ለስድስት ዓመት ተቋርጦ የነበረው የቻይና-ሰሜን ኮሪያ የባቡር መንገድ ተከፈተ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ለስድስት ዓመት ተቋርጦ የነበረው ከቻይና ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚወስደው የባቡር መስመር መከፈቱ ተገለጸ።
ከነገ ሐሙስ ጀምሮ በሳምንት ለአራት ቀናት ከቤጂንግ ወደ ፒዮንግያንግ የሚደረገው የባቡር ጉዞ ይጀመራል።
ጉዞው ተቋርጦ የነበረው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሲሆን፤ ዳግመኛ መጀመሩ "የሁለቱን አገራት ወዳጅነት እንደሚያጠናክር" የቻይና ባቡር ባለሥልጣን አስታውቋል።
ከወረርሽኙ በኋላ ቻይና ወደ መደበኛው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ብትመለስም ሰሜን ኮሪያ ገደቦችን ለማላላት ጊዜ ወስዶባታል።
ከአውሮፓውያኑ 2024 ወዲህ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚገቡ የቱሪስቶች ቁጥር ቀስ በቀስ ከፍ እንዲል ተወስኗል።
ከቤጂንግ ወደ ፒዮንግያንግ በሚወስደው ባቡር መሳፈር የሚችሉት ዓለም አቀፍ ተጓዦች ቁጥር አሁንም ውስን እንደሚሆን ተገልጿል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጉዞ ወኪሎች እንደገለጹት እስካሁን ድረስ ለነጋዴዎች እና ቱሪስቶች በቂ የባቡር ትኬት ይፋ አልተደረገም። የባቡር ትኬት ለመግዛት ቪዛም ያስፈልጋል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው አሁን ላይ ቪዛ ያላቸው በሰሜን ኮሪያ የሚማሩ፣ የሚኖሩ ወይም ቤተሰብ የሚጠይቁ ቻይናውያን ናቸው።
ነገ የመጀመሪያው ጉዞ ለሚደረግበት ባቡር፤ ገበያ ላይ የቀረቡ ትኬቶች ተሽጠው ማለቃቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጿል።
በብዛት የባቡር ትኬት የቆረጡት ነጋዴዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ጋዜጠኞች ናቸው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጉዎ ጂኩን "በሁለቱ አገራት መካከል ዘላቂነት ያለው ትራንስፖርት መኖሩ ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በላኩት ደብዳቤ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትስስር "ሶሻሊስት መርሕን ተከትሎ የበለጠ እንደሚጠናከር" ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ኪም ይሄንን ደብዳቤ ከመላካቸው ከአንድ ወር በፊት ዢ በላኩላቸው ደብዳቤ፤ የደቡብ ኮሪያ ገዢ ፓርቲ መሪ ሆነው በመመረጣቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
ደቡብ ኮሪያን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ቻይናውያን ናቸው።















