እንግሊዝ፡ የተሳሳተ አስከሬን የተሰጣቸው ቤተሰቦች ሌላ ግለሰብ ቀበሩ

ኩምበርላንድ ሆስፒታል

ክስተቱ ያጋጠመው በእንግሊዟ ካርሊስል በምትባል ከተማ ነው።

ከሆስፒታል የተሰጣቸውን የቤተሰባቸውን አስከሬን በቀብር አስፈፃሚው ድርጅት መሰረት ይቀብራሉ።

የቀብሩ ስነ ስርዓት የተፈፀመውም ካርሊስል በሚባል መካነ መቃብር ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ቤተሰብ በተሰባሰበበት በባለፈው ወር ነው።

በኋላም ነው ቤተሰቡ የተሰጣቸው አስከሬን የተሳሳተ መሆኑንና ለሌላ ግለሰብ የቀብር ስነ ስርዓት አካሂደው መቅበራቸውን የተረዱት።

የተሳሳተ አስከሬን መቀበሩን በመጀመሪያ ይፋ ያደረገው ኒውስ ኤንድ ስታር የተባለ ጋዜጣ ሲሆን ፤ ቤተሰቡም ቆፍረው ለማውጣት ተገደዋል።

ስህተቱ ተፈፅሞበታል ተብሎ የሚታመነው ኩምበርላንድ የተባለው ሆስፒታል ስራ አስፈፃሚዎችም ምርመራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

የቀብር ስራ አስፈፃሚው ጆርጅ ሃድሰንና ልጆቹ ለጋዜጣው እንደተናገሩት "የሚያሳዝንና ከፍተኛ ስህተት ነው የተፈፀመው" ብለዋል።

ፈታኝ ወቅት

የቀብር አስፈፃሚው ቃለ አቀባይ እንደተናገሩት "የሌላ ሰው ግለሰብ አስከሬን እንደቀበርን አላወቅንም ነበር። ለቤተሰቦቻቸው ከልብ አዝነናል" ብለዋል።

ጆርጅ ሃድሰንና ልጆቹ ከ150 አመታት በላይ ቀብር በማስፈፀምም ስራ ተሰማርተው እንዳገለገሉና እንዲህ አይነት ስህተትም አጋጥሟቸው እንደማያውቅ አስረድተዋል።

ቢቢሲም ከቀብር አስፈፃሚዎቹ ተጨማሪ መሪጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በሰሜን ኩምብሪያ የሚገኘው የእንግሊዝ ጤና አገልግሎት ቢሮ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው የቀብር አስፈፃሚዎቹ እንዲህ አይነት ስህተት እንዴት እንደተፈፀመ የሚያደርጉት ምርመራን እንደሚደግፉና "ቤተሰባቸውን ላጡትና በፈታኝ ሁኔታም እያሉ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ነገር ለደረሰባቸውም ኃዘናችን ጥልቅ ነው" ብለዋል።

መስሪያ ቤቱም የራሱን የውስጥ ምርመራ እንደጀመረና ሲጠናቀቅም ስለተፈጠረው ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው በጥልቀት እንደሚያስረዱ ተገልጿል።