በሳዑዲ እስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአእምሮ መታወክ መጋለጣቸውን ገለፁ

የፎቶው ባለመብት, Amiin
ሳዑዲ አረብያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በፀጥታ አካላት እየታደኑ እየተያዙ መሆኑን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በእስር ቤት ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ የቆዩት ደግሞ መንግሥት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ባለማድረጉ የተወሰኑት ከጭንቀት የተነሳ ለሕመም እና የአእምሮ መታወክ እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና አምባሳደር የሆኑት ሌንጮ ባቲ በኤምባሲው ፌስቡክ ገጽ ላይ ከሳዑዲ የውጪ ጉዳይ ባለስልጣናት ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት እና እዚያ ስላሉ የኢትዮጵያ ዜጎች አስመልክቶ እሁድ ሰኔ 6 2013 ዓ.ም መወያየታቸው ተገልጿል።
በዚህ ውይይታቸው በእስር ላይ ስለሚገኙ፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ስለ ተቃጠለባቸው እና በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ስለገቡ ኢትዮጵያን መወያየታቸውን እና ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በጋራ እየሰሩ መሆኑ ሰፍሯል።
ነሚድ ኡስማን ሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ሹሜሲ የተባለ እስር ቤት ውስጥ ከአንድ አመት በላይ ታስሯል።
ይህ ወጣት ከስራው ቦታ ከሪያድ ተይዞ፣ በሪያድ ገጠራማ ስፍራ ለአምስት ወር ከታሰረ በኋላ አሁን ወዳለበት ወደ ጅዳ እስር ቤት መዛወሩን ይናገራል።
ጅዳ ውስጥ ከታሰሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቢፈልጉም የሚጠይቀን የመንግሥት አካል አላገኘንም ይላል።
"ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚያናግረን ሰው ለማግኘት ብለን ከዚህ በፊት ለሶስት ቀን እና ከዚያ በላይ የረሃብ አድማ ላይ ነበርን። ነገር ግን 'ተዋቸው፤ ይቀመጡ' ብለው መልስ እንደሰጡ ፖሊሶች ነገሩን" ይላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በየሳምንቱ ከሳዑዲ በርካታ ስደተኞችን ወደ አገራቸው እየመለሰ መሆኑን ቢናገርም ወጣቱ ከዚህ የተለዬ ሃሳብ አለው።
ይህ ወጣት ግን "እንደምንሰማው ዜና ከሆነ መንግሥት በብዛት ወደ አገር ቤት የሚመልሰው ከሪያድ ነው። እኛ ደግሞ የምንሰማው የተለያዩ በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች እየወሰደ እንደሆነ ነው። ከዚህ ውጪ ከየት እንደሚያስገቡ አይገባንም" በማለት ቅሬታውን ይናገራል።
"እዚህ ጅዳ ያለነው ሰዎች ላይ ማግለል ይደርስብናል። ቢያንስ እኔ ያለሁበት እስር ቤት ውስጥ 30 ሺህ እንሆናለን። እኔ ያለሁበት ክፍል ውስጥ ደግሞ ከ100 በላይ አንድ ላይ እንኖራለን።"
ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው መሐመድ ኑር ያሲን በበኩሉ፣ ሳዑዲ ጅዳ ከተማ ውስጥ የፀጥታ አካላት የኢትዮጵያን ዜጎች እያደኑ እየያዙ እንደሆነ ይናገራል።
ከባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ጀምሮ ይህ እስር እየበረታ እንደመጣ የሚናገረው መሐመድ፣ የዚያኑ ቀን ወደ 500 የሚሆኑ ሰዎችን መያዛቸውን አውቃለሁ ይላል።
"ከ500 ሰው በላይ የሚሆኑ የያዟቸውን ሰዎች ወደ እስር ቤት አልወሰዱም። አንድ ግቢ ውስጥ ነው ያስቀመጧቸው። የኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው የሚፈልጉት። ጥፋት ያጠፋው ሌላ አካል ቢሆንም እየተፈለገ እና እየታሰረ ያለው ግን የኢትዮጵያ ዜጋ ብቻ ነው" ይላል።
"በከተማ ውስጥ ሰው መንቀሳቀስ አይችልም። ስድስት ቀን ሆኖታል። ወጣ ብለን ምግብ መግዛት አንችልም፤ እኔ አሁን ተደብቄ ነው ያለሁት"
መሀመድ የአገሪቱ የፀጥታ አካላት ኢትዯጵያውያንን ሲይዙ "እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ ነው የሚመቱት" ሲል ያስረዳል።
አብዛኛዎቹ የተያዙትንም በአንድ ግቢ ውስጥ ታጉረው እንዳሉ እና ወደ ሺሙሲ እስር ቤት እንዳላስገቧቸውም ይናገራል።
ለበሽታ እየተጋለጥን ነው
ወጣት ነሚድ በእስር ቤት ውስጥ በቂ አየር ስለማያገኙ በርካታ ሰዎች ለበሽታ እየተጋለጡ እንደሆነ በመግለጽ የሕክምና አገልግሎትም እንደማያገኙ ይገልጻል።
" የታመመ ሰው ከክፍላችን አስወጡልን ብንልም እሺ አይሉንም። ነገር ግን ይገርፉናል፤ ይሰድቡናል።
በግርፊያ እና በተለያዩ ጉዳቶች የተነሳ አእምሯቸውን የሳቱ ሰዎች (ያበዱ) አሉ። እኔ ጋር ራሱ ቢያንስ አራት ሰዎች አእምሯቸውን ስተዋል።
እነዚህ ወጣቶች ያላቸው ጥያቄ ወደ አገር ቤት መመለስ ሲሆን አሁንም አዳዲስ ሰዎች እየተያዙ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም የታሰሩት ደግሞ ወደ አገር ቤት እየተወሰዱ አይደለም" ሲል ይናገራል።
ሪያድ ውስጥ ከአራት እና አምስት ወራት በፊት የታሰሩ ሰዎች ወደ አገር ቤት እየተወሰዱ እንደሆነ የሚናገረው ይህ ወጣት፣ ጅዳ ግን ለረዥም ጊዜ የታሰሩት ግን መረሳታቸው እንዳሳዘነው ይናገራል።
"መንግሥት ሲዘግብ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በማቆያ ወስጥ ያቆያቸው ናቸው ይላል። እኛ ግን በማቆያ ውስጥ ሳይሆን ለሰው ልጅ የማይመች እና ክብር የሌለው ቤት ውስጥ ታጉረን ነው ያለነው"
የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ያሉ እና ወደ አገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ ዜጎችን በየሳምንቱ ወደ አገር ቤት እያስገባ መሆኑን ሲናገር ነበር። በዚህም ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ዜጎች ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።
መድልኦ ይደርስብናል ለሚለው የስደተኞቹ ቅሬታ የተባለ ነገር ባይኖርም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ይናገራል።
በሳዑዲ አረቢያ ልዩ መልዕክተኛ እና አምባሳደር የሆኑት ሌንጮ ባቲ ከሳዑዲ የውጩ ጉዳይ ባለስልጣናት ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚመለከት እና በአገሪቱ ስላሉ የኢትዮጵያ ዜጎች አስመልክቶ እሁድ ዕለት ሰኔ 6 2013 ዓ.ም መወያየታቸው በኤምባሲው የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ተገልጿል።
በዚህ ውይይታቸውም አምባሳደር ሌንጮ፣ እስር ቤት የሚገኙ የኢትዮጵያውያን ዜጎችን፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለባቸው እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ወደ ሳዑዲ አረቢያ በሕገወጥ መልኩ ገብተው እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን በምን መልኩ በፈቃዳቸው ወደ አገራቸው መመለስ ይቻላል በሚለው ላይ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸው በፌስቡክ ገፁ ላይ ተገልጿል።
በተጨማሪም በውይይታቸውም ላይ ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ከገንዘብ ቅጣት እና ከእስር ውጪ ወደ አገር ቤት መመለስ የሚችሉበትን መንገድ ላይ ተወያይተዋል።
እንዲሁም በቅርቡ ፖሊስ ኢትዮጵያውያን በጅምላ አፍሶ የማሰር ተግባር እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ በሰፊው መወያየታቸውን ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።
ኤምባሲው የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በጋራ እየሰሩ መሆኑን በመግለጽ እስከዚያው ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ ባለው መንገድ በትዕግስት እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፏል።













