ማዳጋስካር፡ ከአውሮፕላን ላይ የወደቀችው ተማሪ አላና ኩትላንድ አስክሬን ተገኘ

አላና ኩትላንድ

የፎቶው ባለመብት, Cutland family

የምስሉ መግለጫ, አላና ኩትላንድ በካምብሪጅ ሮቢንሰን ኮሌጅ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት እያጠናች ነበር

በማዳጋስካር ከአንድ አነስተኛ አውሮፕላን ላይ የወደቀችው የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ አስክሬን መገኘቱ ተገለፀ።

ከደቡብ ምስራቃዊ ክፍል ሚልተን ኬይኔስ የመጣችዋ የ19 ዓመቷ አላና ከትላንድ፤ ከአነስተኛ አውሮፕላኑ ላይ የወደቀችው ባሳለፍነው የአውሮፓዊያኑ ሐምሌ 25 ነበር።

የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሲኖላ ኖሜንጃሃሪይ እንደገለፁት የተማሪዋ አስክሬን ትናንት በአንድ ገጠራማ አካባቢ ተገኝቷል።

ከትላንድ በሮቢንሰን ኮሌጅ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቷን እየተከታተለች የነበረ ሲሆን በሞተችበት ወቅት በአፍሪካዊቷ ደሴት በሥራ ልምምድ ላይ ነበረች ተብሏል።

ከትላንድ ከአውሮፕላኑ ላይ የመውደቅ አደጋ ያጋጠማት የአውሮፕላኑን በር በመክፈቷ እንደነበር ፖሊስ የገለፀ ሲሆን ያንን ያደረገችበት ምክንያት ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ትወስደው የነበረው የወባ መድሃኒት የፈጠረባት ስሜት ለፈፀመችው ድርጊት ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ቢገመትም ጉዳዩ ግን አሁንም እየተጣራ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኮሎኔል ዲ ይ ላ ፔክስ እንደተናገሩት ከሆነ ተማሪዋ እየሰራችው በነበረው ጥናት ስጋት እንዳደረባትና ደስተኛ እንዳልነበረች ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት ማዳጋስካር በደረሰች በቀናት ውስጥ የጀመረችው ፕሮጀክት እየተሳካ እንዳልሆነ ተናግራ ጉዳዩን ለመቋጨት ያሰበች ትመስል ነበር ብለዋል።

ተማሪ ከትላንድ ማዳጋስካር በገባች በሁለተኛ ቀኗ በሥራዋ ክትትል የሚያደርጉላትን ግለሰብ (ሱፐርቫይዘር) በትንሹ ሁለት ጊዜ እንዳገኘቻቸው ኮሎኔል አክለዋል።

ባለፈው ሳምንት ከውጭ ጉዳይ ቢሮ በኩል በወጣው መግለጫ የተማሪዋ ቤተሰቦች ተስፋ ባላት እና ጠንካራ በሆነችው ልጃቸው ሞት ክፉኛ ልባቸው በሀዘን እንደተሰበረ ገልፀዋል።

"ሁል ጊዜ መልካምና ቤተሰቦቿን መርዳት የምትወድ ፣ በሕይወቷ ከብዙ ሰዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝትና መግባባት የነበራት ነበረች፤ ሁልጊዜም ትናፍቀናለች። " ሲሉ ቤተሰቦቿ ሀዘናቸውን ገልፀዋል።

ትምህርቷን ስትከታተልበት ከነበረው ሮቢንሰን ኮሌጅ ዴቪድ ውድማን በበኩላቸው "በአላን ሞት በጣም ነው የደነገጥነው" ብለዋል።

በኮሌጁ ውስጥ በነበራት የሁለት ዓመታት ቆይታም በተለያየ መልኩ ለኮሌጁ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ስታበረክት እንደነበር በመግለፅ " ሁላችንም እንናፍቃታለን " ሲሉ ጥልቅ ሀዘናቸውን ገልፀዋል።