ስለላ፡ ኢራን ለአሜሪካዊው ቤተሰብ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ትክፈል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢራን እአአ 2007 ላይ አገሯ ውስጥ ለተሰወረው የቀድሞው የኤፍቢአይ አባል ቤተሰብ 1.45 ቢሊዮን ዶላር እንድትከፍል የአሜሪካ ፍርድ ቤት አዘዘ።
ሮበርት ሌቪንሰን ለተባለው ግለሰብ ባለቤትና ልጆች የሚሰጠው ይሰጥ ከተባለው ገንዘብ 1.35 ቢሊዮን ዶላር ለደረሰው ጉዳት እና 107 ሚሊዮን ዶላር ለእገታ ነው።
ግለሰቡ የት እንዳለ እንደማያውቅ የገለጸው የኢራን መንግሥት ስለ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የአሜሪካ ባለሥልጣኖችና የሮበርት ቤተሰቦች፤ ሮበርት በኢራን እጅ ሳለ እንደሞተ ያምናሉ።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ “ወደ ፍትሕ አንድ እርምጃ ነው። እስካሁን ኢራን ለድርጊቷ እርምጃ አልተወሰደባትም። ውሳኔው ሮበርትን ባይመልስልንም በቀጣይ ኢራን ሰዎችን ከማገት እንድትቆጠብ ይረዳል” ብለዋል።
ግለሰቡ ደብዛው የጠፋው 2007 ላይ ወደ ኢራኗ ደሴት ኪሽ ከተጓዘ በኋላ ነበር።
የአሜሪካ መንግሥት እንዳለው፤ ግለሰቡ ኢራን ውስጥ ለብዙ ድርጅቶች በግል መርማሪነት ይሠራ ነበር።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ከሆነ ግን ወደ ኢራን የሄደው ፍቃድ ያልተሰጠው የሲአይኤ ሥራ ይዞ ሲሆን፤ ደሴቷ ላይ አሜሪካዊውን የሕግ ተሳዳጅ ዳውድ ሻላሁዲን አግኝቷል።
ሮበርት በወቅቱ በቀጠናው ያለውን ሕገ ወጥ የሲጋራ ዝውውር እየመረመረ እንደሆነ እንደነገረውም ገልጿል። ከተገናኙ በኋላ በኢራን የጸጥታ ኃይሎች ተይዘዋል።
2011 ላይ ሮበርት የእስረኞች ልብስ አድርጎ የሚያሳይ ፎቶ ለቤተሰቡ ተልኳል። በወቅቱ ሂላሪ ክሊንተን “የታገተው በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነው” ብለው ነበር።
2019 ላይ ባለቤቱ ለአሜሪካ ምክር ቤት “ተትቷል፤ ተረስቷል፤ ትኩረት ተነፍጓል” ስትል ተናግራለች።
የዓመቱ መባቻ ላይ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ዌሪ፤ “ባለፉት 13 ዓመታት የሰበሰብነው መረጃ ሮበርት ታግቶ ሳለ መሞቱን ይጠቁማል” ሲሉ ለቤተሰቡ ተናግረዋል።
ኢራን ስለ ግለሰቡ ስላለበት ሁኔታ መረጃ እየፈለገች ቢሆንም፤ በሕይወት እንዳለ የሚጠቁም ነገር አለማግኘቷል ገልጻ ነበር።
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ “ኢራን የቀድሞ ኤፍቢአይ እና ዲኢኤ ልዑክን ከምድረ ገጽ አጥፍታለች። ወደ 13 ዓመታት ገደማ አግታ አሰቃይታዋለች። ኃላፊነቱን ግን አልወሰደችም። ባለቤቱና ልጆቹ ምን እንደገጠመው ሳያውቁ ለመኖር ተገደዋል። ይህ ድርጊት መወገዝ አለበት” ብለዋል።












