በተማሪዎቹ 'ፕራንክ' የተደረገው መምህር በደረሰበት አደጋ ሕይወቱ አለፈ

ላውራ ሁጌስ የአበባ ጉንጉን ስታስቀምጥ

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, la
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ ውስጥ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ተማሪዎቹ ከፈጸሙት የቀልድ ድርጊት (ፕራንክ) ጋር ተያይዞ በመኪና ተገጭቶ ሞተ።

የጆርጂያ ግዛት ባለሥልጣናት እንዳሉት 'ቶይሌት ፔፐር ፕራንክ' የሚሉት አሜሪካ ውስጥ የተለመደ ጨዋታን ለመጫወት ተማሪዎቹ በመምህሩ ቤት አቅራቢያ በሚገኙ ዛፎች ላይ ሶፍት አድርገው በፈጠሩት ቀልድ ወቅት ነበር መምህሩን ለሞት የዳረገው አደጋ የተከሰተው።

ጄሰን ሁግስ የተባለው የ40 ዓመት መምህር ተማሪዎቹ በቤቱ ዙሪያ በሽንት ቤት ወረቀት ዛፎችን አሸብርቀው በነበረበት ጊዜ ከቤቱ ወጥቶ ሁኔታውን እየተመለከተ ሳለ በአካባቢው በዘነበ ዝናብ ምክንያት አንሸራቶት በወደቀበት በመኪና ተገጭቶ ነው ለኅልፈት የበቃው።

አደጋውን ያደረሱትም በመምህራቸው ቤት ዙሪያ ፕራንኩን ያዘጋጁት ተማሪዎች መምህራቸው እንዳያያቸው በያዟቸው መኪኖች ከአካባቢው ለመራቅ በፍጥነት እያሽከረከሩ ሳለ ነው የወደቀውን መምህር በመግጨት ጉዳት እንዳደረሱበት ፖሊስ አስታውቋል።

ተማሪዎቹ በመኪና የሰው ሕይወት በማጥፋት ክስ ቢመሠረትባቸውም የሟቹ መምህር ቤተሰቦች ግን ክሱ እንዲነሳ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

መምህሩን በዚህ መልኩ ገጭቶ ሕይወቱን ያጠፋውን ተማሪ በተሽከርካሪ አደጋ በማድረስ ወንጀል ክስ የቀረበበት ቢሆንም የሟች መምህር ቤተሰቦች ግን ክሱ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነችው የማቹ መምህር ባለቤት ላውራ ሁጌስ ባለቤቷ በተማሪዎች ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ እንደነበር ገልጻለች።

የፕራንክ ጨዋታው እንደሚደረግ ያውቅ እንደነበር እና ከልጆቹ ጋርም አባሮሽ ለመጫወት በጉጉት ሲጠብቅ እንደነበር ላውራ ተናግራለች።

አስተማሪውን ገጭቶ የገደለው ጄይደን ሪያን ዋላስ የተባለው የ18 ዓመት ተማሪ እና ሌሎች ሁለት ተማሪዎች የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጭዎች ከመድረሳቸው በፊት አስተማሪውን ፈጥነው ወደ ሆስፒታል ወስደውት ነበር።

ነገር ግን በሕይወት ማትረፍ አልተቻለም። ዋላስ እና ሌሎች አራት ተማሪዎች የሌላ ሰው ንብረት በማሽከርከር ወንጀል ተከሰዋል።

ነገር ግን የሟቹ መምህርባለቤት ላውራ የተማሪዎቹን ክስ ለማቋረጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

"አስደንጋጭ አደጋ ነው፣ ነገር ግን ቤተሰባችን የእነዚህ ተማሪዎች ሕይወት እንዲመሰቃቀል አይፈልግም" ብላለች ላውራ።

"ይህ ጄሰን ልጆቹን ለመቅረጽ ከደከመለት ዓላም የሚጻረር ነው" ብላለች።

የአካባቢው ኅብረተሰብ ሁጌስ ያስተምርበት እና ያሰለጥንበት በነበረው አካባቢ ላይ መታሰቢያ ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው።