ቴክኖሎጂ፡ ቻይና ሰራሹ ቲክቶክ የትራምፕ እግድ ላይ ህጋዊ እርምጃን እንደሚወስድ አስታወቀ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ሰራሹ የተንቀሳቃሽ ምሥል መጋሪያ ቲክቶክ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እንዳይሰራ የጣሉትን እግድ እንደማይቀበለውና ህጋዊ እርምጃንም እወስዳለሁ ብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ከቲክቶክ ባለቤት ባይት ዳንስ ጋር የሚደረግ ማንኛውንም የንግድ ግብይትም ሆነ ስምምነት ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ተቀባይነት እንደሌለው ፍፁማዊ ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ቲክቶክም አሜሪካ ምድር ላይ እንዳይሰራ ውሳኔያቸውን አስተላልፈዋል።

የዋሽንግተን ባለስልጣናት ቲክቶክ የአሜሪካውያንን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ይሰጣል የሚል ስጋታቸውን ያሰማሉ።

ቲክቶክ በበኩሉ ለቻይና መንግሥት ምንም አይት መረጃ እንደማያቀብል እንዲሁም ቁጥጥር እንደማይደረግበት በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።

ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 80 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።

ለአመት ያህልም ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ልዩነቶችን ለመፍታት ቢሞክርም አስተዳደሩ "እውነታንና ተጨባጭ መረጃዎችን" መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ችግር ገጥሞኛል በማለት ኩባንያው ከሰሞኑ ገልጿል።

"የህግ የበላይነት ወደ ጎን እንዳይባልና፣ ኩባንያችንም ሆነ የደንበኞቻችን ተጠቃሚነት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲታይ የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ለመቃወም ወደ ፍርድ ቤት እናመራለን" በማለት የኩባንያው ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

ህጋዊ ሂደቱን በዚህ ሳምንት እንደሚጀምር ቲክቶክ ለቢቢሲ ቢዝነስ ሪፖርተን ቪቪየን ኑኒስ አሳውቋል።

በዚህ ሳምንት አርብ እንዲሁ ቻይናዊ አሜሪካውያን የሆኑ ግለሰቦች ትራምፕ ዊ ቻት የተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ላይ የጣሉትን እግድ ለመቃወም ሌላ ክስ ጀምረዋል። ዊ ቻት የቻይናው ኩባንያ ቴንስንት ንብረት ነው።

በወጣቶች በተለይም ከሃያ አመት በታች ባሉት ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ቲክቶክ ዳንስ፣ አለም አቀፍ ፖለቲካ ሌሎችንም ጉዳዮችን በተመለከተ አጠር ያለ ቪዲዮ የሚጋራበት መተግበሪያ ነው።

በተለይም በቅርብ ወራት ከፍተኛ የሆነ የዝና ጣራ ላይ የወጣ ሲሆን የመተግበሪያው ቪዲዮዎች በቢሊዮን በሚቆጠር ጊዜ ዳውንሎድ ተደርገዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ቻይና የፌደራል መንግሥት ሰራተኞችን መዋያ ቦታ ለማወቅ፣ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለማስፈራራትና በኩባንያዎችም ላይ ለመሰለል ቲክቶክን ትጠቀምበታለች በማለት ይወነጅላሉ።

በቻይና ኩባንያዎች የሚመረቱ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች መጨመርም "ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት እንዲሁም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ምጣኔ ኃብትን ላይ ጫና የሚያሳድር ነው "ብለዋል ትራምፕ

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ በቻይና ላይ የንግድ ጦርነት ሲያውጁ ስለነበር በቲክቶክና በዊቻት ላይ የጣሉት እገዳ ብዙ የሚያስገርም አልሆነም።

ቲክቶክን ያገደችው አሜሪካ ብቻ ሳትሆን ህንድም አግዳለች፣ አውስትራሊያም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ከጫፍ ላይ ናት።