ሴቶች በሚያገኙት ትንንሽ ነገር ተይዘው መቆም የለባቸውም - ኡባ አደም የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, DIRE DAWA UNIVESITY FB
ስሜ ኡባ አደም ይባላል። በምዕራብ ሐረርጌ ዞን መቻራ ከተማ ነው ተወልጄ ያደግኩት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በመቻራ ከተማ ተምሬ ጨረስኩ።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በገለምሶ ከተማ ነው ያጠናቀቅሁት። 12ኛ ክፍል በከፍተኛ ውጤት ስለጨረስኩ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ፋክልቲ ተመደብኩ።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። ቢሆንም ግን ዩኒቨርስቲ ስመደብ በኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ትምህርት ዘርፍ ለመመደብ ፍላጎት ነበረኝ።
በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ዩኒቪርስቲዎች ብዛት ስምንት ብቻ ነበር። እኔም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ስምንተኛ ምርጫዬ ነበር ያደረግኩት።
ፍላጎቴ የነበረው ከአንድ እስከ ሦስተኛ የሞላኋቸው የትምህርት ዘፎችና ዩኒቨርስቲዎች እንዲደርሱኝ ነበር።
ነገር ግን እንደ ሃሳቤ ሳይሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፍላጎቴ ባልሆነ የትምህርት ክፍል ተመደብኩ። በዚህም ሳቢያ ትምህርቴን በደስተኝነት አልነበረም የምከታተለው ነበር።
የመጀመሪያ ዓመት የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ውጤቴ ዝቅተኛ ስለነበር ተምሬ እንደጨረስኩ ትምህርቴን ለጊዜው አቋርጬ (ዊዝድሮው ሞልቼ) ወደ ቤተሰቤ ተመልስኩ።
በቀጣይ ዓመት ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ያወጣውን የመግቢያ ፈተና ተፈትኜ ስላለፍኩ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ ትምህርቴን ተከታትዬ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያዝኩ።
ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከሕንድ አገር ሴንተራል ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሃይበር ዋትስ ነው የተመረቅኩት፣ ሦስተኛ ዲግሪዬንም እዚያው ሕንድ አገር በሃንድራ ዩኒቨርስቲ አጠናቅቄያለሁ።
ጉዞ ወደ አመራርነት
ሁለተኛ ዲግሪዬን ከጨረስኩ በኋላ በጅግጅጋ ከተማ ግብርና ቢሮ ውስጥ ኢፋ በሚባል ፕሮጀክት ሪጂናል አካውንታንት ሆኜ እየሰራሁ ነበር።
ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በ1999 ዓ.ም ሰዎችን እየፈለገ ነበርና የዩኒቨርስቲው ቦርድ ወደ ዩኒቨርስቲው እንድገባ ጥያቄ አቅርቦልኝ ተቀላቀልኩ።
በዩኒቨርስቲ ውስጥም የአድሚኒስትሬሽን ዴቬሎፕመንት ምክትል ፕሬዝዳንት እና መምህርት ሆኜ ሥራ ጀመርኩ።
ሦስተኛ ዲግሪዬን እየተማርኩ የመመረቂያ ጽሁፌን አስገብቼ ወደ ድሬዳዋ ተመልሼ መጣሁ።
በወቅቱ የእኛ ትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዲግሪ ማስተማር ስለጀመረ እዚያው ሥራ ቀጠልኩ።
በ2010 ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ እየሰራሁ ሳለ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን ቦታን ለመያዝ ተወዳድሬ ስለተሳካልኝ ኃላፊነቱን ተረከብኩኝ።
በምክትልነትም አንድ ዓመት ከስድስት ወር በቦታው ላይ አገልግያለሁ።
ከዚያ በመቀጠል በዩኒቨርስቲው ውስጥ በነበረው ችግር ምክንያት በፕሬዝዳንቱ እና ሌሎች የዩኒቨርስቲ አስተዳደሮች ላይ በተወሰደው እርምጃ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆኜ ለስምንት ወራት ያህል ሰርቻለሁ።
ቦታው ክፍት ስለነበር በወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሬ በፕሬዝዳንትነቱ ቦታ ላይ ተሾምኩ።
ሌላኛው ጉዳይ ፕሬዝዳንት እንድሆን ምክንያት የሆነኝ፣ አምና የተፈጠረው ችግር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ብዙ ዓመት ስላገለገልኩ እና ዩኒቨርስቲውን የመቀየር ፍላጎት ስለነበረኝ ነው።
ውድድሩን ማሸነፌን ስሰማም በጣም ነው ደስ ያለኝ።
እኔ ወደ ዩኒቨርስቲው አመራርነት ስመጣ ዩኒቨርስቲው ትልቅ ችግር ውስጥ ነበር። ይህንንም ችግር ለማስተካከል ትልቅ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብን ነበር።
በዚያን ጊዜ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር። ይህንንም ችግር ለመፍታት ከእኔ ጋር ያሉ አመራሮች እና ከዩኒቨርስቲው ማህኅበረሰብ ጋር አብረን በመሆን ትልቅ ሥራ እየሰራን ነበር።
እናም ባከናወነው ጥሩ ሥራ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው ተመልሰው ነበር።
ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሸኝ ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ጋር ተመልሰዋል።
አሁንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመጣ በኋላ ተማሪዎቻችን ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ትልቅ ሥራ በመስራት ላይ እንገኛለን።
የቤተሰብ ኃላፊነት እና ዩኒቨርስቲ
የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ብሆንም የሦስት ልጆች እናትም ነኝ። ልጆቼ ስላደጉ ያን ያህል አልቸገርም። ቤት ውስጥ ባል ሚስቱን የሚያግዝ ቢሆንም ሚስትን የሚጠብቁ ብዙ ሥራዎች ይኖራሉ።
ሁልጊዜም ደግሞ ቤት ውስጥ ስለማልቸገር የቤት ውስጥ ኃላፊነትና የቢሮ ሥራን እያመጣጠንኩ እሰራለሁ።
ቤት ውስጥ ሁሉም ሥራ እንደ እናት አይሰራም። "ቢሮ ውስጥም ኃላፊ ሲኮንም ሁሉም ሥራ እንደ ራስ ላይሰራ ይችላል" ስለዚህ በሁለቱም በኩል ያለውን ኃላፊነት ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴቶች በአመራርነት በርከት ብለው አይታዩም። ለዚህም ደግሞ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
በተለያዩ መስኮች ውስጥ ሴቶችን የሚገጥሙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ተጋፍጦ በማለፍ ስኬታማ ከመሆን በተጨማሪ ለሌሎችም በር መክፈት ይቻላል። ፈተናዎችን በመሸሽ ስኬት ስለማይገኝ፤ ኃላፊነት ሳንሸሽ ካሰብነው ለመድረስ መጣር አለብን እላለሁ።
ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከመምህርነት ባሻገር የሚኖረው የአመራርነት ሥራ ብዙ ኃላፊነቶችን መወጣት የሚጠይቅ ነው። በዚህ መስክ ላይ በአገራችን በርካታ ሴቶች ስለሌሉ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶች የበኩላቸውን ለማበርከት መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች መካከል የሴቶችን ብቃት በተመለከተ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችና እንቅፋቶችን በጽናት ለማለፍ እራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው። በዚህ ሂደትም ውስጥ በርትቶ የራስን ብቃት በማሳየት ተወዳዳሪና ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ማሳየት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።
የወደፊት እቅድ
እኔ በአሁኑ ሰዓት በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ነኝ። የወደፊት እቅዴም የተለያዩ የጥናት ሥራዎችን በማከናወን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ላይ መድረስ ነው።
ለረዥም ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆኜ የመስራት እቅድ የለኝም። ወደ መማር ማስተማሩ ሥራ ተመልሼ ጥናት እየሰራሁ መቀጠል እፈልጋለሁ።
የሴቶች ሥራ አደባባይ ወጥቶ እውቅና ባያገኝ እንኳን እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። በተጨማሪም ሴቶች በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሆነ ቦታ ላይ ሲደርሱ፤ ያ ያገኙት ነገር ይበቃኛል ብለው መቆም እንደሌለባቸውና ወደ ቀጣዩ ስኬታቸው መሻገር አለባቸው ብዬ አምናለሁ።
እኛ ሴቶች በርትተን ከሰራን ብዙውን የኅብረተሰቡን ችግሮች መፍታት እንችላለን። እኔ በበኩሌ ሴቶች ከወንዶች በላይ ይሰራሉ ብዬ አምናለሁ።
ሴቶች ባገኙት ትንንሽ ነገሮች ይበቃናል ብለው ትልቅ ነገር ከማቀድና ከመስራት ራሳቸውን መቆጠብ የለባቸውም።
የቤት ውስጥ ኃላፊነትና የቢሮ ኃላፊነትን ጎን ለጎን በማስኬድ ካቀድነው ቦታ መድረስ ስለምንችል በትንንሽ ስኬቶች በቃን ብለን መቆም የለብንም።














