‘ወደ ሀገሬ የገባሁት 8 ዓመት የለፋሁበትን በሙሉ ትቼ ነው’፡ ከሳዑዲ ተመላሽ

ከሳዑዲ ተመላሽ ሴት ከአውሮፕላን እንደ ወረደች ተንበርክካ ምስጋና ስታቀርብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረብያ 100 ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿን ለመመለስ አቅዳ እስከ ግንቦት ወር አጋማሽ ድረስ 25 ሺህ ያህል መመለስ ችላለች።

ሽኩሪያ መሀመድ ወደ ሳዑዲ ያቀናችው በ2006 ዓ.ም የ19 ዓመት ወጣት ሆና ነው።

በሳዑዲ እስር ቤት ለዘጠኝ ወራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቆየቷን የምትናገረው ሽኩሪያ፣ ከዚያ በፊትም ቢሆን በሳዑዲ አረቢያ በመከራ የተሞሉ በርካታ ጊዜያትን ማሳለፏን ለቢቢሲ ገልጻለች።

ሽኩሪያ የሁለት ዓመት ቪዛ አግኝታ ሳዑዲ ከደረሰች በኋላ በ600 መቶ ሪያድ ወርሃዊ ደመወዝ አንድ ቤት ውስጥ ስራ ተቀጠረች።

ሁለት ዓመት የሰራችበት ቤት፣ አሰሪዎቿ ስልክ እድትይዝ አይፈቅዱም ነበር።

ወደ ቤተሰቦቿ ለመደወል “ስልኩ ሰራም አልሰራም” ለአሰሪዎቿ 50 ሪያድ ለካርድ የመክፈል ግዴታ ነበረባት።

በዚህ ሁኔታ ሁለት ዓመታት ከቆየች በኋላ ደመወዝ እንዲጨመርላት እና ስልክ መያዝ እንዲፈቀድላት ጠየቀች። ይህ እንደማይሆን ተነገራት።

ሽኩሪያ ሌላ አማራጭ ወሰደች። ከቤቱ መጥፋት።

“የሚያስጠፋን ሀገሩን የሚያውቅ አረብ ነው። [የሚያስጠፉን ሰዎች] ብዙ ሪያድ ይከፍሉልናል እና እኛ ሰርተን እንከፍላለን እንጂ በእጃችን ብር የለም። ከጠፋን በኋላ ለሁሉም ሰው ጥሩ አይገጥመውም። ”

ታድያ ቀድሞ ከምትሰራበት ቤት ከጠፋች በኋላ ምን ዓይነት ህይወት እንደገጠማት በፍጹም ማስታወስ እንድማትፈልግ በጥልቅ ስሜት ነግራናለች።

ሽኩሪያ ማስታወስ የማትፈልጋቸውን በርካታ ‘የስቃይ’ ጊዜያትን አሳልፋ፣ ወደ አገሯ ይዛው የምትገባውን ጥሪት “የአቅሟን ያህል” መሰብሰብ ችላለች።

ከሌሎች ኢትዮጵያውን ጋር በጋራ በተከራዩት ቤትም ያሰባሰበችውን ጥሪት ታስቀምጥ ነበር።

እንደ ሽኩሪያ ገለጻ ይህ ቤት ከሚሰሩበት ቦታ እረፍት ሲኖራቸው የሚቆዩበትም ነው።

እናም ለእረፍት ቤት ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በነበረችበት ቀን በድንገት ፖሊሶች ሰብረው ገቡ።

“ሳልዘጋጅበት፤ ምንም ሳልይዝ መጥተው ከቤት ይዘውን ወጡ። መሳሪያ ምናምን ስለሚይዙ ‘ይሄን ልያዝ’ ብሎ መጠየቅ አይችልም። ወረቀት ስለሌለኝ መብቴ አይደለም።”

የሳዑዲ ተመላሾች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ

የፎቶው ባለመብት, MOFA

ኢትዮጵያውያን እስረኞች በሳዑዲ እስር ቤቶች

የሽኩሪያ ቀጣይ መዳረሻ የነበረው እስር ቤት ነበር።

ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ሴት ኢትዮጵያውያን በተጨናነቀ ሁኔታ በጋራ ታስረው እንደነበር ታስታውሳለች።

በእስር ቤቱ ነፍሰጡሮች እና ከአንድ በላይ ልጆችን የያዙ እናቶች እንደነበሩ የምታስታውሰው ሽኩሪያ እስር ቤት ውስጥ የወለዱ እንደነበሩም ትናገራለች።

ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለመውጣት በተደጋጋሚ ለእስር ቤቱ ጥበቃዎች ጥያቄ ያቀርቡም ነበር።

“ሀገራችን እንግባ ብለን ስንጠይቅ ይደበድቡናል፤ ምግብ ይከለክሉን ነበር። ይቀጡናል። ‘መንግሥታችሁ ነው እንጂ የማይፈልጋችሁ እንጂ የኛ ችግር ነው ወይ?’ እያሉ ለ24 ሰዓት ምግብ ይከለክሉናል” ትላለች።

ይህም ብቻ አይደለም። በእስር ቤት ውስጥ በኢትዮጵያኑ መካከል ግጭት እንደሚፈጠር ትናገራለች።

ስደተኞቹ በብሔር ተከፋፍለው “ሃይላንድ ውሃ ምናምን ያደርጉና በዛ ይደባደባሉ። . . . [አንድ ቀን] አሞኝ ተኝቼ ስለነበረ። ውሃ የተሞላ ሃይላንድ አይኔ ላይ ወድቆብኝ ነበር። ግንባራቸውን የተፈነከቱ ነበሩ። እነሱም ወደ ህክምና ቢሄዱም የኔ አይኔን ስለነበረ ዋና ክትትል ያደረጉልኝ ለኔ ነው።”

ሽኩሪያ በዚህ መልክ ለ8 ወራት በእስር ቤት ቆይታለች።

በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያኖችን በሚመለከት ጉዳዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ተቆጣጥሮ ‘በአሳሳቢ’ ሁኔታ ያሉት ኢትዮጵያውን “ፍትህ ይሰጣቸው” በሚል ተደጋጋሚ ጥሪ ይቀርብ ጀመር።

በዚህ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ የሚገኙ 100 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገባ ይፋ አደረገ።

ሽኩሪያም በዚህ እድል ወደ አገሯ ብትገባም ነገሮች እንዳሰበቻችው አልሆኑም።

ከሳዑዲ ተመላሾች ምን ድጋፍ ተደረገላችው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስገባቸው 100 ሺህ ዜጎች መካከል በመጀመሪያው ዙር 490 ኢትዮጵያውያን መጋቢት 21/2014 ዓ.ም ገብተዋል።

ከዚህ ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 15/2014 ዓ.ም 25 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የስደተኞች ጉዳይ ድርጀት (አይ ኦ ኤም) ለቢቢሲ የላከው መረጃ ያመለክታል።

በሴቶች እና ማህበራዊ ሚኒስቴር የስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተበባሪ የሆኑት አቶ አሳልፈው አመዲን ከሳዑዲ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ላሉ ኢትዮጵያውን መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እየደረገ ስለመሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኃላፊው የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ እና ይህንን ጉዳይ የሚከታተል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ ኮሚቴ መኖሩን አስታውሰው ተመላሾቹን ከአየር ማረፊያ ከመቀበል ጀምሮ ያሉ ስራዎችን እንደሚከታተል ጠቁመዋል።

በዚህ ስራ ላይ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ድርጀትም ይሳተፋል። ተመላሾቹ በሚቆዩበት ማዕከላት ድርጀቱና መንግሥት ለተመላሾቹ የጤና አገልግሎት፥ የስነልቦና ድጋፍ፥ “ግንዛቤ ማሳደጊያ” ገለጻ እንደሚሰጣቸው ኃላፊው ጠቁመዋል።

አቶ አሳልፈው ተመላሾቹ በማዕከላቱ “የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር” እስከ አራት ቀናት እንደሚቆዩ እና የምግብ፣ የንጽህና እቃዎች፣ የህጻናት አልሚ ምግብ ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

በማዕከላቱ ለአራት ቀናት ከቆዩ በኋላ ወደ የመጡበት አካባቢ እንደሚላኩ የገለጹት ኃላፊው “ወደ የአካባቢያቸው ሲመጡ የኪስ ገንዘብ ጭምር ይሰጣቸዋል” ብለዋል።

“እነኚህ ሰዎች ወደ የክልሎቻቸው ሲሄዱ በየክልሎቻቸው ባሉ የኛ መዋቅሮች ማህበረሰብ ውስጥ ሲቀላቀሉ መደበኛ ህይወታቸውን በአግባቡ እንዲጀምሩ ህብረተሰቡም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የሚያስችሉ ስራዎችም ከክልሎች ጋር በመቀናጀትም እንሰራለን” ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል የስነ ልቦና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ከስደት ተመላሾች አይ ኦ ኤም ከኢትዮጵያ ሳይኮሎጂስቶች ማህበር በተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች አማካኝነት ድጋፍ እንደሚያቀርብ ገልጿል።

በተጨማሪም አይኦኤም ከሴቶች እና ማህበራዊ ሚኒስቴር እንዲሁም ከዩኒሴፍ ጋር በመሆን ከወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ጋር የተጠፋፉ ሕጻናት የማፈላለግ እና የማገናኘት ስራ እንደሚሰራ ገልጿል።

ሆኖም ከተመላሾቹ ብዛት አንጻር ያለው ሃብት በቂ እንዳልሆነ የሚያነሳው አይ ኦ ኤም በተለይም ሁሉም ከስደት ተመላሾች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንዳገኙ ማረጋገጥ ፈተና መሆኑን ጠቅሷል።

ከዚህም አልፎ በተለይ በአዲስ አበባ ወይም በሌላ ስፍራ ቤተሰብ፥ ዘመድ ወይም ጓደኛ የሌላቸው የትግራይ ተወላጅ ከስደት ተመላሾችን ለረዥም ጊዜ ለማቆየት የሚስችል አገልግሎት “እጅግ ውስን መሆኑ” ሌላኛው ችግር እንደሆነም አመላክቷል።

”አሁን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩት መንግሥት ባዘጋጃቸው መጠለያዎች ውስጥ፣ በርካቶች ደግሞ የአይ ኦ ኤም አጋሮች ጋር ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን የማቆያ ቦታዎች እጥረት ከፍተኛ ችግር እየሆነ መጥቷል” ሲል ገልጿል።

አይ ኦ ኤም ከስደት ተመላሾች በዘላቂነት ለማቋቋም እና “አነስተኛ ቢዝነሶችን” ጀምረው ራሳቸውን የሚያግዙበት ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ይህ አይነት ድጋፍ ከተመላሾች ቁጥር አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው ብሏል።

ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ሰዎችን በዚህ መልኩ ድጋፍ የማግኘት እድላቸው ”እጅግ የጠበበ” ነው ሲልም አክሏል።

በዘላቂነት ድጋፍ ያለማግኘታቸው ደግሞ ከስደት ተመላሾቹ መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሰደዱ ያስገደዷቸው ችግሮች ላይ መልሶ ይጥላቸዋልም ሲል አትቷል።

አቶ አሳልፈው በበኩላቸው መደበኛ ያልሆነ ስደት አንዱ መነሻ የሆነውን ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ለመቅረፍ ለስደት ተመላሾቹ “የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የክሀሎት ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ አነስተኛ ብድሮችን ማመቻቸት ሰዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ለማደረግ ሰፊ ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው” ብለዋል።

ከሳዑዲ ተመላሽ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Ministry of Foreign Affairs

“ያጠራቀምኩት እዚያው ቀረ”

በ19 ዓመቷ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናችው ሽኩርያ፣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ አገሯ ስትመለስ 27 ዓመት ሞልቷታል።

ስምንት ዓመት በስደት የቆየችው ሽኩርያ፣ ከእስር ቤት መውጣቷ እና ወደ ሀገር መመለሷ “እጅግ በጣም" አስደስቷታል።

ሆኖም በስደት ያሳለፍኩት ሕይወት "በዜሮ ተባዝቷል" ትላለች።

ከዚህ ሁሉ ዓመታት “ድካም እና መከራ በኋላ” እጇ ላይ የቀረ ይህ ነው የምትለው ነገር የለም።

በስደት ስምንት ዓመት በቆየችባቸው ዓመታት በተለይም ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት በኋላ “አገሬ ስገባ እሰራበታለሁ” በሚል ገንዘብ እና የተለያዩ ንብረቶችን ከጓደኞቿ ጋር በተከራይችበት ቦታ ታስቀምጥ ነበር።

ይሁን እንጂ ወደ እስር ቤት ስትወስድ ያጠራቀመችውን በሙሉ መልሳ ማግኘት አልቻለችም።

“እዛ ህይወታችንን በሙሉ በስንት ነገር አሳልፈን፣ እንደምንም ኖረን ያጠራቀምነው ገንዘብ አላገኘነውም። [ወደ ሀገራችን] ገብተን ራሳችንን እናስተዳድርበታለን በሚል ነው ያጠራቀምነው። ግን እዛም ባዶ እዚህም ባዶ ሆንን” ስትል ገልጻለች።

አሁን ከእህቷ ልጅ ጋር ያለምንም ስራ እየኖረች እንደሆነ የምትናገረው ሽኩሪያ “ወደፊት ምን እንደሚመጣ አላውቅም። በራሴ የምጀምረውም የምሰራውም ነገር የለም። እዛ ያጠራቀምኩት እዛ ቀረ። እዚህም ሆኜ ልብስ እንድገዛ የረዳኝ ወንድሜ ነው. . . ያንን ሁሉ ፈተና አይቼ ተመልሼ ልውጣ ማለት ደግሞ ይከብዳል” ብላለች።

ወደ ኢትዮጵያ ከገባች በኋላ “ስማችንን መዝገበው ያለውን ነገር ጠየቁን” የምትለው ሽኩርያ “እንደውላለን” ከማለት በስተቀር የተደረገላት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደሌለም ተናግራለች።

“ተስፋ የሚሰጡን ነበር የመሰለን። አሁን ከመጣን ሁለተኛ ወራችንን ይዘናል። እና እስካሁን የተጠየቅነውም ነገር የለም። ይሄ ነው የተባልነው ነገርም የለም። ከዛም ሰርተን አላገኘንም፤ "

አክላም ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ነገሮች ይቀየራሉ የሚል ተስፋ የነበራት ቢሆንም አሁን ግን ያ ተስፋዋ መጥፋቱን ለቢቢሲ ገልጻለች።