ምርጫ 2013፡ በምርጫው ዕለት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ

ድምጽ የሚሰጥ ሰው እጅ እና የድምጽ መስጫ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB

ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው ምርጫ ዝግ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ሁሉም ኢትዮጵኣውያን ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ወጥተው በምርጫው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጨምረውም ዜጎች በዚያው ዕለት "ኢትዮጵያን ለማስዋብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸው እንዲያኖሩ" ጠይቀዋል።

በምርጫው ቀን ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ስለሚሆኑ በቀጣይ ቅዳሜ ክፍት ሆነው የሰኞውን ሥራቸውን እንደሚያካክሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

ከሌላው ጊዜ በተለየ በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ በሥራ ቀን ላይ እንዲሆን በመደረጉ እንዲሁም በዚያ ዕለት ሥራ ዝግ እንደሚሆን በይፋ ባለመነገሩ በተለያዩ ሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በመራጭነት ለመሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታ ሲያጠያይቅ ነበር።

ከዚህ በፊት በነበሩት ምርጫዎች ድምጽ የሚሰጥበት ዕለት ዕሁድ ስለሚሆን ያለተጨማሪ መመሪያ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ሰዎች በእረፍት ቀናቸው በምርጫው እንዲሳተፉ አስችሏል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ ሰኔ 07 ቀን በሰጠው መግለጫ ላይ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ በሚሰጥበት ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም፣ ሥራ ይኖራል ብሎ እንደማይጠብቅ ገልጾ ነበር።

6ኛው አገራዊ ምርጫ የዛሬ ሳምንት ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ በድምጽ መስጫ ዕለት ቦርዱ ሥራ እንዲኖር ፍላጎት የለውም ብለዋል።

የመንግሥት እና የግል ተቋማት ትብብር ማድረግ ሕጋዊ ግዴት መኖሩን አስታውሰው፤ ተቋማት ትብብር እንዲያደርጉ በይፋ ቦርዱ ጥያቄ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

"ሥራ አይኖርም ብለን ነው የምናስበው። ይህ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ እና ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ይረዳል። ይህ በረዥም ጊዜ የሚደረግ ስለሆነ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በዚህ ረገድ ይተባበሩናል ብለን እንጠብቃለን" ብለዋል።

በዚህም መሠረት ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በምርጫው ዕለት ዝግ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

ሶሊያና በመግለጫቸው ላይ አክለውም ምርጫ ጣቢዎች ማለዳ 12 ሰዓት ተከፍተው ምሽት 12 ሰዓት እንደሚዘጉ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ቆጠራ እንደሚካሄድ እና የየምርጫ ጣቢያዎቹ ውጤት እንደሚገለጽ፤ በማስከተለም የአገር አቀፍ ውጤት በሕጉ መሠረት ይፋ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በመጪው ሰኞ ለመኪካሄደው የድምጽ መስጠት ተግባር አገልግሎት ላይ የሚውሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ወደ ተለያዩ የምርጫ ክልሎች ከዛሬ ሰኞ ምሽት ጀምሮ መላክ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በግንቦት ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች በተያዘላቸው ጊዜ ተዘጋጅተው ባለመጠናቀቃቸው በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።

ነገር ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በ54 የምርጫ የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ምርጫ እንደማይካሄድ አስታውቋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል እንዲሁም የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የገለፁት ባለፈው ሳምንት ነበር።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ከአጠቃላይ ምርጫው ጋር ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ቀን ይካሄዳል ተብሎ ታቅዶ የቆየ ቢሆንም ሕዝበ ውሳኔው በሚከናውንባቸው አካባቢዎች በጸጥታ ችግር የተነሳ ድምጽ የማይሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች መኖራቸው ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት ሕዝበ ውሳኔውን በትክክል መመዘን ስለማይቻል ሕዝበ ውሳኔው ከሌሎች የምርጫ ክልሎች ጋር ጳጉሜን 01 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከናወን ይሆናል ሲል ቦርዱ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድባቸዋል በተባሉት አከባቢዎች ያሉ የዞን አመራሮች በውሳኔው ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ማሰማታቸውን ሶሊያና ጠቅሰዋል።

የዞን አመራሮች ሕዝበ ውሳኔው በጉጉት የሚጠበቅ ነገር ስለነበረ በልዩ ሁኔታ የሚካሄድበት አማራጭ ካለ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን እና የራሳቸውን አማራጮችም መሰንዘራቸውን ጨምረው አመልክተዋል።

ምርጫው ቀርቶ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ የሚቻልበት አማራጭ ካለ ብለው መጠየቃቸው በመግለጫው የተነሳ ሲሆን እስካሁን ግን ቦርዱ በዚህ ላይ ውሳኔ አለማስተላለፉን አብራርተዋል።

"ቦርዱ ከሕግ እና ከኦፕሬሽን አንጻር አይቶ ምናልባት ዛሬ ወይ ነገ ውሳኔ ይሰጣል" ብለዋል።

ታዛቢዎች

ሶሊያና ወደ 45ሺህ ለሚጠጉ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች የምርጫ ታዛቢዎች ባጅ ሰጥተናል ብለዋል።

የውጪ አገር ታዛቢዎችን በተመለከተ ሲናገሩም፤ "ምርጫውን ለመታዘብ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ታዛቢዎች ቁጥር የለኝም። የመጡ አሉ፣ እየመጡ ያሉም አሉ። በዚህ ሳምንት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ የውጪ ታዛቢዎች አሉ። የአፍሪካ ሕብረት፣ አይአርአይ ሚሽን ከድጋፍ ሰጪዎች ጋር መጥተዋል" ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ እና የምሥራቅ አፍሪካ ተቋማት ምርጫውን ለመታዘብ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ በሂደት ላይ ያለ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ሳምንት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

እውቅና የሌላቸው ምርጫ ጣቢያዎች

ከሰሞኑ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 79 የምርጫ ጣቢያዎች ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ ተከፍተው መራጮችን ሲመዘግቡ ነበር ማለቱ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ 2፣ በድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር 6 እንዲሁም በደቡብ ክልል በ71 መራጮችን የመዘገቡ የምርጫ ጣቢያዎች እውቅና የላቸውም በማለት ቦርዱ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።

ሶሊያና በሰጡት መግለጫ፣ እውቅና የላቸውም የተባሉት የምርጫ ጣቢዎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያ ኮድ ሳይሰጣቸው የመራጮች ምዝገባ ያካሄዱ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ሳይከናወን የመራጮች ምዘገባ ያከናወኑ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር ሳይሆን ከአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር ጋር ተባብረው ምርጫ ጣቢያ ከፍተው መራጮች የመዘገቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

71 የምርጫ ጣቢያዎች መጀመሪያውኑ መከፈት ያልነበረባቸው ናቸው ያሉት ሶሊያና፤ እውቅና የላቸውም በተባሉት እነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ ሰዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ወደፊት ውሳኔ ይሰጥበታል ብለዋል።

"ከድምጽ መስጫ በፊት ውሳኔ ይሰጣል። የአሰራር ግድፈት ትክክለኛውን አሰራር ሳይከተል መከፈቱን የተመዘገቡ መራጮች አያውቁም። የእነሱን መብት ለመጠበቅ ከድምጽ መሰጫ በፊት ውሳኔ መስጠት የተለያዩ አመራጮች አሉ ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ስላሉ አንዱ ላይ ውሳኔ እንሰጣለን።"

ለስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጮች በመላ አገሪቱ መመዝገባቸው ይታወቃል።