መንግሥት 131 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሱን ገለጸ

ከሳዑዲ ተመላሽ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, @mfaethiopia

መንግሥት 131 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሱን አስታወቀ።

በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በተመሰረተው ብሔራዊ ኮሚቴ አማካኝነት 131 ሺህ ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ መመለስ እንደተቻለም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት መጋቢት 26፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከ16 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና አጋር ተቋማት የተውጣጣው ኮሚቴው በአንድ ዓመት ውስጥ 131 ሺህ ስደተኞችንም በመመለስ መርኃ ግብሩ መጠናቀቁም ነው የተገለጸው።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ሥራ መጋቢት 2፣ 2014 የተጀመረ ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችንም ከ7 እስከ 11 ባሉት ወራት ውስጥ ለመመለስም እቅድ ተይዞ ነበር።

ተመላሽ ስደተኞቹ ትናንት ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ እና የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተቀብለዋቸዋል።

በባህረ ሰላጤው ግዛት ላሉ ዜጎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ስደተኞችን በፍቃዳቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኝነት ማሳየቱን ሚኒስትር ዲኤታዋ አስታውቀዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ከስደት ተመላሾቹ ተመልሰው የሚቋቁመበትና ምቹ ሕይወት እንዲመሩ ለማስቻል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ይሰራል ማለታቸውም ሰፍሯል።

በሴቶች እና ማኅበራዊ ሚኒስቴር የስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሳልፈው አመዲን ከሳዑዲ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ላሉ ኢትዮጵያውን መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ስለመሆኑ ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።

ኃላፊው የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ እና ይህንን ጉዳይ የሚከታተል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ መኖሩን አስታውሰው፣ ተመላሾቹን ከአየር ማረፊያ ከመቀበል ጀምሮ ያሉ ሥራዎችን እንደሚከታተል ጠቁመዋል።

በነዳጅ ምርት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርቶ ለመቀየር መዳረሻ ከሚያደርጓቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተለያየ ወቅት በአገሪቱ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በሚል በርካታ ኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑና በማያፈናፍኑ እስር ቤቶች እንደቆዩና ለበርካታ የጤና እክሎች መጋለጣቸውን ቢቢሲ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

እስረኞቹ በቂ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ በሕይወት ለመቆየት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንደሚያዙ ይናገራሉ።

በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ከመቆያታቸውም ባሻገር በጥበቃዎች ማሰቃየትና ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች መግለጹ የሚታወስ ነው።

የማዕከሉ ጥበቃዎች በጎማ በተሸፈነ ብረት በፈጸሙባቸው ድብደባም ስደተኞች መሞታቸው ተመልክቷል።