ማኅበረሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን "በከፍተኛ ቁጠባ" እንዲጠቀሙ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሳሰቡ

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

የፎቶው ባለመብት, FANA/YOUTUBE

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት እና በዚሁ ምክንያት የተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ ሕብረተሰቡ እና ተቋማት ነዳጅን "በከፍተኛ ቁጠባ" እንዲጠቀሙ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አሳሰቡ።

በጦርነቱ ምክንያት የታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ "አስፈሪ" ሲሉ የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት "በቅርቡ ተጨማሪ የነዳጅ ቁጠባ እርምጃዎችን" ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ይህንን ማሳሰቢ የሰጡት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም. የኢራን ጦርነት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የፈጠረውን ቀውስ እና በአገር ውስጥ ያለውን የነዳጅ ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ሚኒስትሩ ይህንን መግለጫ የሰጡት መንግሥት በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ እስከ 17 ብር የሚደርስ ጭማሪ ባደረገ ማግሥት ነው። ማክሰኞ ይፋ በተደረገው የዋጋ ጭማሪ መሠረት 129 ብር ሲሸጥ የነበረው ቤንዚን 132 ብር ከ18 ሳንቲም ገብቷል።

ተመሳሳይ ዋጋ የነበረው ነጭ ናፍጣ ደግሞ የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎበት ዋጋው ወደ 139 ብር ከ84 ሳንቲም ከፍ ብሏል። ከፍተኛ የሆነው የ17 ብር ጭማሪ ያስተናገደው ኬሮሲን ደግሞ 146 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ከታየው ከፍተኛ ጭማሪ አንጻር መንግሥት ያደረገው ማሻሻያ "በጣም ዝቅተኛ ተደርጎ የሚታይ" እንደሆነ ገልጸዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የከፈቱባት ኢራን በአጸፋው ከዓለም ነዳጅ አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች። በተጨማሪም በጦርነቱ የኢራን እና የሌሎች የመካለኛው ምሥራቅ አገራት የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ጥቃት ተፈጽሙባቸዋል።

በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት በበርሜል 120 ዶላር ገብቶ ነበር። ኋላ ላይ ግን ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በበርሜል 89 ዶላር እየተሸጠ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፤ "የዓለም ዋጋ በትንናትነው ዕለት ደረሰበት፣ ጂቡቲ ላይ የምንረከብበት ዋጋ በምናይበት ጊዜ ቤንዚን 205 ብር ከ74 ሳንቲም መሆን ነበረበት። […] አሁንም መንግሥት ቤንዚንን በሊትር 73 ብር ከ56 ሳንቲም እየደጎመ የሚገኝ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።

ነጭ ናፍጣም በዓለም ዋጋ በሊትር 238 ብር ከ13 ሳንቲም እንደደረሰ በመጥቀስም፤ በሊትር 98 ብር ከ29 ሳንቲም በመንግሥት እየደጎመ መሆኑን አስረድተዋል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ፣ አስፈሪ በሆነ መልኩ እየጨመረ ባለበት ጊዜም ቢሆን በከፍተኛ ድጎማ አሁንም እየቀረበ [ነው]" ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ ነዳጅ "በተቀመጠለት የግብይት ሰንሰለት" እና "መንግሥት ባስቀመጠው ዋጋ ብቻ" መሸጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ ቀውስ ሊያስከትል ሚችለውን "ጫና ለመቋቋም የሚያስችለውን አማራጭ" እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል። ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል ከዲፖ ማቅረብ እና አጣዳፊ ግዢ መፈጸም የሚሉትን ጠቅሰዋል።

የነዳጅ መቅጃ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን መስተጓጎል "ለመቋቋም እንዲቻል በሌሎች አማራጮች በአፋጣኝ የነዳጅ ግዢ" ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ገልጸዋል።

አህመድ አክለውም የመካከለኛው ምሥራቅ ፈጠረው ይህ ቀውስ ምን ያህል ሊቆይ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አንስተዋል።

"በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት መቼ እንደሚያቆም እና የተፈጠረው የነዳጅ ምርት ላይ ደረሰው ውድመት እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠረው ችግር እስከ መቼ እንደሚዘልቅ መገመት [እንደማይቻል]" ተናግረዋል።

በመንግሥት ጉዳዩን እየተከታተለ በአገር ውስጥ የነዳጅ "በአስተማማኝ መልኩ እንዲቀርብ" እንደሚደርግ ያነሱት አህመድ፤ "ከዚህ ጎን ለጎን ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ቁጠባ ሥራ ውስጥ መግባት ይኖርብናል" ብለዋል።

"ሁሉም ነዳጅ ተጠቃሚ አካላት፣ እና መላው ማኅበረሰቡ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ መንግሥዊ ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሁሉም ነዳጅ ተጠቃሚ አካላት በሙሉ ነዳጅን በከፍተኛ ቁጠባ መጠቀም እንዳለባችሁ ማሳሰብ እንፈልጋለን" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህም ባሻገር "በቅርቡ በተጠና ሁኔታ ተጨማሪ [የነዳጅ] የቁጠባ እርምጃዎች ለሕብረሰቡ የሚገለጹ ይሆናል" ሲሉ በመንግሥት ይፋ የሚደረጉ አሠራሮች እንደሚኖሩ አስታውቀዋል።

በአገር ውስጥ የሚታየውን ትክከለኛውን የግብይት ሰንሰለት አለመጠቀም እና መንግሥት ባስቀመጠው ዋጋ ያለመሸጥ ሁኔታ ለማስተካከል የሚወሰደው እርምጃ እንደሚጠናከርም የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ገልጸዋል።