‘እጅ የበዛበት’ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office of Addis Ababa
ከሰሞኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ጋር ተያይዘው በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት ዕጣው ውድቅ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።
በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነውና ውዝግብ ባስከተለው ዕጣ ውስጥ መሳተፍ የነበረባቸው 79 ሺህ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ቢሆኑም፣ በድብቅ የተዘጋጁ 172 ሺህ ያህል ሰዎች በዕጣው ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርገዋል ተብሏል።
በዚህም 93 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተገቢ ባልሆነ መንገድ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት በተዘጋጀው ዕጣ ውስጥ መካተታቸው ተገልጿል።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ ቤቶች ግንባታ እና ቤቶቹን የማስተላለፍ ሂደት በተለይም ዕጣ አወጣጡ ጋር ተያይዞ ከቅሬታዎች፣ ወቀሳዎችና ሐሜቶች ነጻ ሆኖ አያውቅም።
የቤቶቹ ግንባታ ጥቃት፣ ግንባታቸው እና መሠረተ ልማቶቻቸው ያለመሟላት በየጊዜው የሚነሳ ጉዳይ ቢሆንም፣ በቤት ችግር እየተንገላታ ዕድሉ ይደርሰኛል ብሎ የሚጠብቀው ነዋሪ ዋነኛው ቅሬታ ግን ቤቶቹን የማስተላፍ ሂደቱ ወይም ዕጣው ሆኖ ቆይቷል።
ከዚህ በፊት በነበሩት ሂደቶች ምዝገባው ውስጥ ያልተካተቱ ሰዎች በባለሥልጣንት ትዕዛዝ ቤቶቹ እንዲሰጣቸው ሲደረግ መቆየቱን ዘወትር የሚነሳ ጉዳይ ነው።
በግንባታ ዕቃዎች መወደድ ምክንያት እና ግንባታዎችን ለማከናወን ባጋጠመ የገንዘብ ችግር ምክንያት በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት መከናወን ያልቻለው የጋራ ቤቶች ግንባታ በርካቶች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል።
በዚህ መካከል የከተማው አስተዳደር ተጠናቀዋል ያላቸውን ከ25 ሺህ በላይ ቤቶችን ይፋዊ በመሆነ ሂደት ለተመዝጋቢዎች ሊያስተላልፍ መሆኑን ባለፈው ሳምንት አሳውቆ ነበር።
ይህም በቤት ችግር በእጅጉ እየተፈተነ ላለው የከተማው ነዋሪ አንዳች ተስፋን አጭሮ በጉጉት እንዲጠብቅ አድርጎታል።
አርብ ሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ለ20/80 እና ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎች ዕጣው በወጣበት ወቅት፣ ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት የከተማው አስተዳደር ዕጣው የሚወጣበት ሂደት ከአድልዎ ነጻ እንዲሆን የሚያደርግ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ከንቲባዋ እዳሉት ሳይሆን የዕጣ ማውጣቱ ሂደት ችግር እንደነበረበት ቅሬታ መቅረብ የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነበር።
አስተዳደሩም ጥቆማዎች መድረሳቸውን ተከትሎ በአስቸኳይ የማጣራት ሥራ እንዲካሄድ ተደርጎ፣ የዕጣ ማውጣት ሂደቱ ተዓማኒነት የሌለው ስለነበረ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲሆን ተወስኗል።
የተከሰተው ምንድን ነው?
የአዲስ አበባ ከንቲባዋ ከ14ኛው ዙር የዕጣ ማውጣት ሂደት ጋር በተገነናኘ የተከሰተውን ችግር “የቴክኖሎጂ ውንብድና አጋጥሞናል፣ ድርጊቱም አመራር የመራው ወንበዴ ነው” በማለት ሁኔታው የቤት ስርቆት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ጭምር የተስተዋለበት እንደነበር ተናግረዋል።
የዚህ ስራ ሌላው አላማ መንግሥት ህዝብን ማገልገል ብቃት የለውም የሚል ገፅታ ለመፍጠርና ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲያምፅ ለማድረግ በማሰብ ነው በማለት ከንቲባ አዳነች ገልፀዋል፡፡
በዚህ ሂደት ችግር እንዳጋጠመን ማጣራት መጀመራችን ህዝብን ሃብት መታደግ እንድንችል አድርጎናል፡፡ ህዝቡን መታደግ ችለናል፡፡
ለከተማው አስተዳደሩ የዕጣ ማውጣት ሂደቱን በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት ሥርዓቱ አስተማማኝ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ማረጋገጫ እንደሰጠው ቢነገርም፣ ተቋሙ ሕጋዊ በሆነ ደብዳቤ ማረጋገጫ እንዳልሰጠ በምርመራው ተደርሶበታል።
ከንቲባዋ እንዳሉት ለዕጣው ሂደት ግብአት የሚሆኑ መረጃዎች (ዳታ) ለቀናት በሰዎች አጅ መቆየታቸውና ይህም የሆነው በኃላፊዎች ትዕዛዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ በግለሰቦች እጅ የገባው ወሳኝ መረጃ ቤት ለማግኘት የሚጠበቀውን ቁጠባ ያቋረጡ እና በዚህ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ብቁ ያልሆኑ ሰዎች ጭምር እንዲካተቱ ዕድልን ፈጥሯል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው እንዳሉት፣ ይህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተመዝጋቢዎች በዕጣ ለማስተላለፍ በከተማው አስተዳደር ሥራ ላይ የዋለው ሥርዓት በርካታ ችግሮች አሉበት።
በዚህም ሥርዓቱ ተመሳሳይ ሶፍትዌሮችን ለማልማት የሚያስፈልጉ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያልጠበቀ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን “ሦስቱን አካላት፤ አልሚውን፣ ተጠቃሚውን እና አረጋጋጩን አካላት የቀላቀለ እንዲሁም ለምዝበራ ያጋለጠ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሸመቴ።
ጨምረውም ለዚህ የዕታ ማውጣት ሂደት ግብአት የመሆነው መረጃ (ዳታ)፣ ከእጅ ንክኪ ነጻ መሆን የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ነገር ግን እጅ በዝቶበት እንደነበረ ተገልጿል።
ባለሙያዎችም እንዳሉት ዕጣውን ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋለው ሥርዓት ሲዘጋጅ ተገቢውን መንገድ ያልተከተለና ሁሉም ሂደት በአንድ ሰው የተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
በሂደቱም ቤት ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ እየቆጠቡ ለዕጣ ብቁ የሆኑ ነዋሪዎችን የሚመለከተው ከባንክ እና ከቤቶች ልማት የተገኘው መረጃ የአያያዝ ችግር የነበረበትና ለውጥ ለማድረግ የተጋለጠ እንደነበር ተገልጿል።
የመረጃ መዛባት በተፈጸመበት ኮምፒውተር ላይ በተደረገው ምርመራ የተፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይታወቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥንቃቄዎች መደረጋቸው የተደረሰበት ሲሆን፣ በተጨማሪም መረጃን ማጥፋት፣ መጨመር እና ማዘዋር ድርጊት መፈጸሙ ተረጋግጧል።
በዚህ ተፈጸመ በተባለው “የቴክኖሎጂ ውንብድና” በአጠቃላይ ለውድድር ብቁ ናቸው ተብለው የተገለጹት 79 ሺህ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች የነበሩ ሲሆን፣ በድብቅ የተዘጋጁ 172 ሺህ ያህል ሰዎች ለዕጣው ዝግጁ ሆነው ነበር። በዚህም 93 ሺህ ተገቢ ያልሆኑ ሰዎች በዕጣው መካተታቸው ተገልጿል።
በሕገወጥ መንገድ መረጃወቸው በዕጣው ውስጥ ተካተው ከተገኙት ውስጥ ደግሞ በባንክ የቆጠቡትን ገንዘብ ቀድመው አውጥተው የተዘጉ ተመዝጋቢዎች፣ የአመዘጋገብ ችግር ያለባቸውና ብቁ ያልሆኑ ሰዎች ጭምር ተካተው መገኘታቸውን በምርመራው የተሳተፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በሕገወጥ መንገድ በዕጣው ውስጥ እንዲካተቱ በተለያዩ መንገዶች የተዘጋጁ ሰዎች መረጃ ውስጥ እንዲካተት ብቻ ሳይሆን፣ ዕጣ ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋለው ሥርዓት የሚፈለገውን ሰው ዕጣ እንዲያወጣ ተደርጎም የተዘጋጀ መሆኑም ተመልክቷል።
በዚህም የሚጠበቅባቸውን የቤት ቁጠባ በባንክ ሲያከናውኑ ከቆዩት ተመዝጋቢዎች መረጃ ውስጥ ያልተካተቱ ሰዎች በዕጣው አሸናፊ ሆነው መገኘታቸውም በምርመራ ተደርሶበታል።












