ሩሲያ ዩክሬናዊያን ሕጻናትን አግታ መውሰዷ የጦር ወንጀል መሆኑን ተመድ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AP
ዩክሬናዊያን ሕጻናት ታግተው በግዳጅ ወደ ሩሲያ መወሰዳቸው ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንዲሁም የጦር ወንጀል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ።
በዩክሬን ምርመራ ያደረገው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዳለው፤ ሩሲያ በቁጥጥሯ ሥር ካዋለቻቸው የዩክሬን ግዛቶች "በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን" ወስዳለች።
በዚህም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "በቀጥታ ተሳታፊ መሆናቸው ግልጽ ነው" ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ወደ 20,000 የሚጠጉ ሕጻናት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሩሲያ እና ቤላሩስ መወሰዳቸውን ዩክሬን ገልጻለች።
የተመድ ኮሚሽን በአውሮፓውያኑ 2022 በሩሲያ የተወሰዱ 1,205 ሕጻናትን ጉዳይ መርምሯል። ከሕጻናቱ 80% የሚሆኑት የት እንዳሉ ወላጆቻቸው የማያውቁ ሲሆን እስካሁን ድረስም ወደ አገራቸው አልተመለሱም።
ተመድ እንዳለው በሕጻናቱ ላይ የተፈጸመው የግዳጅ ስወራ እና ያለ ምክንያት ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እንዲቆዩ ማስገደድ ሲሆን፤ ይህም በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል እንዲሁም በጦር ወንጀልነት ይፈረጃል።
አብዛኞቹ ሕጻናት ይኖሩ የነበረው ሩሲያ በቁጥጥር ሥር ባዋለቻቸው ዶንተስክ እና ሉሀንስ በተባሉ የዩክሬን ግዛቶች ነው።
ሩሲያ ሕጻናቱን ከዩክሬን ግዛት የወሰደችው በዩክሬን "ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላል" በሚል መሆኑን ተመድ ገልጿል። ሕጻናቱ ሩሲያ ከተወሰዱ በኋላ ከተለያዩ ቤተሰቦች ጋር እንዲኖሩ ተደርገው የሩሲያ ዜግነት ተሰጥቷቸዋል።
ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ሕጻናትን በግዳጅ ወስዳለች የሚለውን ክስ አስተባብላለች።
ፑቲን በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር "ልጆች ታፍነው ተወስደዋል የሚለው ግነት ነው። ሕጻናትን ከጦር ቀጠና ታድገናል። ሕጻናቱን ወደ አገራቸው ለመመለስም አያስቸግረንም" ብለዋል።
ዩክሬን በበኩሏ ሕጻናቱ ወደ ዩክሬን ለመመለስ መሰናክል እንደገጠማቸው ገልጻለች።
የተመድ መርማሪ ኮሚሽን "ከትውልድ አገራቸው ታግተው መወሰዳቸው እና ሩሲያ ውስጥ የሚደርስባቸው ጫና ለከፍተኛ ጭንቀት አጋልጧቸዋል" ሲል ሕጻናቱ ያሉበትን ሁኔታ ገልጿል።
ወደ አገራቸው መመለስ የቻሉ ሕጻናት ሩሲያ ሳሉ በደረሰባቸው ጫና ምክንያት "ጭንቀት እና የመተው ፍርሃት" እንደሚገጥማቸው ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል።
በሩሲያ የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉ ዩክሬናዊያን ታዳጊዎች "ከዚህ በኋላ ዩክሬን የምትባል አገር ወድማለች። ወላጆቻችሁም ሞተዋል" እየተባለ እንደሚነገራቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
አንድ ዩክሬናዊት እናት "አሁንም ድረስ ልጄን እየፈለግኳት ነው። ስለ እኔ ምን ታስብ ይሆን ብዬ እጨነቃለሁ። ዩክሬናዊያን በሚጠሉበት ሩሲያ እንዴት እየኖረች ይሆን?" ብላለች።
በአውሮፓውያኑ በ2023 ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
የሩሲያ የልጆች መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቫ-ቤሎቫ እና ፑቲን ላይ ከቀረቡ ክሶች መካከል ዩክሬናውያን ሕጻናትን አግቶ መውሰድ ይገኝበታል።
ኮሚሽነሯ የ15 ዓመት ዩክሬናዊ ታዳጊን "ለማሳደግ መውሰዳቸውን" በአንድ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
ታዳጊው የተወለደበት ማሪፑል ከተማ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው። ኮሚሽነሯም ታዳጊውን "እንደ አዲስ እያስተማሩ" እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሆኖም ግን ታዳጊው ወደ ሩሲያ መሄድ እንደማይፈልግ ገልጾ ነበር።
ዩክሬን እስካሁን 2,000 ሕጻናትን ማስመለስ እንደቻለች አስታውቃለች።
የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ሕጻናቱን ለማስመለስ ንቅናቄ በማድረግ ይታወቃሉ። "ከፑቲን ጋር የምወያይበት መንገድ አለኝ" ያሉት ሜላኒያ ለፕሬዝዳንቱ ይፋዊ ደብዳቤም ልከዋል።
በአምስት ዓመቱ ጦርነት ከ15,000 በላይ ንጹኃን ዜጎች ሲገደሉ፤ ከ41,300 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል። 3.7 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።















