ፕሬዚዳንት ሺ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ ባደረጉበት ወታደራዊ ትዕይንት፤ 'ቻይና በጉልበተኞች አትሸበርም' አሉ

በትዕይንቱ ከቀረቡ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ግዙፍ ውሃ ጠላቂ ድሮኖችን ጨምሮ አዳዲስ የረቀቁ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ ባደረጉበት ወታደራዊ ትዕይንት የቻይናን ግስጋሴ መግታት እንደማይቻል ተናገሩ።

ሺ "አገራቸው በጉልበተኞች አትሸበርም" ሲሉም የድል ቀን እየተባለ በሚጠራው ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓን ድል የተቀዳጀችበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ተናግረዋል።

በዚህ ታላቅ የወታደራዊ በዓል የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ 26 መሪዎች ተገኝተዋል።

ሶስቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት በዚህ ወታደራዊ ትዕይንት ቻይና የሌዘር መሳሪያዎች፣ የኒውክሌር ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን ይፋ አድርጋለች።

ፕሬዚዳንት ሺ በዚህች ዕለት ቻይናውያን የሰው ልጅ ስልጣኔን ለመታደግ "ታላቅ ብሔራዊ መስዋዕትነት ከፍለዋል" ብለዋል።

"ታሪክ የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ የተሳሰረ እንደሆነ እና አነሳሱም ሆነ ውድቀቱ በአንድ ላይ መሆኑን ያስገነዝባል" ሲሉም ተናግረዋል።

"ቻይና በማንኛውም ጉልበተኛ አትሸበርም፤ ሁልጊዜም ወደፊት እንደገሰገች ነው" ሲሉ የአገራቸውን አቋም አሳውቀዋል።

"አዲስ ጉዞ፣ አዲስ ዘመን ነው" ያሉት ሺ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች የቻይናን ኮሚኒስት ፓርቲ መከተል እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

"የቻይናን እሴት በጠበቀ መልኩ በሶሻሊዝም ጎዳና ላይ አጥብቀን መቆየት አለብን" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሺ ከወታደራዊ ትዕይንቱ በፊት በማዕከላዊ ቤጂንግ በሚገኘው ቻግንአን ጎዳና ላይ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወታደሮቻቸው ሰላምታ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሆንግኪ ከተሰኘ ጥቁር ተሽከርካሪያቸው ሆነው ነው ለወታደሮቻቸው ሰላምታ የሰጡት፤ እንዲሁም ንግግር ያደረጉት።

በትዕይንቱ ከቀረቡ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከወታደራዊው ትርዒት በፊት ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓን ላይ ድል የተቀዳጀችበት 80ኛ ዓመት ለማመላከትም 80 ጊዜ ጠመንጃ ተተኩሷል።

የክብር ዘብ አባላትም በቲያንመን አደባባይ ላይ በተዘረጋው ቀይ ምንጣፍ ላይ የቻይናን ሰንደቅ ዓላማ የያዘ ወታደር በክብር አጅበው ሲራመዱ ታይተዋል።

የቻይና ብሄራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሰንደቅ ዓላማዋም ከፍ ብሎ ተውለብልቧል።

ቻይና በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ታንኮችን እንደሁም የፀረ ድሮን ስርዓቷን ጨምሮ የታጠቀቻቸውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች በበዓሉ ላይ አሳይታለች።

በወታደራዊ ትዕይንቱ ላይ ዓሉ የቻይና ጦር ሠራዊት አባላት እና ጡረታ የወጡ ወታደሮችን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ከቲያንመን አደባባይ ተሰልፈው ነበር።

ከአንድ ሰዓት በላይ በቆየው ወታደራዊ ትዕይንት በተንታኞች እና በምዕራቡ ዓለም ጥብቅ ክትትል የተደረገበት ነው።

ርዕሰ መዲናዋ ቤጂንግ በዚህ ግዙፍ የወታደራዊ ትዕይንት ለመታደም የሚመጡ በርካታ የዓለም መሪዎችን ለመቀበል በከፍተኛ ሁኔታ ደምቃ ታይታለች።

በዚህ ዝግጅት ላይ ከታደሙት መሪዎች አንዱ ኪም ጆንግ ኡን በቻይና ከስድስት ዓመታት በኋላ ሲገኙ ነው።

በዚህ ወታደራዊ ትዕይንት እንዲታደሙ ከተጋበዙት መካከል የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ የቪየትናም ፕሬዚዳንት ሉዎንግ ኩዎንግ፣ የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን እንዲሁም የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል ተጠቅሰዋል።