በሳዑዲ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ላይ መሆናቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, HRW
በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የስደተኞች የማቆያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አስከፊ በሆነ አያያዝ ውስጥ እንደሚገኙ ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጸ።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት እንዳለው ሕጋዊ ሰነዶች ሳይኖራቸው ሥራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ የገቡት እነዚህ ስደተኞች ተይዘው የሚገኙበት ማዕከል የተጨናነቀ ከመሆኑ ባሻገር በጥበቃዎች ማሰቃየትና ድብደባ እንደሚፈጸምባቸውም አመልክቷል።
የማዕከሉ ጥበቃዎች በጎማ በተሸፈነ ብረት በሚፈጸምባቸው ድብደባ ጉዳት እንደሚደርስባቸው የገለጸው ሂማን ራይትስ ዋች፤ በጥቅምትና ኅዳር ወራት ውስጥ ቢያንስ ሦስት ለሚሆኑ ስደተኞች ሞት ምክንያት መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ባሉ የስደተኞች ማቆያ ውስጥ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረስውን ሰቆቃ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም በርካታ ሰዎች ከሳዑዲ እንዲወጡ ማድረጉ ይታወሳል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ በማቆያ ማዕከሉ ያሉት ስደተኞች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ፣ ድብደባ እንዳይፈጸምባቸውና ያሉበት የአያያዝ ሁኔታ በተገቢው መንገድ እንዲሻሻል ጠይቋል።
"ሃብታም ከሚባሉት የዓለም አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ስደተኞችን በዚህ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ለወራት በከፋ ሁኔታ መያዟ በምንም መልኩ አሳማኝ አይደለም" ሲሉ የሂማን ራይትስ ዋች የስደተኞች መብት አጥኚ ናዲያ ሃርድማን ተናግረዋል።
በዘራቸው ላይ የተመሰረቱ ማጥላላቶችና ስድቦች እንደሚሰነዘሩባቸው የገለጹት ስደተኞቹ በኮሮናቫይረስ የመያዝ ስጋት እንዳላቸውና በሚታመሙ ጊዜ ህክምና ለማግኘት በሚጠይቁበት ጊዜ በማቆያው ጠባቂዎች ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው ገልጸዋል።
በድብደባ ምክንያትም የሞቱ ሦስት ሰዎች እንዳሉ ስደተኞቹ እንደነገሩት የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ገልጿል።
በእነዚህ የማቆያ ማዕከላት ውስጥ ስላለው አስከፊ አያያዝ በተመለከተ ለረጅም ጊዜያት ቅሬታ ሲቀርብ የነበረ ሲሆን፤ በእነዚህ ቦታዎች ለሥራ ወደ ሳዑዲ የሄዱ በርካታ ስደተኞች ያለበቂ ምግብና መጠለያ በችግር እንዲቆዩ መደረጋቸውን ኢትዮጵያውያን ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ያናገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደነገሩት በማቆያ ማዕከሉ ውስጥ የቻድ፣ የጋና፣ የኬንያ፣ የናይጄሪያና የሶማሊያ ዜጎች ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን በቁጥር በርካታ ናቸው።
በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ባሉ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚሰሩ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ አገራት ዜጎች ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥም ተገቢው የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸውን ሰራተኞችን የማሰር ተግባር በተለያዩ ጊዜያት በመደበኝነት ሲካሄድ ቆይቷል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንዳለው በፈረንጆቹ ግንቦት ወር 2017 እና መጋቢት 2019 መካከል ባላው ጊዜ ውስጥ በየወሩ በአማካይ 10 ሺህ በአጠቃላይ 260 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ እንዲወጡ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኛ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ጉዳይን እንደሚከታተል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም ገልጸው፤ በተጨማሪም ጉዳዩን ለሳዑዲ ባለስልጣናት በማሳወቅ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከመጠየቅ ተቆጥበው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ውስጥ እየተፈጸሙ ናቸው ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ሕገ ወጥ ግድያን በተመለከተ መንግሥት ምርመራ እንዲያደርግና ጥፋተኛ በሆኑት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።














