ሽንፈት ያስተናገዱት የሊቨርፑልና የቼልሲ አሠልጣኞች ጫና በረታባቸው

የቼልሲ እና ሊቨርፑል አሰልጣኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቼልሲ እና ሊቨርፑል አሰልጣኞች

ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 23/2015 ዓ.ም. በተካሄዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሽነፈት ያስተናገዱት የሊቨርፑል እና ቼልሲ አሰልጣኞች ጫና በርክቶባቸዋል።

የሊቨርፑል አሠልጣኝ የርገን ክሎፕ ቡድናቸው በማንቸስተር ሲቲ 4-1 መረታቱ “ፍፁም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

ባለፈው የውድድር ዘመን ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ሲገናኙ ማን ሊረታ እንደሚችል መገመት የሚያዳግትና እልህ አስጨራሽ የሆነ ፍልሚያ የሚታይበት ነበር።

ቅዳሜ ዕለት በኤቲሃድ ስታድየም ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ ግን ማንቸስተር ሲቲ የበላይነቱን ያሳየበት ሆኖ ተገኝቷል።

ምንም እንኳ ሊቨርፑል በ17ኛው ደቂቃ በሞ ሳላሕ አማካይነት የመጀመሪያዋን ጎል ቢያስቆጥርም አርጀንቲናዊው ሁሊያን አልቫሬዝ ከ10 ደቂቃ በኋላ ሲቲን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከእረፍት በኋላ ኬቪን ደ ብሩይነ፣ ኢካይ ጉንዶጋን እና ጃክ ግሪሊሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሲቲ ጨዋታውን በበላይነት አጠናቋል።

ማንቸስተር ሲቲ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከአርሰናል ጋር እየተፎካከረ ሲሆን ሊቨርፑል ደግሞ ከቻምፒዮንስ ሊግ ቀጣናው በ7 ነጥብ ርቆ ይገኛል።

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተከላካይ ሪዮ ፈርዲናንድ ጊዜው ለሊቨርፑል “አስጨናቂ” ነው ሲል ተደምጧል።

አለን ሺረር በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል “ተስፋ አልባ ሆነው ቀድሞ ከምናውቃቸው በተለይ በጣም ተዳክመው ነበር” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሊቨርፑልን በ2022/23 የውድድር ዘመን የቅዳሜውን ጨዋታ ጨምሮ በፕሪሚዬር ሊጉ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። ከዚህ መሃል ስምንቱ ከሜዳቸው ውጭ የቀመሱት ሽንፈት ነው።

ባለፈው የውድድር ዘመን በአራት የዋንጫ ውድድሮች እስከመጨረሻ ተፋልመው ፕሪሚዬር ሊጉን በሲቲ በአንድ ነጥብ ልዩነት ሲነጠቁ በቻምፒየንስ ሊግ ደግሞ በማድሪድ ተረትተው ዋንጫ ማጣታቸው ይታወሳል።

ክሎፕ እንደሚሉት ሊቨርፑል እያሳየ ያለው ደካማ አቋም በዚህ ዓመት የተደጋገመ ቢሆንም ማንቸስተር ዩናይትድን ከረቱ በኋላ ግን መንፈሳቸው ተነቃቅቶ ነበር።

አሠልጣኙ “ሁለት ተከታታይ ጎሎች በፍጥነት ማስተናገዳችን ሁሉን ነገር አበላሽቶታል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የተቆጠሩብን ጎሎችን ለመቀበል እጅግ አዳጋች ነው። እኛም አልተፋለምንም። እውነት ለመናገር ፍፁም ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

አክለው ተጨማሪ ጎል አለመሳተናገዳቸው "ዕድለኞች ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

የዩርገን ክሎፕ ቡድን በያዝነው የውድድር ዘመን ምንም ዓይነት ዋንጫ ካለማንሳቱም በላይ እስከ አራት የማጠናቀቅ ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው።

ማንቸስተር ሲቲ ያለ ኮከቡ አጥቂያቸው ኧርሊንግ ሃላንድ ገብተው ሊቨርፑልን አርበድብደው ወጥተዋል። አንድ ጎል ያስቆጠረው ግሪሊሽ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

የሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድናቸው ጎል ሲያስቆጥር በሊቨርፑል ተቀያሪ ተጫዋቾች ፊት መጨፈራቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ አንዳንድ ተንታኞች አስተያየት ቢሰጡም አሠልጣኙ ግን ይህን አጣጥለዋል።

ግራሃም ፖተር

ሌላኛው ጫና እየበረታባቸው ያሉት ግለሰብ የምዕራብ ለንዱን ቡድን ቼልሲ አሠልጣኝ ግራሃም ፖተር ናቸው።

ምንም እንኳ ቼልሲ ጎል ለማግኘት በርካታ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም ኳስን ከመረብ ማገናኘት ተስኖት አምሽቷል።

ከአስተን ቪላ ጋር በነበረው የቅዳሜ ምሽት ፍልሚያ ቼልሲ 27 ጊዜ የጎል ሙከራ አድርጎ፤ 69 በመቶ ኳስን ተቆጣጥሮ፤ 2-0 ተሸንፏል።

ቼልሲ ምንም እንኳ በስታምፈርድ ብሪጅ የኳስ የበላይነቱን ቢያሳይም በአስተን ቪል መረታቱን ተከትሎ ወደ 11ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። ቼልሲ በዚህ የውድድር ዘመን ያስቆጠረው 29 ጎል ከ12 የፕሪሚዬር ሊግ ተቀናቃኞቹ ያነሰ ሲሆን ወራጅ ቀጣና የሚገኙት ሊድስና ሌይስተር የተሻለ የጎል ክምችት አላቸው።

አዲሱ የቼልሲ ባለቤት አሜሪካዊው ቶድ ቦህሊ ክለቡን ለማጠናከር ከ550 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ቢያወጡም በክለቡ ጥሩ መሻሻል የለም ይህም በፖተር ላይ ጫና እያበረታባቸው ነው።

አንዳንድ ደጋፊዎች የቼልሲ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ ቅሬታቸውን በድምፅ ሲያሰሙ ‘ፖተር ይውጡ’ የሚል የማሕበራዊ ተጠቃሚም በርክቷል።

ቼልሲ በያዝነው የውድድር ዘመን በሜዳው አራት ጊዜ ሲሸነፍ በአራቱም ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር ተስኖቷል።

ሰማያዊዎቹ በቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከሪያል ማድሪድ ይፋለማሉ።

የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋች ሃስልቤይንክን ጨምሮ የተወሰኑ የእግር ኳስ ተንታተኞችና የቀድሞ ተጫዋቾች ቼልሲ አሠልጣኙን ማባረር የለበትም ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ አሠልጣኙ ይበቃቸዋል፤ መሰናበት አለባቸው የሚል አስተያየት ሲሰጡ ተስተውለዋል።