ተተኪ ልትሆን ትችላለች ስለተባለችው የሰሜን ኮሪያው መሪ ልጅ ምን እናውቃለን?

የፎቶው ባለመብት, KCNA
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ላይ ድል የተቀዳጀችበትን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ለማክበር ወደ ቤይጂንግ ማቅናታቸው የመገናኛ ብዙኃን መነገጋሪያ ሆኗል።
የድል በዓል ለመታደም ከስድስት ዓመታት በኋላ ወደ ቻይና የሄዱት ኪም ከቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተዋል።
በዚህ የመሪው ጉብኝት ሴት ልጃቸው ኪም ጁ አየ አጅባቸው ሄዳለች።
ኪም የጦር መሳሪያ በታጠቀው ባቡራቸው ሲወጡ ጥቁር ኮፍያ እና ጃኬት ያደረገችው ሴት ልጃቸው የበርካቶችን ቀልብ ስባለች።
እንደ የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት ከሆነ ኪም የአባቷ የሥልጣን ወራሽ ልትሆን እንደምትችል ነው።
ስለ ኪም ዕድሜዋን ጨምሮ የሚታወቁ መረጃዎች በጣም ውስን ናቸው። ስለሷ ምን እናውቃለን?
የፕሬዝዳንቱ ኪም ጆንግ ኡን እና ባለቤታቸው ሪ ሶል ጁ ሦስት ልጆች መካከል ሁለተኛዋ እንደሆነች ይታመናል። ሆኖም ፕሬዝዳንት ኪም ስለ ቤተሰባቸው ካላቸው ጥብቅ ምሥጢራዊነት የተነሳ የልጆቹ ቅደም ተከተልን በተመለከተ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ፕሬዝዳንት ኪም ባለቤታቸውን ለሕዝብ እንኳን ያስተዋወቁት ከተጋቡ ከዓመታት በኋላ ነው።
እስካሁን ድረስ በአገሪቱ አመራር የተረጋገጠውም ሆነ ለሕዝብ ዕይታ የበቃችው ብቸኛ ልጃቸው ናት።
ሌላ ልጃቸው በአደባባይ ታይቶ አይታወቅም።

የፎቶው ባለመብት, KCNA
ፕሬዝዳንት ኪም ልጅ እንዳላቸው መጀመሪያ የተሰማው ተገማች ካልሆነ ምንጭ በኩል ነበር።
ታዋቂው አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ዴኒስ ሮድማን ምሥጢራዊ ወደሆነችው ሰሜን ኮሪያ ባደረገው ጉዞ "ልጃቸው ጁ አየን አቅፎ እንደነበር" በአውሮፓውያኑ 2013 ከዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ተናገረ።
ከዚያም በኋላ ስለ ልጅቷ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ ምንም አልተሰማም።
ከሦስት ዓመታት በፊት አባቷ የአገራቸውን አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳዔል ይፋ ሲያደርጉ አጠገባቸው ነበረች።
ከዚያም በኋላ ፎቶዋ በፖስታ ቴምብሮች ላይ ታትሞ የወጣ ሲሆን፣ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ግብዣ ላይ የኪም ጆንግ ኡን "የተከበረች" ሴት ልጃቸው ተብላ መቅረብ ጀመረች።
የተከበረ/የተከበረች የሚለው ቅጽል በሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ስፍራ ላላቸው ሰዎች የሚሰጥ ማዕረግ ነው።
ፕሬዝዳንት ኪም "የተከበሩ ጓድ" የሚል ስያሜ ያገኙት የወደፊት መሪነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ስለዚች ትንሽ ልጅ ጥቂት ተጨማሪ መረጃዎችን ለፓርላማ አባላት መስጠቱን የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።
ፈረስ ግልቢያ፣ የበረዶ ሸርተቴ እና መዋኘት ትወዳለች።
በሰሜን ኮሪያ መዲና ፒዮንግያንግ በመኖሪያ ቤታቸው ትምህርቷን ትከታተላለች።
ዕድሜዋም 10 ዓመት አካባቢ እንደሆነች መረጃው ጠቁሟል።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት በተጨማሪም ይህች ትንሽ ልጅ ተተኪያቸው ልትሆን እንደምትችል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ኪም ዕድሜያቸው ወጣት ከመሆኑ በተጨማሪ ሌሎች "ተለዋዋጭ ምክንያቶች" ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, KCNA
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበርካታ አጋጣሚዎች ከአባቷ ጎን ትታያለች።
ከአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ጅማሮ እንዲሁም ወታደራዊ ትዕይንቶች ላይ ከአባቷ ጎን ቆማ የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ወታደራዊ ሰላምታ ሲሰጧት ታይተዋል።
ነገር ግን ልጃቸው ማክሰኞ ዕለት ከሰሜን ኮሪያ ውጭ የታየችበት ከመሆኑ አንጻር ታሪካዊ ሲሆን፣ እንዲሁም ይህ ጉዟቸው ኪምን በቀጣይነት ማን ሊተካ ይችላል የሚሉ ግምቶችን የበለጠ ያቀጣጥላል።
ከአውሮፓውያኑ 1947 ጀምሮ ሰሜን ኮሪያን የመሩት የኪም ቤተሰቦች ሥልጣን በደም እንደሚወራረስ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
የእነሱ ዝርያ የተቀደሰ እንደሆነ በመግለጽ አገሪቱን መምራት የሚችሉት እነሱ ብቻ እንደሆነ አመላክተዋል።
ፕሬዝዳንት ኪም ሴት ልጃቸውን ለመሪነት በማጨት በወንዶች መሪነት ብቻ የተሞላውን ታሪክ ለመቀየር እንደሚፈልጉ ይነገራል።
ሰሜን ኮሪያን እስካሁን ድረስ ባለው ሴት መርቷት የማያውቅ ሲሆን፣ የሚነሳባቸውን ትችትም ለመቀልበስ ነው ተብሏል።















