ያልተገታው የኢትዮጵያውያን እስርና ሰቆቃ በሳዑዲ አረቢያ

የፎቶው ባለመብት, HRW
በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዝ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሠማሩባት አገር ናት።
በነዳጅ ወደ በለጸገችው የመካከለኛው ምሥራቅ አገር የሄዱ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ገቢ እያገኙ ህይወታቸውን ለውጠዋል።
ወደ ሳዑዲ ያቀኑ ኢትዮጵያውያን ላለፉት በርካታ ወራት የሚናገሩት ግን ሠርቶ ስለመቀየር ሳይሆን ስለሚደርስባቸው መከራ እና ግፍ ሆኗል።
በአገሪቱ ይሠሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ተይዘው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል።
ይህን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
በየዕለቱ በርካታ በረራዎች እየተደረጉ ዜጎቹን የማውጣት ሥራ መከናወኑ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ ቀጥሏል።
ላለፉት ሳምንታት ይህ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ የማስወጣት እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል።
ይህን ተከትሎም በሳዑዲ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ችግር ላይ እንዳሉ መናገር ጀምረዋል።
ቢቢሲ በእስር ላይ የሚገኙትን ኢትዮያውያንን ለማናገር ያደረገው ጥረት ባይሳካም በሳዑዲ የሚኖሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማግኘት ስላሉበት ሁኔታ ጠይቋል።
መሐመድ* ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካቀና ዓመታት ተቆጥረዋል።
ኢትዮጵያውያን ለምን ሳዑዲ ውስጥ እንደሚታሰሩ ይህ ነው የሚለው ምላሽ መስጠት አይቻለውም።
"በምን ምክንያት ኢትዮጵያውያን ብቻ ተለይተው እንደሚታሰሩ አላወቅነውም፤ ግራ የሚያጋባ ነው። ጂኦ ፖለቲክሱ ሊሆን ይችላል። [ኢትዮጵያዊያን] መታሰር ከጀመሩ ቆይቷል። ለሁላችንም እንቆቅልሽ የሆነ ጉዳይ ነው" ሲል ግራ መጋባቱን ይገልጻል።
በሳዑዲ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር የሚማቅቁ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
ችግራቸው እንዲታወቅላቸው በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ጭምር መልዕክታቸውን በስፋት ያስተላልፋሉ።
እስሩን "አዲስ አይደለም" የሚለው መሐመድ "አዲሱ ነገር ሰው እየተጎዳ መሆኑ ነው" ሲል ይገልጻል።
ኢትዮጵያውያን የታሰሩት ምቾት በሌላቸው ክፍሎች ውስጥ መሆኑንም ይጠቅሳል።
"የታሰሩባቸው ክፍሎች የተጨናነቁ ናቸው። አንድ ክፍል ውስጥ በብዛት ስለሚታሰሩ በሙቀት እና በሌሎችም ነገሮች ህይወት እስከ ማጣት ድረስ ችግር እየደረሰባቸው ነው" ሲል ያክላል።
ሱሌማንም* በዚህ ሃሳብ ከሚስማሙት እና መኖሪያቸውን ሳዑዲ ካደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።
ኢትዮጵያውያን እየተጎዱ በመሆናቸው የዓለም ሕዝብ፣ መገናኛ ብዙኃን እና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ሊጮሁላቸው እንደሚገባም ይገልጻል።
"እስር ቤት ውስጥ ቆይተዋል። ሁሉም ሰው እንደሚያየው በጣም ትልቅ ጉዳት ነው ያለው። ስለዚህ ለማን አቤት እንደምንል በጣም ጨንቆናል። ህጻናት እየተጎዱ ነው። ሴቶች እየተጎዱ ነው። እስር ቤት ውስጥ ይወልዳሉ። የሚለብሱት እና የሚበላ ነገር የላቸውም" ይላል ያሉበትን ሁኔታ ሲያብራራ።
ተመሳሳይ ችግር ከሚደርስባቸው መካከል ነፍሰጡሮችን ጨምሮ ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር በየእስር ቤቱ የሚማቅቁት እናቶች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም።
አንዳንዶቹ ደግሞ በዚያው 'የማይመች' እስር ቤት ውስጥ እስከ መውለድ ደርሰዋል። ወልደው በቀናት ልዩነት ወደ እስር ቤት እንዲገቡ መደረጋቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ይገልጻሉ።
አገር እና ሕዝብ ችግር ላይ ሲወድቅ ሲደግፉ እና ሲያበረታቱ ለነበሩት በሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ሲሉም ይገልጻሉ፤ ኢትዮጵያውያኑ።
"እኔ የሚገርመኝ እዚህ [ሳዑዲ] የታሰረው ሰው ቲኬት ቆርጦ ወደ አገሩ መመለስ የሚችል ነው። አገሩም ገብቶ ደግሞ መንግሥትን የሚያስቸግር አይመስለኝም፤ ሁሉም ቤተሰብ ያለው ነው። ይሄ ዜጋ እንዴት ተረሳ? በሳዑዲ የሚኖር ዜጋ ለምን ተረሳ?" በማለት በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከቤተሰብ በተጨማሪ አባይን [ህዳሴ ግድብን] ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደነበር መሐመድ ይጠቅሳል።
'ይህን ሲመለከቱም ነው ትኩረቱ በቂ አይደለም የሚሉት'
በተለያዩ የሳዑዲ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥታቸው ምላሽ እንደሚጠብቁ የሚናገረው መሐመድ "የዚህ አገርን መንግሥት መውቀስ አንችልም። መውቀስም ካለብን የኢትዮጵያን መንግሥት ነው። እንዲተባበሩን መጠየቅ ካለብንም የአገራችንን መንግሥት ስለሆነ ነው" ይላል።
ጨምሮም "ይህን ጉዳይ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል ለምን ችላ እንዳሉት ለሁላችንም እንቆቅልሽ ሆኖብናል። ይህን ሁሉ ሕዝብ ምን ዓይነት ጉዳት እየደረሰበት እንደሆነ እያየ እንዴት እስከዛሬ መፍትሔ እንዳለተሰጠ ምንም አልገባንም" ሲል ይጠይቃል።
ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ያለምንም ጥፋት ኢትዮጵያዊ ብቻ በመሆኑ ተለይቶ ጥቃት ሲደርስበት እና ተለይቶ ሲንገላታ መንግሥት ደግሞ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱ ያሳስባል የሚለው ሱሌይማን "ብዙ ሰው እየተጎዳ ነው። ስለዚህ ሁሉም ድምጽ ይሁነን" በማለት ይጠይቃል።
በሳዑዲ ያሉት ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ከማለት ባለፈ ኢትዮጵያውያኑን በፍጥነት መመለስ ካልተቻለ አደጋው በየቀኑ እየከፋ እንደሚሄድ ያስጠነቅቃሉ።
"መንግሥት ችግር ላይም ቢሆን ሌላው ቢቀር ሽማግሌዎች፣ አዛውንቶች እና ህጻናት አሉ። እናቶች አሉ እርጉዝ ሴቶች አሉ። እዚያው [እስር ቤት] ሜዳ ላይ ነው የሚወልዱት። ለህጻናት እና ለሴቶች እንኳን ቅድሚያ ተሰጥቶ የሆነ ነገር ቢደረግ እያልን ነው ሁላችንም የምንጮኸው" ሲል መሐመድ ጥሪ ያቀርባል።
አብዲም* በሳዑዲ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ነው።
የአገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር ስለሚያደርግ የሚያውቃቸውን ብዙ መረጃዎች መስጠት እንደማይችል ገልጾልናል።
ካለው ችግር ጎን ለጎን እስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሌላ ችግር አለባቸው ይላል።
"ትናንት እስር ቤት ውስጥ ልጆች [ኢትዮጵያውያን] በብሔር ተጣልተው ነበር። 180 ሆነው አንድ ክፍል ውስጥ ነበሩ። እነርሱ ተጣልተው ችግር ደርሶ ነበር። በዚህ ምክንያት ካሉበት ክፍል እንዲወጡ የሚጠይቁም ነበሩ" ሲል ሌላውን ችግር አስረድቷል።
"ዛሬ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ሲገቡ እዚህ ደግሞ ከዓመት በላይ ህጻናት ታስረው ሲንገላቱ ማየት በጣም ያምማል። ስለዚህ ከተቻለ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን" የሚለው መሐመድ ነው።
ሱሌማን በበኩሉ "በእርግጥ አገር ውስጥ ችግር አለ። ችግርም ቢሆን ሰው ሲቸገር ወደ አገሩ ነው የሚሸሸው እንጂ ወደ ሌላ አገር አይደለም። ሁላችሁም የዚህን ሕዝብ እሮሮ ለመንግሥት እንድታሰሙ በአላህ ስም እጠይቃለሁ። ሁኔታው በጣም ከባድ ነው። ህጻናትና ሴቶች በጊዜ ካልተመለሱ ፈታኝ ይሆናል። ይህንን አደራ ማለት እፈልጋለሁ። በጣም በጣም ያሳዝናል" ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ የሳዑዲ ፖሊስ ሰዎችን ይዞ ወደ እስር ቤት የመወርወሩ ስጋት የቀነሰ ቢመስልም፣ ፍርሃት ግን እንዳለባቸው ኢትዮጵያዊያን ይናገራሉ።
"[ፖሊሶች] ቤት ለቤት እየዞሩ [ፈቃድ ስለመያዛችን] ይጠይቃሉ። በጥቆማም ጭምር ነው የሚንቀሳቀሱት። ከ50 እስከ 60 መኪና በመያዝ ሰፈር የሚወሩት ነገር አሁን አሁን የለም" ይላል መሐመድ።
"እንደዚያ ማለት ግን ቆሟል ማለት አይደለም። በተለይ በየሱቁ እና በተለያየ ቦታ ፍተሻ እና ጥያቄ አለ። ወረቀት የሌለው ሰውማ መንቀሳቀስ አይችልም። መንግሥት በየቦታው ፖሊስ መድቧል። ፖሊሶቹ ሃበሻ ስለሚያውቁ [የፈቃድ] ወረቀት ይጠይቃሉ። ከሌለህ ይዘው ይሄዳል" ሲል መሐመድ አሁን ያለውን ሁኔታው ይገልጻል።
መሐመድ ከሰሞኑ የገጠመውን እንኳን እንደሚከተለው አጫውቶናል።
"መጀመሪያ ላይ በብዙ መኪና ነበር በየቀኑ የሚንቀሳቀሱት። ቤቴን ሰብረው ገብተው ነበር። እኔ ጋር የነበረ ልጅ ወረቀት ስለሌለው ይዘውት ወጡ። ሌሎቹ ስለነበራቸው አልነኳቸውም። አላህ ረድቶኛል። ብዙ ሰፈር ብዙ ጓደኞቻችን፣ ወልደው አራስ ህጻናት ይዘው የታሰሩ አሉ።
በሳዑዲ አረቢያ በስቃይ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ምላሽ መስጠቱ ተዘግቧል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በእስር ላይ ያሉ ዜጎችን ወደ አገራቸው ሲመልስ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ሂደት አለመቆሙን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፣ የተወሰነ መቀዛቀዝ እንደነበር ጠቅሰው፤ እንደ ከዚህ በፊቱ በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በቅርቡም በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የመመለሱ ዘመቻ መልሶ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
*ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በተለያየ መንገድ ክትትል ይደረግብናል በሚል ስጋት ማንነታቸው እንዳይገለጽ በመጠየቃቸው ስማቸው ተቀይሯል።















