13 አስደናቂ የፓስፖርት እውነታዎች

ፓስፖርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፓስፖርት ለሰዎች እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆነ የጉዞ ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ ስለተጓዦች ማንነት ዝርዝር መረጃን የያዘ ሲሆን ሃገራት ባለፓስፖርቶቹ ወደ ድንበራቸው እንዲገቡ መፍቀዳቸውን የሚገልጹበትም ነው።

በዓለም ላይ ያሉ ሃገራት የየራሳቸው የሆኑ የተለያየ አይነት ፓስፖርቶችን ለዜጎቻቸው ይሰጣሉ። ከእንዚህ ፓስፖርቶች ጋር በተያያዘ አስደናቂ እውነታዎችን እነሆ. . .

1. ለየት ያለ ምስል በፓስፖርት ላይ

የስካንዴኔቪያን ሃገራትን ፓስፖርቶች በመመርመሪያ ብርሃን ውስጥ ስንመለከታቸው የአካባቢው መለያ የሆነው አንጸባራቂ የሠሜናዊ ብርሃን ምስል በገጾቹ ላይ ይታያል።

በስካንዴኔቪያን ፓስፖርቶች ላይ የሚታየው ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በስካንዴኔቪያን ፓስፖርቶች ላይ የሚታየው ምስል

2. የመጀመሪያው ፓስፖርት መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል

በመጽሃፈ ነህሚያ ላይ የፋርሱ ንጉስ አርጤቅስ በጁዲያ ግዛት በኩል ለሚያልፍ ባለስልጣን ያለችግር እንዲጓዝ የሚፈቅድ የይለፍ ደብዳቤን ሰጥቶ ነበር። ይህም መጀመሪያው ፓስፖርት እንደሆነ ይታመናል።

3. ፓስፖርቶች ፎቶግራፎችን ብቻ የያዙ ነበሩ

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መጀመርን ተከትሎ አንድ ለጀርመን የሚሰራ ሰላይ በሃሰተኛ የአሜሪካ ፓስፖርት ወደ ብሪታኒያ ከገባ በኋላ ፓስፖርቶች ፎቶግራፍ ብቻ እንዲኖራቸው ተደረገ።

4. ክብደት ከጨመሩ ወይም ከቀነሱ ፓስፖርት ይቀይራሉ

አሜሪካ ውስጥ ክብደት ከጨመሩ ወይም ከቀነሱ፣ ፊትዎ ላይ ቀዶ ጥገና ካደረጉ፣ ከተነቀሱ ወይም ንቅሳት ካስወገዱ እንዲሁም ለጌጥ የሚሆኑ ቀዳዳዎችን ካስበጁ በአዲሱ ገጽታዎ መሰረት ፓስፖርትዎን ማሳደስ ይኖርብዎታል።

5. ቤተሰብ ፎቶ ለፓስፖርት ተቀባይነት ነበረው

ፎቶግራፍ ፓስፖርት ለማግኘት አስፈላጊ በሆነበት የመጀመሪያ ጊዜያት የፈለጉትን አይነት ፎቶ ማቅረብ ይችሉ ነበር። ከቤተሰብዎ ጋር የተነሱትንም ፎቶ ቢሆን ተቀባይነት ነበረው።

ፓስፖርት ላይ ያለ የቪዛ ማህተም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው ከማብቃቱ ከወራት በፊት መታደስ አለበት

6. የፓስፖርትየአገልግሎት ጊዜ የሚያበቃው መቼ ነው?

ጉዞ ለማድረግ ሲያስቡ ፓስፖርትዎ አገልግሎት የሚያበቃው ቢያንስ ስድስት ወር እንዳለው ያረጋግጡ።

አብዛኞቹ የአውሮፓ ሃገራትን ጨምሮ አንዳንድ ሃገራት ተጓዦች ወደ ድንበራቸው ከሚገቡበት ቀን አንስቶ ፓስፖርታቸው ለሦስት ወራት የሚያገለግል መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ።

ነገር ግን ተጓዦች አስተማማኝና በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ከስድስት ወር በላይ እንዲሆን ይመከራል። ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሩሲያ፣ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎች ሃገራትም የተጓዦች ፓስፖርት የስድስት ወራት የአገልግሎት ጊዜ እንዲኖረው ይጠይቃሉ።

ይህም የሆነው ተጓዦች በጉዞ ላይ እንዳሉ የፓስፖርታቸው የአገልግሎት ጊዜ አብቅቶ ወደ መጡበት ለመመለስ ችግር እንዳይገጥማቸው ለማድረግ ነው።

7. በኩዊንስላንድ በኩል ወደ አውስትራሊያ ለሚገቡ ፓስፖርት አያስፈልግም

ይህ የተፈቀደው ግን ከአውስትራሊያ አቅራቢያ ከምትገኘው የፓፓዋ ኒው ጊኒ ደሴት ውስጥ ያሉና ተለይተው ከተጠቀሱ ዘጠኝ መንደሮች ለመጡ ነዋሪዎች ብቻ ነው።

ለዚህም ምክንያቱ ፓፓዋ ኒው ጊኒ ነጻነቷን ስታገኝ ከአውስትራሊያ ጋር በደረሰችው ልዩ ስምምነት መሰረት የአካባቢው ነዋሪዎች ያለፓስፖርት እንዲገቡ ስለተፈቀደ ነው።

8. ቫቲካን የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪ የላትም

ቫቲካን ምንም አይነት የኢሚግሬሽን ቁጥጥር ባይኖራትም፤ ጳጳሱ የቫቲካን ቁጥር አንድ ፓስፖርት ነው ያላቸው።

የአሜሪካ ፓስፖርትና የጉዞ ትኬት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሁሉም አሜሪካዊያን ፓስፖርት የላቸውም

9. በርካታ አሜሪካዊያን ፓስፖርት የላቸውም

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዳለው ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ዜጎች ከግማሽ ያነሱት ናቸው ፓስፖርት ያላቸው።

10. ቶንጋ ፓስፖርቶች ትሸጥ ነበር

170 የደቡባዊ ፓሲፊክ ደሴቶችን የምትይዘው ቶንጋ የተባለችው ሃገር ለአንድ ፓስፖርት 20 ሺህ ዶላር እያስከፈለች ትሸጥ ነበር።

ሟቹ የፖሊኔዢያ ሉአላዊ ግዛት ንጉሥ ቱፋሁ ቱፑ የሃገራቸውን ገቢ ለማሳደግ ሲሉ የግዛቲቱ ዜጎች ላልሆኑ ሰዎች ጭምር የቶንጋን ፓስፖርት ይሸጡ እንደነበረ ይነገራል።

11. የሚንቀሳቀሱ የሚመስሉ ምስሎች ፓስፖርት ላይ

በጉዞ ላይ እያሉ መሰላቸት ቢገጥምዎ የስሎቬኒያና የፊንላንድ ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች ፓስፖርታቸውን በመጠቀም ዘና የማለት ዕድል አላቸው።

የፓስፖርቶቹን ገጾች ወደፊት በፍጥነት እንዲገለጡ ሲያደርጉ በፓስፖርቱ ገጾች የግርጌ ጠርዝ ላይ ያሉት ምስሎች ሲንቀሳቀሱ መመልከት ይችላሉ።

ይህን መጫወቻ የሚመስል ተንቀሳቃሽ ምስል አላቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ይህን መጫወቻ የሚመስል ተንቀሳቃሽ ምስል አላቸው

12. በሃሰተኛ መንገድ ለመስራት አስቸጋሪው ፓስፖርት

የኒካራጓ ፓስፖርት 89 የተለያዩ አይነት አስመስሎ መስራትን ለመከላከል የሚያስችሉ የደህንነት ገጽታዎች አሉት። እነዚህም በግልጽ የሚታዩና በስውር የሰፈሩ ናቸው።

በዚህም ምክንያት የኒካራጓ ፓስፖርት በዓለም ላይ ካሉ ፓስፖርቶች ሁሉ ሀሰተኛ ለመስራት አስቸጋሪው እንደሆነ ተነግሯል።

13. ንግሥቲቱ ፓስፖርት የላቸውም

የዩናይትድ ኪንግደሟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ለዜጎቻቸው ፓስፖርትን የሚሰጡ በመሆናቸው ፓስፖርት መያዝ አያስፈልጋቸውም ይላሉ አንዳንዶች።

ነገር ግን ንግሥቲቱ ምስጢራዊ ሰነዶች አሏቸው። እነዚህ ሰነዶችም የሚገኙትና የሚዘዋወሩት በንግሥቲቱ መልዕክተኞች እጅ ነው። እነዚህ የጉዞ ሰነዶችም 15 እንደሆኑ ይነገራል።