በርካታ የትራምፕ ደጋፊዎች ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ድጋፍ ለመግለጽ አደባባይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ያላቸው ድጋፍ ለመግለጽ አደባባይ ወጡ።
በፍሎሪዳ ግዛት ለትራምፕ ድጋፍ ለመግለጽ የወጡ ሰዎች ትራምፕ “ቀጣዩ ፕሬዝዳንታችን ይሆናሉ” የሚል መፈክር አሰምተዋል።
ደጋፊዎቹ ለትራምፕ አጋርነታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የወሲብ ፊልም ተዋናይቷን ዝም ለማሰኘት 130ሺህ ዶላር ከፍለዋል በሚል በወንጀል እንደሚከሰሱ በተገለጸበት ወቅት ነው።
አደባባይ የወጡት ደጋፊዎች ትራምፕ የቀረበባቸው ክስ በፖለቲካ ሕይወታቸው ላይ የሚያሳድረው ጫና የለም ከማለታቸው በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደውን 2024 ምርጫ ያሸንፋሉ የሚል እምነት አላቸው።
“ዳግም ፕሬዝዳንታችን ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። ገና በርካታ ሰዎች ሊደግፏቸው አደባባይ ይወጣሉ” ስትል ለቀድሞ ፕሬዝዳንት ድጋፍ ለመስጠት አደባባይ የወጣች ሴት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሜርሲ የተባለች ሴት ደግሞ ይህ "ምንም የሚለውጠው ነገር አይኖርም" ካለች በኋላ እንደውም ክሱ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለትራምፕ ኃይል ይሆናቸዋል ብላለች።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ አስተባባሪዎች የቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ ክስ እንደተመሰረተ ከተገለጸ በኋላ በነበሩት ሰዓታት ለምርጫ ቅስቀሳ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቋል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ባይደረግም፤ ስቶርሚ ዳንኤልስ ለተባለችው ሴት የ2016ቱ ምርጫ ከመደረጉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት 130ሺህ የአሜሪካ ዶላር መክፈላቸው ተገልጿል።
ትራምፕ ክፍያውን የፈጸሙት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት እየቀሩት ስለሆነ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እርምጃ የምርጫ ቅስቀሳ ጥሰት ጋር የሚስተካከል ነው በማለት የሚከራከሩ አሉ።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የቀድሞ የወሲብ ፊልም ተዋናይት በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየቀረበች ከትራምፕ ጋር እአአ 2006 ላይ ወሲብ መፈጸማቸውን ተናግራለች።
ትራምፕ ያሸነፉበት የ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለ ግንኙነታቸው ምንም እንዳትል በትራምፕ ጠበቃ ማይክል ኮሀን በኩል ከቀድሞ ፕሬዝዳንት 130ሺህ ዶላር መቀበሏን ዳንኤልስ ትናገራለች።
የትራምፕ ጠበቃም ገንዘቡን በትራምፕ ትዕዛዝ ለዳንኤልስ ከሰጡ በኋላ ገንዘቡ እንደተተካላቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ተናግረዋል።
የ76 ዓመቱ ትራምፕ በበኩላቸው 130ሺህ ዶላር መክፈላቸውን ቢያምኑም፤ ከዳንኤልስ ጋር የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት የለኝም እንዲሁም የምርጫ የፋይናንስ ሕጎችን አልጣስኩም በማለት ይከራከራሉ።
ትራምፕ ከነገ በስቲያ ማክሰኞ በኒው ዮርክ ተገኝተው እጃቸው ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ እንደ ማንኛው ወንጀለኛ የጣት አሻራቸው ተወስዶ በፖሊስ ፎቶ ግራፋቸው ከተነሳ በኋላ ፍድር ቤት ቀርበው የቀረቡባቸው ክሶች ይነበብላቸዋል።












