“ኡጋንዳውያኑ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የምጽዓት ቀንን ሽሽት አይደለም” የኛንጋቶም ባለሥልጣን

ከኡጋንዳ ምሥራቃዊ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት የምፅዓትን ቀን ሽሽት ነው መባሉ ሐሰት መሆኑን የኛንጋቶም ወረዳ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።
በደቡብ ኦሞ ዞን፣ የኛንጋቶም ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሎኪኛኒጋ ሙርሌ፣ ኡጋንዳውያኑ በወረዳቸው እንደሚገኙ አረጋግጠው፣ “አመጣጣቸው አካባቢውን ለማየትና የቤተክርስቲያን መልዕክት ለማድረስ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንንም ከፌደራል ደኅንነት መሥሪያ ቤት ለመጡ አካላት ማስረዳታቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ሐሙስ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ኡጋንዳውያኑ “የምጽዓት ቀን በአካባቢያችን ይኖራል። ሞት መፈናቀል ይኖራል ብለው በመስጋት የገቡ መሆናቸውን” ተናግረዋል።
ኡጋንዳውያኑ ከምሥራቅ ኡጋንዳ በተለይም ሴራሬ፣ ኩሚ እና ጎራ ከተባሉ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
የቱርክ መንግሥት የዜና ወኪል አናዶሉ ከአንድ ወር በፊት፣ የኡጋንዳን ፖሊስ ጠቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን ዘግቦ ነበር።
ሃይማኖታዊ ተጓዦቹ የሚገኙበት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ፣ ዜጎቹ በቁጥር ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ 277 እንደሚደርሱ እና በቤተክርስቲያን የእንግዳ መቀበያ እና በግለሰቦች መኖሪያ አርፈው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኡጋንዳውያኑ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት የምጽዓትን ቀን ሽሽት ነው መባሉን ግን “የተሳሳተ መረጃ” ሲሉ አጣጥለውታል።
ከወረዳቸው ከዚህ ቀደም ባዘጋጁት ፌስቲቫል ላይ ከኬንያ ቱርካና፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኡጋንዳ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ተሳትፈው እንደነበር ያስታወሱት ምክትል አስተዳዳሪው፣ “እነርሱ የመጡት በታሪክም ኛንጋቶም ማኅበረሰብ ከኡጋንዳ ነው የመጣው ብለው ስለሚያምኑ አካባቢውን ለማየት ነው” ብለዋል።
አቶ ሎኪኛኒጋ ፍልሰተኞቹ ታኅሳስ ወር ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጸው፤ እንመለሳለን ከማለት ውጭ መቼ እንደሚመለሱ እንዳልገለጹላቸው ተናግረዋል።
“እነርሱ ሲመጡ ዝናብ አልነበረም። ዝናብ እስከሚዘንብ ድረስ ቆይተን ለእናንተ ዘር ሰጥተን ነው የምንሄደው እግዚአብሔር የነገረን መልዕክት ይህ ነው። ከዚያ በኋላ እንመለሳለን ነው ያሉት” ብለዋል።
በኢትዮጵያ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን፣ በድርቁ ሳቢያ በርካታ እንስሳት የሞቱ ሲሆን በሰዎችም ላይ ጉዳት ደርሷል።
አሁን ላይ ግን በአካባቢው ከፍተኛ ዝናብ እየዘነበ ቢሆንም ኡጋንዳውያኑ አሁንም በሥፍራው እንደሚገኙ ምክትል አስተዳዳሪው ጨምረው ተናግረዋል።
አናዶሉ በዘገባው የሃይማኖት ቡድኑ ተከታዮች የዓለም ፍፃሜ ኡጋንዳ ውስጥ ከሚኖሩበት አካባቢ ይጀምራል ብለው በማመን ከጥፋቱ ለመሸሽ እንደተሰደዱ ፖሊስ በምርመራዬ አረጋግጫለሁ ማለቱን አስነብቦ ነበር።
ተከታዮቹ በአካባቢያቸው ሞት እንደሚከሰት እና እዚያ አካባቢ የሚኖር ሰው በሙሉ እንደሚሞት በመሪዎቻቸው እንደተነገራቸውም ፖሊስ ጨምሮ ለዜና ወኪሉ ገልጿል።
ግለሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድም ለትራንስፖርት ሲሉ ንብረታቸውን እንደሸጡም ተነግሯል።
የኡጋንዳ ፖሊስ በበኩሉ መንደር በሚገኘው 'ክራይስት ዲሲፕልስ ቸርች' የሚባለው የሃይማኖት ቡድን ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንም አናዶሉ ዘግቧል።
በኡጋንዳ ለሰዎች ተገቢ ያልሆነ መረጃ በመንገር ለሞት የሚዳርጉ በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ።
እንደ አውሮፓውያኑ 2000 በደቡብ ምዕራብ ኡጋንዳ ካኑንጉ ዲስትሪክት ጆሴፍ ኪብዌቴሬ የተባለ የሃይማኖት ቡድን መሪ ለአማኞቹን ዓለም በቅርቡ ሊጠፋ እንደሆነና ንብረታቸውን እንዲሸጡ በመንገር ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ የቤተክርስቲያኑን በሩን ዘግቶ እሳት ለቆባቸዋል። በዚህም 700 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።












