''መድሀኒት አግኝቻለሁ'' የምትለው ማደጋስካር ቫይረሱን መቆጣጠር ለምን አቃታት?

የፎቶው ባለመብት, RIJASOLO
የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት አንድሬ ራሆሊና ምንም እንኳ ኮሮናቫይረስን የሚያድን መድሀኒት ተገኝቷል፤ ተጠቀሙት እያሉ ቢሆንም በማደጋስካር የሚገኙ ሆስፒታሎች እየጨመረ የመጣውን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቋቋም አቅቷቸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ከእጽዋት የተሰራው 'መድሀኒት' ፈዋሽነቱ እና ደህንነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሰዎች እንዳይጠቀሙት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
በሕንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው ደሴቲቷ አገር ማደጋስካር ባለፈው ወር ብቻ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ የጨመረ ሲሆን፣ እስካሁን 13 ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። 162 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንዳጡ የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ፕሬዝዳንቱ ግን ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ ይፋ የተደረገውና 'ኮቪድ- ኦርጋኒክስ' ተብሎ የሚጠራውን የእጽዋት መድሃኒት ማሞካሸታቸውን ቀጥለዋል።
በማደጋስካር የተግባራዊ ሳይንስ ምርምር ኢንስቲትዩት 'አርትሚዝያ' ተብሎ ከሚጠራው ተክል የተሰራው 'መድሀኒት' በፈሳሽ መልክ የሚወሰድ ነው። ለመድሃኒቱ በዋነኛነት እንደ ግብአት የሚጠቅመው ተክል ደግሞ የወባ በሽታን ለማከም በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላል።
መጠጡ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱን ሰዎችን እንዳይዝ ለመከላከልና የተያዙትን ለማከም እንደሚረዳ በአገሪቱ በስፋት እየተነገረ ነው። ባለፉት አራት ወራት ደግሞ በትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች እንዲወስዱት ተደርጓል።
በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ 'መድሀኒቱን' በአደባባይ ወጥተው ሲያከፋፍሉ የነበረ ሲሆን በተጨማሪም ሩዝ፣ ዘይትና ስኳር በዋና ከተማዋ ለሚገኙ ድሃ የማህበረሰብ ዜጎች አከፋፍለዋል።
ነገር ግን ህዝብ እንዲሰበሰብ በማድረጋቸው ከበርካቶች ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው '' ወረርሽኙ ብዙም አይቆይም፤ ጊዜውን ጠብቆ ይጠፋል፤ እኛም እናሸንፈዋለን'' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም ከዋና ከተማዋ ውጪ በሚገኙ ገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች የቫይረሱ ስርጭት እስከዚህም ነው በማለት 'መድሀኒቱን' በነጻ ማከፋፈሉን እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጀት በበኩሉ በባህላዊ ህክምና በኩል እየተሰሩ ያሉት የፈጠራ ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆኑም ሳይንሳዊ ምርምር ሳይደረግ መጠቀም ላይ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስጠንቅቋል።
ባሳለፍነው ወር ደግሞ የጤና ሚኒስትሩ አህመድ አህመድ ዓለማቀፍ ድርጅቶችና አገራት እርዳታ እንዲያደርጉ ተማጽነው ነበር።
የማደጋስካር ዋና ከተማ የምትገኝበት የአናላማንጋ ግዛት ላይ ተጥሎ የነበረው የአምስት ሳምንታት የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱ ደግሞ በርካቶች ቫይረሱ ከነጭራሹ ሚሊየኖችን እንዲያጣቃ ዕድል እንደሚከፍት ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ግን በቴሌቪዥን መስኮት ባስተላለፉት መልዕክት የማደጋስካር ህዝቦች ከዚህ በላይ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን መቋቋም ስለማይችሉ ነው ገደቡን ለማላላት የተገደድነው ብለዋል።

















