የእስልምና ሃይማኖት መሪው ይሞታሉ ያሉት ፓስተር ጥቃት ደረሰባቸው

የፎቶው ባለመብት, Glorious Word Power Ministries/Facebook
በጋናዋ መዲና አክራ የሚገኙ ፓስተር የሃገሪቱ ዋና ኢማም በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ይሞታሉ ብለው በመተንበያቸው አገልግሎት የሚሰጡበት ቤተ አምልኮ በወጣት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጥቃት ደረሰበት።
ለአምልኮ አገልግሎት የሚውሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ መስኮቶችና ወንበሮች እንዳልነበሩ ሆነዋል ይላል ከወደ አክራ የተሰማው ዜና።
ይሞታሉ ተብለው ትንቢት የተነገረባቸው ዋና ኢማም ኑሁ ሻራቡቱ ግን ጥቃት አድራሾቹን ተቃውመዋል። የተፈጸመው ተግባርም ትክክል አይደለም ሲሉ ሙስሊም ወጣቶቹን አውግዘዋል።
በአፍሪካ የሚገኙ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎች ብዙ ጊዜ ከታላላቅ ክስተቶች እስከ የሃገር መሪዎች ሞት ድረስ ትንበያ ሲሰጡ ይስተዋላሉ።
በፈረንጆቹ 2015 በናይጄሪያ ታዋቂ የሆነው የሃይማኖት መሪ ቲቢ ጆሽዋ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ በሂላሪ ክሊንተን ይሸነፋሉ ብለው ተንብየው ነበር። ትንበያቸው ሳይሰምር ሲቀር በፌስቡክ ገጻቸው ተላልፎ የነበረውን መልእክት ወዲያው እንዲጠፋ ተደርጓል።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ዋዜማ ዕለት በተላለፈው የትንቢት ንግግር ፓስተር ኦዉሱ ቤምፓ 19 ዋና ዋና ክስተቶችን የጠቀሱ ሲሆን፤ የኢማሙ ሞት ደግሞ ከእነዚህ መካከል ይገኝበታል። ይህንን የሰሙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ፓስተሩ ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢወተውቱም አሻፈረኝ ብለው ነበር።
ቆንጨራ ይዘው ወደ ቤተ አምልኮው የገቡት ወጣቶች ጥቃቱን በፌስቡክ ቀጥታ ስርጭት አስተላልፈውታል።
ይህንን የተመለከቱት ዋና ኢማም ኑሁ ሻራቡቱም ፓስተሩ ተሳስተዋልና ይቅር በሏቸው የሚል መልእክታቸውን ለተከታዮቻቸው አስተላልፈው ነበር።












