በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሐሙስ ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጠመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትናንት ሐሙስ ምሽት ርዕደ መሬት መከሰቱን ባለሙያና ነዋሪዎች ገለጹ።
የመሬት መንቀጥቀጡ ያጋጠመው በሃረማያ፣ በድሬዳዋና ሐረር ከተሞች እንዲሁም በአቅራቢያቸው በሚገኙ አካባቢዎች እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ አነስተኛ መጠን እንዳለውና በርዕደ መሬት መለኪያ ሦስት እንደተመዘገበ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ፣ አስትሮኖሚና የህዋ ምርምር ዳይሬክተር እንዲሁም የርዕደ መሬት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ርዕደ መሬቱ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች የነበሩ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለጥቂት ሰከንዶች የቆየው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ሐሙስ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ላይ እንደተከሰተ ገልጸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ባጋጠመበት ጊዜ በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የነበረ አንድ ተማሪ ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት ጊዜ ተማሪዎች ከነበሩባቸው ህንጻዎች ተሯሩጠው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጨምሮም በመሬት መንቀጥቀጡም ሆነ ተማሪዎች ከህንጻዎች ለመውጣት በሚሯሯጡበት ጊዜ "ከድንጋጤ በስተቀር የደረሰ አደጋ ወይም ጉዳት የለም" ብሏል።
"እንቅጥቃጤው በተከሰተባቸው ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ህጻው ወደ ግራና ቀኝ የሚወዛወዝ ወይም የሚነቃነቅ ይመስል ነበር። እንዲሁም ከባድ ድምፅ ይሰማ ነበር" ሲል ተናግሯል።
ርዕደ መሬቱ ከተከሰተባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው ሐረር ነዋሪ የሆነው አብዱራህማን በበኩሉ "ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲፈጠር ቤታችን ላይ አንዳች ነገር የወረደ ያህል ነበር የተሰማኝ፤ ነገር ግን ወደ ውጪ በመውጣት ስመለከት ግን ምንም ነገር አልነበረም" ብሏል።
የርዕደ መሬት ተመራማሪው ፕሮፌሰር አታላይ አየለ እንደሚሉት "ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በዋናነት የተከሰተው ኤጀርሳ ጎሮ በምትባለው ቦታ ሲሆን ስፍራው ለሃረማያና ለድሬዳዋ የሚቀርብ ነው።"
ሐሙስ ምሽት ያጋጠመው ቀላል የመሬት መንቀጥቀጥ የፈጠረው ንዝረት እስከ ሐረር ከተማ እንደተሰማ ማረጋገጣቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር አታላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጨምረውም ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል 3 ደረጃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን መጠኑም አነስተኛ ከሚባሉት የሚመደብ በመሆኑ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት እንደሌለ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ለሁለት በሚከፍለው የስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች ላይና ከፍታማ ስፍራዎች ላይ እንዲህ አይነቱ ርዕደ መሬት መከሰቱ የሚጠበቅ እንደሆነ ፕሮፌሰር አታላይ ተናግረዋል።
ርዕደ መሬቱ የተከሰተበት "ይህ ቦታ በስምጥ ሸለቆ ጫፍ ላይ የሚገኝ ስለሆነ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ በፊትም በአካባቢው ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ ያውቃል" ብለዋል።
እንዲህ አይነቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው ግን አፋር ውስጥ በሚገኘው ሰመራ አካባቢ 'አይሻ ብሎክ' በሚባለው ቦታ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመሬት መንቀጥቀጦች መጠንና የሚከሰቱባቸው ጊዜያት በትክክል ቀድሞ ስለማይታወቅ በተለይ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ባሉ ቦታዎች የሚገነቡ ህንጻዎች አደጋውን በሚቋቋሙበት ሁኔታ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለባቸው ፕሮፌሰር አታላይ ይመከራሉ።












