ሂዩማን ራይትስ ዋች ከሳዑዲ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች እስርና እንግልት ገጥሟቸዋል አለ

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በሳዑዲ ሕገወጥ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲደረግ ቆይቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በሳዑዲ ሕገወጥ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲደረግ ቆይቷል

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ ውጪ አስረው በደል ፈጽመውባቸዋል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት አመለከተ።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ከሳዑዲ የተመለሱት የትግራይ ተወላጆች እስር፣ መንገላታት እና የደረሱበት እንዳይታወቅ መደረጋቸውን አመልክቶ የሳዑዲ መንግሥትም ስደተኞቹን የሚይዝበትን አስከፊ ሁኔታና ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን እንዲያቆም ጠይቋል።

በተለያዩ ጊዜ ከሳዑዲ አረቢያ የሚባረሩ የትግራይ ተወላጆችን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኙ የመቀበያ ጣቢያዎች እንደሚያስገቧቸውና አንደንዶቹም ከሕግ ውጪ እንዲቆዩ እንደሚደረግ ሪፖርቱ አመልክቷል።

ጨምሮም ከተመላሾቹ መካከል ወደ ትግራይ በመጓዝ ላይ የነበሩ ሰዎች በመንገድ ላይ ወይም አፋር ክልል ውስጥ ተይዘው እዚያው ክልል ውስጥና በደቡብ ኢትዮጵያ የማቆያ ቦታዎች ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ገልጿል።

"በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አስከፊ በደሎች የገጠማቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በማቆያ ማዕከላት ውስጥ እንዲያዙ ተደርገዋል" ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሐርድማን ተናግረዋል።

"በአደጋ ውስጥ ለሆኑ የትግራይ ተወላጆች ሳዑዲ አረቢያ ከለላ መስጠት ያለባት ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ከሕግ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙትን መልቀቅ አለባት" ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በአስከፊ ችግር ውስጥና በእስር ላይ የሚገኙ 40 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ባለፈው ዓመት መጀመሩ ይታወሳል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች እንዳለው ከፈረንጆቹ ኅዳር 2020 እስከ ሰኔ 2021 ድረስ ከሳዑዲ ከተመለሱት ኢትዮጵያውያን 40 በመቶው የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ሥራ አጥነት፣ ድርቅ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አደገኛ በሆኑ የባሕር ላይ መስመሮች በመጓዝ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲገቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ደግሞ በባሕር ላይና በበረሃዎች ላይ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ወቅት በገጠሟቸው አደጋዎች ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ከሳዑዲ ተመላሽ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የገጠማቸውን እንግልት በተመለከተ 23ቱን ማናገሩን ጠቅሶ ለወራት በአዲስ አበባ፣ በአፋር ሰመራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ሾኔ፣ በኦሮሚያ ጂማ ውስጥ በሚገኙ የማቆያ ቦታዎች ተይዘው መቆየታቸውን ገልጿል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በሪፖርቱ ላይ እንዳለው ጉዳዩን በሚመለከት ምላሽ ለማግኘት ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ዋሽንግተን ለሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ እና ለሳዑዲ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን አመልክቷል።

አንድ ዓመት ያለፈው ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እንግልትና እስር እያጋጠማቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተቋማት በሪፖርቶቻቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ፖሊስ ጉዳዩን በተመለከተ ቀደም ሲል በሰጡት ምላሽ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ሳይሆን ከሕገ ወጥ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።