋል።
ይህም ብቸኛው የሚያዝናናቸው ተግባር እንደሆነ የ86 ዓመቷ ባለቤታቸው ግንቦት ወር ላይ ለሰንደይ ታይምስ ተናግረው ነበር።
እኝህ የዕድሜ ባለፀጋ ቅዳሜ ዕለት በተፈጥሯዊ ምክንያት በኬፕ ታውን ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
"ከሁለት ሳምንት በፊት አያቴ እንጨት እየፈለጠ ነበር። በጣም ጠንካራ ሰው ነበር። ልበ ሙሉ ነበር።" ሲል አንድሬ ኔዶ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
"በቀናት ውስጥ ግን ያ ልበ ሙሉውና ጠንካራው ሰው በአንዴ ኩምሽሽ አለ" ይላል አንድሬ። ሕልፈታቸው ከዘመኑ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር እንደማይገናኝ ግን ቤተቦቻቸው ያምናሉ።












