35ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ አስታወቀ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳዑዲ አረቢያ መመለስ የሚፈልጉ ከ35ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን መመዝገባቸውን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ "ከ35ሺህ በላይ ዜጎች ለመመለስ ተመዝገበዋል፤ በቅርብ ጊዜም ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ" ብለዋል።

አምባሳደር ዲና በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመስ ዝግጅት መጠናቀቁን ጭምረው ተናግረዋል።

ለዚህም እንዲረዳ በአሁኑ ሰዓት ተመላሽ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በማጣራት የመመዝገብ ሥራ እየተከናወነ ነው መሆኑንና ወደ ኢትዮጵያ ለመመስ ከተመዘገቡት መካከል በተለያዩ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች እንዳሉበት ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ "ከ35ሺህ ውስጥ ስንቱ እስረኛ ነው? ስንቱ በመጠለያ ጣቢያ ያለ ነው የሚለው ዝርዝሩ የለኝም" ብለዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ፍቃደኛ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለሱ ተግባር ለምን ዘገየ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ዲና ሲመልሱ፤ "እስኪመዘገቡ እና እስኪለዩ ድረስ ጊዜ ይወስዳል። መመዝገቡ እና መለየቱ ለደኅንነት እና ለአገር ፍላጎት እንዲሁም ለሎጂስቲክስ አስፈላጊ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች እንጂ የዘገየው በሌላ ምክንያት አይደለም" ሲሉ መልሰዋል።

ከአንድ ወር በፊት በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የሚመር ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ ሳውዑ አረቢያ ተጉዞ በእሰረኞች አያያዝ እና ወደ አገር ቤት በሚመለሱበት ጉዳይ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መነጋገሩን አምባሳደር ዲና አስታውሰዋል።

ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ዜጎችን በተመለከ ቅሬታ መነሳቱን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

" 'በሕገ-ወጥ መንግድ በየመን በኩል የገቡ ናቸው፣ የአገር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው፣ መልካም ሥነ-ምግባር የላቸውም' የሚሉ ቅሬታዎች ተነስተዋል" ሲሉ አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።

ምንም እንኳ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት መሰል ቅሬታዎች ቢነሱም የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን የመውደስ ግዴታ ስላለበት የምዝገባ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና ሥራ አጥነት፣ ድርቅ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አደገኛ በሆኑ የባሕር መስመሮች በኩል በየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲገቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ደግሞ በባሕር ላይና በበረሃዎች ላይ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ወቅት በገጠሟቸው አደጋዎች ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።