ስደት፡ ወደ ጂቡቲ በመመለስ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሞታቸው ተሰማ

ሰደተኞች

የፎቶው ባለመብት, IOM

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ኢትዮጵያዊያን ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ባሕር ላይ አደጋ ደርሶባት ስምነቱ ሲሞቱ በርካቶች የደረሱበት አለመታወቁን ገለጸ።

በጅቡቲ ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ አደጋው በደረሰባት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም ስምንት ስደተኞች ሲሞቱ 12ቱ ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን ድርጅቱ አመልክቷል።

በባሕር ላይ በደረሰው አደጋ ለሞት ከተዳረጉትና የደረሱበት ሳይታወቅ ከቀሩት ውጪ የ14 ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ የተቻለ ሲሆን፤ ሌሎቹንም ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው።

ለስደተኞቹ ሞት ምክንያት የሆነቸው ጀልባ ሰዎቹን አሳፍራ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት በግድ እንድትንቀሳቀስ ከተደረገች በኋላ አደጋው መከሰቱ ተገልጿል።

አደጋው የገጠማት ጀልባ ከሰላሳ በላይ ሰዎችን አሳፍራ እንደነበረ የተነገረው ሲሆን በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት የስደተኞቹ ድርጅት መግለጫ አመልክቷል።

በባሕር ላይ በደረሰው አደጋ ለሞት የተዳረጉትና የደረሱበት ያልታወቁት እነዚህ ስደተኞች ከየመን ወደ ጅቡቲ እየተመለሱ የነበሩ ናቸው ሲል መረጃው አክሎ ገልጿል።

የአካባቢው አገራት በሁለት ጎራ ተከፍለው በሚደግፉት ለዓመታት በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው የመን ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ለከባድ ችግር መጋለጣቸው በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው።

በባሕር ላይ ሳሉ በጀልባቸው ላይ አደጋ የደረሰባቸው ስደተኞችም የመን ውስጥ ካለው ጦርነት ለመሸሽ ወደ ጂቡቲ እየተመለሱ ያሉ ስደተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀር ተገምቷል።

ሳዑዲ አረቢያ የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር በሚል ከ14 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ከአገሯ ማስወጣቷ የተገለፀ ሲሆን እነዚህ ስደተኞች በየመን መንቀሳቀሻ አጥተው ይገኛሉ።