ምርጫ 2013፡ ጥቂት ቀናት የቀሩት የኢትዮጵያ ምርጫ አጭር ዳሰሳ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አዲሱ ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አዲሱ ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳ ላይ

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ደም አፋሳሽ ግጭት ተከስቶ የረሃብ አደጋ አንዣቧል እንዲሁም በብሔሮች መካከል ውጥረት ቢበረታም ኢትዮጵያ ሰኔ 18/2013 ዓ.ም ምርጫ ልታካሂድ አቅዳለች።

ምርጫው ከዓመት በፊት እንዲካሄድ የታቀደ ቢሆንም ባለሥልጣናት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመጥቀስ መራዘሙን አስታውቀዋል።

መራጮች 547 የፌዴራል ፓርላማ አባላትን ይመርጣሉ። የአሸናፊው ፓርቲ መሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ። አገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ለመጨረሻ ጊዜ ያካሄደችው በ 2007 ነበር።

ምርጫው ለምን ትልቅ አጀንዳ ሆነ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ስልጣን ይዘው ጭቆናን ለማስቆም ቃል ከገቡ ወዲህ የሚደረግ የመጀመሪያ ምርጫ ሲሆን ከወዲሁ ግን ስጋቶች ተጋርጠውበታል።

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በበላይነት በተቆጣጠረው ጥምር መንግሥት ላይ የተነሳው የተቃውሞ አመጽ የአገሪቱን መናጡን ተከትሎ ነበር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን የመጡት።

ሙስናን በመዋጋት፣ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ ብዛት ያላቸውን ሴቶችን በካቢኔያቸው ውስጥ በመሾም እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውን የድንበር ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረውን ቁርሾ በማስቀረት ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ሰላም ፈጠሩ።

የለውጥ አራማጁ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸነፉ። የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው ህወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅሟል መባሉን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ "የሕግ ማስከበር" የሚለውን ወታደራዊ እርምጃ ወስዷል። የህወሓት ጥቃት ጠቅላይ ሚንስትሩን ከስልጣን ለማውረድ የተደረገ እንደሆነ ጭምር ተመልክተውታል።

ይህም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለቀጠፈ ግጭት ምክንያት ሲሆን ለጅምላ ችግር እና በክልሉ ውስጥ የረሃብ አደጋ እንዳለ እንዲዘገብ ምክንያት ሆኗል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲባባስ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ባለፈው ዓመት ሊደረግ የነበረው ምርጫ መዘግየት ነው።

መስከረም 2013 የስልጣን ዘመናቸው ያበቃ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘሚያ ወረርሽኙን እንደ ሰበብ ተጠቅመዋል ሲል ህወሓት ወንጅሏል።

በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት በርካቶችን ለሞት ዳርጓል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት በርካቶችን ለሞት ዳርጓል

የዐቢይ ራዕይ ምንድነው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዙ በኋላ በህወሓት የበላይነት የሚመራውን የአራት ብሔሮች ፓርቲ ጥምረት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢህአዴግ) አፈረሱ።

ኢሕአዴግ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በስልጣን ላይ የነበረ ፓርቲ ሲሆን ሰፊ የአፈና እና የማጭበርበር ክስ በሚቀርብበት የ2007 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ሁሉንም መቀመጫ አሸንፏል።

አንድ ፓርቲ ማቋቋም አገራዊ አንድነትን ለማጎልበትና የብሔር ክፍፍልን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ኢሕአዴግን በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ እንዲተካ አድርገዋል።

ሆኖም ግን ተቺዎቻው የብሔር ልዩነቶችን ችላ ለማለት መሞከር ቅሬታን ከማትረፍ ባለፈ በየአካባቢው ያለውን ስልጣን በመሰብሰብ በመዲናዋ አዲስ አበባ ያከማቻል ይላሉ።

ህወሓት አዲሱን ፓርቲ ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከዐቢይ ጋር ለነበረው አለመግባባት ቁልፉ ጉዳይ ነበር።

ቀሪዎቹ ሦስቱ የኢሕአዴግ አባላት ማለትም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ፈርሰው አንድ ወጥ ፓርቲ ለመሆን ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ በምርጫው የበላይነት እንደሚያገኝ ይጠበቃል

ተቃዋሚዎች አሉ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ40 በላይ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አቅርበዋል ቢልም አብዛኞቹ የክልል ፓርቲዎች ናቸው ብሏል።

ከዘጠኝ ሺህ በላይ ዕጩዎች በፌዴራል እና በክልል የምርጫ ፉክክር ላይ የሚወዳደሩ ሲሆን ይህም ከየትኛውም የኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች የተካፈሉበት መሆኑን ተገልጿል።

ሆኖም ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት በአመራሮቻቸው ላይ የወሰደው እርምጃ ለምርጫ ለመዘጋጀት የያዙትን ዕቅዶች ስለማስተጓጎሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለው የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኙት የኦሮሚያ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን እንደሚያገሉ አስታወቀዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተወሰኑ አመራሮቹ መታሰራቸውን እና መዲናዋ የሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ያሉ ቢሮዎቹ በመንግሥት መዘጋታቸውን በመጥቀስ በመጋቢት ወር ከምርጫው ራሱን አግሏል።

ፓርቲው ዐቢይ ከመጡበት ኦሮሚያ ክልል የተገኘ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች ያሉት በኢትዮጵያ ካሉ አንጋፋ ፓርቲዎች አንዱ ነው።

የጃዋር መሐመድ ፓርቲ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስም (ኦፌኮ) እንዲሁ በመጋቢት ወር በተመሳሳይ ምክንያቶች ከምርጫው ለመውጣት መገደዱን አስታውቋል።

ፓርቲው ጃዋርን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አመራሮቹ እና የምርጫ ታዛቢዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

በቅርቡ ህወሓት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ተሰይሟል። የተወሰኑት አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎቹ ደግሞ በስደት ላይ ናቸው ወይም በትግራይ የሽምቅ ውጊያ ማድረጉን ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎችን ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲን (ኢዜማ) የሚመሩት ብርሃኑ ነጋ በምርጫው የሚሳተፍ አገራዊ መገለጫ ካላቸው ጥቂት ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

የ62 ዓመቱ ፖለቲከኛ እና ምሁር በ1997 የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው የተመረጡ ሲሆን በወቅቱ በህወሓት የበላይነት በተያዘው መንግሥት አሸናፊነታቸው ተቀልብሶ ለእስር ተዳረጉ።

ዓለም አቀፍ ጫናን ተከትሎ ከ21 ወራት እስር በኋላ ተለቀዋል። ወደ አሜሪካ በማቅናት በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር ሙያቸው ቀጥለው ነበር። በኋላም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ስልጣን ሲይዙ ወደ አገር ተመልሰዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ለ10 ዓመታት የትጥቅ ትግል ያስተባበረው የግንቦት ሰባትን ከመሠረቱት ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ቡድኑ እአአ ሰኔ 2018 የትጥቅ ትግል ማቆሙን ገልጾ የዐቢይ መንግሥት ማሻሻያዎች "እውነተኛ ዲሞክራሲ" እና "እውነተኛ ዕድል" ለመፍጠር ተስፋ እንዳላቸው አስታውቆ ነበር።

ብርሃኑ ነጋ የተቃዋሚው ኢዜማ መሪ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ብርሃኑ ነጋ የተቃዋሚው ኢዜማ መሪ

ምርጫው በሁሉም አካባቢዎች ይካሄዳል?

አይካሄድም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከወራት በፊት ድል ማድረጋቸውን በገለጹበት የትግራይ ክልል ምርጫው አይካሄድም። የአገሪቱ ፓርላማ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የትግራይ ክልል አስተዳደርን ሕገ-ወጥ በማለት አውጆ ድምጽ ከሰጠ በኋላ ክልሉ በጊዜያዊ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ይገኛል።

ጊዜያዊው አስተዳደር የምርጫ ጽህፈት ቤቶችን ከከፈተ በኋላ በትግራይ ምርጫ እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

የምርጫ ቦርድ በምርጫ ወረቀቶች ላይ የተስተዋሉ ጉድለቶችን በመጥቀስ ምርጫው በአገሪቱ በሚገኙ ሌሎች 54 የምርጫ ክልሎችም ምርጫው ለሌላ ጊዜ ተላልፏል ብሏል።

የሎጂስቲክስና የፀጥታ ችግሮችን በመጥቀስ ከአጠቃላዩ 547 የምርጫ ክልሎች በ78ቱ ድምጽ እንደማይሰጥ የሮይተርስ የዜና ወኪል የምርጫ ቦርድን ጠቅሶ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በበርካታ ክልሎች የብሔር ግጭቶች ጨምረዋል። ይህም ምርጫውን ያዳክማል የሚል ስጋት አለ።

ከትግራይ በተጨማሪ የፌደራል ኃይሎች በኦሮሚያ ታጣቂዎችን እና በአማራ ክልል ደግሞ ደግሞ የብሔር ግጭቶችን ለማስቆም ተሰማርተዋል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመሬት እና በሃብት ምክንያት በሚደረጉ ግጭቶችና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን በሚይዙ የተለያዩ ክልሎች መካከል ምርጫው የድንበር አካባቢዎች ውዝግብ ላይ ውጥረትን እንዲጨምር አድርጓል።

የምርጫ ቦርድ በየካቲት ወር በ98 የምርጫ ክልሎች የጸጥታ ስጋት መኖሩን ጠቅሶ ኦሮሚያን እና አማራን ጨምሮ አንዳንድ የክልል መንግሥታት በቂ ጥበቃ ባለማድረጋቸው ከሷል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስር ላይ የሚገኘው ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ

ነፃ እና ፍትሃዊ ይሆናል?

ባለፈው ግንቦት የአውሮፓ ሕብረት "በቁልፍ መለኪያዎች ላይ ስምምነት አለማድረጉን" በመጥቀስ የምርጫ ታዛቢ ልዑኩን ላለመላክ መወሰኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተልዕኮው ነጻነት ላይ ዋስትና ባለመስጠታቸው እና ለደኅንነታቸው ሲባል የመገናኛ መሣሪያዎች እንዲያስገቡ አልፈቀዱም ሲል ከሷል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ሕብረት ውሳኔ "የምርጫውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ አስፈላጊም አስገዳጅም አይደለም" ብሏል።

የአሜሪካ ሴናተሮች ቡድን ባለፈው ወር ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ምርጫውን በኢትዮጵያ ሕጎች እና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ለማካሄድ እየሞከርኩ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ በአሁኑ ወቅት የትኛውም ትልቅ ማሻሻያ "የምርጫውን አጠቃላይ ታማኝነት፣ ተዓማኒነት፣ አጠቃላይነት እና ወቅታዊነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ብለው "ጉድለቶች የማይቀሩ መሆናቸውን" አምነዋል።

ለመራጭነት መመዝገብ ከሚችለው ከ50 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ውስጥ ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ ለመስጠት ለመምረጥ ተመዝግበዋል።

በመጀመርያው የምርጫ መርሃ ግብር መሠረት ከምርጫ ክልሎች የመጀመሪያ ደረጃ ምርጫው ውጤት ምርጫው ከተከናወነበት ቀን አንስቶ ባሉት አምስት ቀናት ሲገለጽ የመጨረሻው የተረጋገጠ ውጤት ደግሞ በ23 ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋል።