የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መሪው የሩሲያ ደጋፊ ናቸው ስትል ዩክሬን ወቀሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን መርማሪዎች የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን መሪው የሩሲያ ደጋፊ ናቸው በማለት የኪዬቭ መኖሪያ ቤታቸውን በረበሩ።
ፓቬል ሌቤድ፤ ኪዬቭ-ፔቼርስክ የተሰኘው የዩክሬን ትልቁ ገዳም መሪ ናቸው። ገዳሙ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን (ዩኦሲ) ንብረት ሲሆን ቤተክርስቲያኒቱ የሞስኮው ቤተክርስትያን አካል ነበረች።
የዩክሬን መሪማሪዎች መሪው ብሔራዊና ኃይማኖታዊ ጥላቻን አነሳስተዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።
የዩክሬን ባለሥልጣናት መሪውና ተከታዮቻቸውን ከገዳሙ ለማስወጣት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
መሪው የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለው የዩክሬን ባለሥልጣናት መነኩሳትና የገዳሙ አባላትን የማስወጣት ሕጋዊ መብት የላቸውም ይላሉ።
ጉዳዩ “ፖለቲካዊ ነው” ያሉት ፓቬል፤ ቅዳሜ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበው “እኔ ከወራሪ ጎን ቆሜ አላውቅም” ቢሉም የሩሲያን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
“እኔ ወረራን እቃወማለሁ። አሁን ዩክሬን ነው ያለሁት። ይህ የኔም መሬት ነው” የሚሉት ፓቬል አሁን ያለበት ሁኔታ “የቁም እሥር” እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፈው አርብ በርካታ የኪይየየ-ፔቼርስክ ተከታዮች ገዳሙ ፊት ተሳብስበው ዩክሬን መነኩሳትን ለማባረር ማቀዷን ተቃውመዋል።
የዩክሬን ደኅንነት አገልግሎት ቴሌግራም በተሰኘው መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ መሪው “የዜጎችን እኩልነት ጥሰዋል” ሲል ወቅሷል።
መግለጫው እንደሚለው ፓቬል “በተደጋጋሚ የዩክሬናዊያንን ኃይማኖታዊ ስሜት ተሳድበዋል፤ ሌሎች እምነቶችን አንቋሸዋል፤ በሌሎች ላይ ጥላቻ ሰብከዋል።”
የደኅንነት አገልግሎቱ አክሎ መሪው “የወራሪውን ኃይል ተግባር ትክክል ነው ብለዋል አሊያም ወረራውን ክደዋል” ይላል።
መሥሪያ ቤቱ የገዳሙ መሪ የስልክ ልውውጥ ነው ያለውን የድምፅ ቅጂ ዩቲዩብ ላይ ለጥፏል።
አንድ የመሪው ነው በተባለ የወንድ ድምፅ በሚሰማበት ቅጂ ላይ “ይህ ጦርነት በሩሲያ ፌዴሬሽን እና አሜሪካ መካከል የሚካሄድ የመጨረሻው ዩክሬናዊ እስኪገደል ድረስ የሚቀጥል ነው” የሚል ድምፅ ይሰማል።
የሩሲያ ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ቫሲል ማሊዩክ “ጠላት የዩክሬን ማሕበረሰብን ለመከፋፈል ቤተክርስትያንን እየተጠቀመ ነው” ብለዋል።
መሥሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ንብረት የሆኑ ሕንፃዎችን መበርበሩና፤ የሩሲያ ደጋፊ ናቸው ያላቸውን 61 የኦርቶዶክስ ቀሳውስትን ማሠሩ ይታወሳል።
ፍርድ ቤት ሰባቱ ላይ እሥር ሲበይን ሁለቱ ከሩሲያ ጋር በተደረገ የእሥረኛ ልውውጥ ወደ ሞስኮው ተልከዋል።
የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፤ አባሎቼ ከሩሲያ ጋር ለመተባበራቸው ምንም ማስረጃ የለም ትላለች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ዩክሬናዊያን ገለልተኛ የሆነውን ‘ኦርቶዶክስ ቸርች ኦፍ ዩክሬን’ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ነገር ግን አሁንም ሚሊዮኖች ባለፈው ዓመት ከዘመናት በኋላ ከሞስኮው የተገነጠለው የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ተከታዮች ናቸው።
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በመወገን የሩሲያን ወረራ ደግፋለች።












