በሸገር ከተማ ቤቶችን በማፍረሱ ሂደት የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ወስደዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተካሄደ ባለው ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት ሂደት የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ መውሰዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የከተማው አስተዳደር ሕገ ወጥ ያላቸውን ቤቶች በሚያፈርስበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የተቃወሙና መንገድ የዘጉ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደደረሰባቸውና በዚህም የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ትናንት መጋቢት/ 22 ፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በአንዳንድ ቦታዎች የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳቱ ሂደት ለሁከት፣ ለእንግልት፣ ለአካልና ሥነልቦና ጉዳት እና ለእስር ምክንያት መሆኑንም ነው ኢሰመኮ የገለጸው።
ፊሎዶሮ በተባለ አካባቢም በነበረ ቤት የማፍረስ ሂደት የሰው ሕይወት ስለማለፉ መረጃ የደረሰው ሲሆን ክትትል እያደረገ እንደሆነም ጠቅሷል።
የከተማ አስተዳደሩ የሞተ ሰው እንደሌለ ጠቅሶ በተለምዶ ለቡ ተክለ ኃይማኖት እና መነ አብቹ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች የፈረሳ ሥራውን ለማደናቀፍ በሞከሩ ላይ የተወሰደ እርምጃ መኖሩን አመልክተዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች በቡድን ተደራጅተው በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሙከራ ያደረጉ አካላትን ለመቆጣጠር ፖሊስ በወሰደው እርምጃ መጠነኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሊኖሩ እንደሚችሉም ለኢሰመኮ ገልጿል።
አስተዳደሩ በጊዜያዊነት በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ሰዎች ቢኖሩም በአጭር ጊዜ ከእስር መለቃቀቸውን ቢያስረዱም ኢሰመኮ ይህንን መግለጫ እስካወጣበት ጊዜ የታሰሩ ሰዎች አሉ ብሏል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ስድስት ከተሞችን በማጣመር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 የወረዳ አስተዳደሮችን በማዋቀር በተመሠረተችው ሸገር ከተማ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት ጋር ተያይዞ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች ለኮሚሽኑ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
ኢሰመኮ አቤቱታውን ተከትሎ ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የሚመለከታቸውን የከተማ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት በማነጋገር እንዲሁም የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት የሚከናወንበትን ሂደት እንዲሁም ቀደም ሲል የፈረሱ ቤቶችን የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃ አጠናቅሯል።
ኢሰመኮ በዚህ የቤት ፈረሳ ሂደት ተገቢ ልየታ ያልተደረገበት ስለመሆኑ፣ ያለበቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ አድሎአዊ እርምጃ ስለመኖሩም በሪፖርቱ አካቷል።
ቤታችን ያለ አግባብ ፈርሷል የሚሉት ነዋሪዎች ከነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መስርተው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ በየአካባቢው ከሚገኙ መሰረታዊ አገልግሎቶች የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሁም ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ቤቶቻቸው ያለ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከሕግ አግባብ ውጭ ፈርሶብናል ሲሉም ለኢሰመኮ መናገራቸው ሰፍሯል።
የሸገር ከተማ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመስረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
ኃላፊዎቹ እየፈረሱ ስላሉ ቤቶች በሰጡት መረጃ የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ የተላለፈውን ውሳኔ መሰረት መደረጉን ነው።
ኢሰመኮ በለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሰበታ፣ ፉሪ እና ለቡ ተክለ ኃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ አካባቢዎች ባደረገው ምልከታ የቤት ማፍረሱ እና በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንዲሁም በቦታው ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ነው የተመለከተው።
የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀ የገለጸው ኢሰመኮ የታዩ ክፍተቶች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማስተካከያ እርምጃዎችንም ጠቅሷል።
ተገቢ ልየታን በተመለከተ
ኢሰመኮ በሪፖርቱ የቤት ፈረሳውና በግዳጅ ማንሳቱ እርምጃ ተገቢ ልየታ አልተደረገበትም ብሏል። የከተማው አስተዳደር የመንግሥትን ይዞታን በመውረርና ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ሕገወጥ የመሬት ግብይት የተገኙ ይዞታዎች ላይ የተደረጉ ግንባታዎችን ነው የተባለ ቢሆንም ሁሉም ቤቶች በተመሳሳይ ስሪት ላይ የተመሰረቱ አይደሉም ብሏል ኢሰመኮ።
ከ2005 ዓ.ም በፊት የተገነቡ ቤቶችን በተመለከተ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ መሰረት በኢመደበኛ መልኩ የተገነቡ ቤቶች የከተሞችን ፕላን እና የመሸንሸን ስታንዳርድ ሲያሟሉ ወደ መደበኛ ስሪት እንደሚዞሩ መደንገጉን አስታውሷል።
ነገር ግን ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት እነዚህ ቤቶች በሕጉ መሰረት ወደ መደበኛ ግንባታ እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን አረጋግጧል። ሆኖም የማዘዋወር ሥራ ሳይሰራም በአሁኑ ወቅት እንዲፈርሱ ተደርገዋል ብሏል ሪፖርቱ።
በሌላ በኩል እንዲፈርሱ የተደረጉ ነዋሪዎቹ የገዟቸው ቤቶችን በተመለከተ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ይገኙበታል ተብሏል።
ቤቶቹ ከከተማ ፕላን ጋር የማይሄዱ ናቸው ከተባለ በሕግ አግባብ በተደነገገው መሰረት ተለዋጭ የቤት መሥሪያ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው ሊነሱ ይገባ እንደነበርም ነው ኢሰመኮ ያስታወሰው። ቤቶቹ በገጠር መሬት ላይ የተሰሩ ናቸው ከተባለም የኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊከወን ይገባ ነበር ብሏል።
በተጨማሪም ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገ ሕገወጥ የመሬት ሽያጭ በተገኘ ቦታ ላይ የተሰሩ ቤቶች እና ከ2005 ዓ.ም በኋላ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ በመንግሥት ይዞታዎች ላይ የተገነቡ ቤቶችም በዚሁ አጋጣሚ እንዲፈርሱ ተደርገዋል ብሏል።
የፈረሱት ቤቶች ስሪትና ግንባታ የተለያየ መሆኑን የጠቀሰው የኢሰመኮ መግለጫ ሂደቱ ላይ ተገቢው መለየት እና ማጣራት ተደርጎ ሊፈጸም ይገባ እንደነበር ጠቅሷል።
“ሕገ ወጥ ግንባታ ማፍረስና የመንግሥት ይዞታ የሆነን ቦታ መልሶ መውሰድ ሕጋዊ እርምጃ ቢሆንም እንኳን፤ የመኖሪያ ቤት ማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት ዜጎችን መኖሪያ ቤት አልባ በሚያደርግ መልኩ መደረግ እንደሌለበትም” ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ እንደሚደነግግም ኢሰመኮ አስታውሷል።
ያለ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስለመከናወኑ
ሌላኛው የኢሰመኮ ሪፖርት የገለጸው እርምጃው ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ (ቀድሞ የማሳወቅ ግዴታ) ስለመከናወኑ ነው።
ኢሰመኮ በማናቸውም ዓይነት ይዞታና ሁሉም ዓይነት ቤቶች በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ መንገድ በተያዙ መሬቶች ላይ የተሰሩ ቤቶች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የመኖሪያ ቤት እንዲፈርስ ሊደረግ እንደማይችል ጠቅሷል።
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅም መደንገጉን ገልጿል።
የከተማዋ አስተዳደር ኃላፊዎች ቤቶች የፈረሱባቸውን ነዋሪዎች በተመለከተ ከባለቤቶቹ ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ መፈጠሩን እንዲሁም በሚፈርሱ ቤቶች ላይ በቅድሚያ ምልክት መደረጉን ገልጸዋል። የቤቶቹ ባለቤት ግንባታውን እንዲያፈርሱ ጊዜ እንደተሰጣቸውና በዚህ ጊዜ ግንባታውን ያላፈረሱ ሰዎች በአፍራሽ ግብረ ኃይል እንዲፈርስ መደረጉንም በተጨማሪ ገልጸዋል።
ሆኖም ኢሰመኮ ባደረገው ምርመራ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ አልተደረገም ብሏል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው አቤቱታ አቅራቢዎች ቤታቸው እንደሚፈርስ አስቀድሞ ያልተነገራቸው እና አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በድንገት መጥቶ እንዳፈረሰባቸው መናገራቸው ተጠቅሷል።
በኢሰመኮ መግለጫ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው በተለምዶ ለቡ ተክለኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ወደ ሥራ ገበታቸው ከሄዱ በኋላ ሃብት ንብረታቸውን ሳያወጡ የፈረሱባቸው ቤተሰቦችን ኮሚሽኑ ማናገሩን ጠቅሷል።
በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ቄስ ሰፈርም እንዲሁ ነዋሪዎቹ ቤታቸው ውስጥ እያሉ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ድንገት መጥቶ ቆርቆሮ መንቀል መጀመሩን ጠቅሰዋል።
አድሏዊ አሰራር
ኢሰመኮ ሌላው የጠቀሰው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አድሏዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንዳሉ ለመመልከት መቻሉ ተገልጿል። በለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ ቄስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተያይዘው ከተሰሩ ቤቶች ውስጥ ሁለት ቤቶችን በማስቀረት ሌሎች እንዲፈርሱ መደረጉን ገልጿል። ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች አድሎው ብሔር ተኮር እንደሆነ ለኢሰመኮ የገለጹ ሲሆን የመንግሥት ኃላፊዎች ማስተባበላቸው ተጠቅሷል።
በርካታ ነዋሪዎች በከፍተኛ ድካም እና ጥረት ያፈሩ ንብረት ሲወድምባቸው ስሜታዊ መሆናቸው የሚጠበቅ መሆኑ ከግንዛቤ በማስገባት የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ምላሽ የተቆጠበ እና በትዕግስት ሊሆን ይገባልም ብሏል።
“ቤቶችን የማፍረስ እና በግዳጅ የማስነሳት ሂደት በርካታ ቤተሰቦችን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል፣ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ለማቋረጥ ተገደዋል፤ በርካታ ቤተሰቦች የእለት ተእለት ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ብሏል።
በተጨማሪም በርካታ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ቦታዎች ለመሄድ ተገደዋል፤ ከፊሎቹም መንገድ ላይ ወድቀዋል ወይም በተለያዩ የአገር ውስጥ መጠለያ ጣቢያ በመሰብሰብ የመንግሥት እርዳታ ለመጠባበቅ ተገደዋል ብሏል።
“ኢመደበኛ ይዞታዎቸን መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃዎች ሰዎች ሕይወታቸው እንዲናጋ እና ቤተሰብ እንዲበተን የሚያደርግ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የተከበሩበት አሠራር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት የኢሰመኮ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል መናገራቸው ሰፍሯል።












